የተረገምንበት ጊዜና ምክንያቱ

አለልታወቅ ብሎ ከጠዋት ከጥንቱ
ከትውልድ ትውልድ እየተሻገረ
ይላላል ያልነው ብሶ እየከረረ
ችግር በሽታችን ዘመን አስቆጠረ፤
ከእውነተኛው ታጋይ- የአስመሳዩ ቁጥር እጅግ ስለላቀ፣
ግድያ ፍጅቱ ከአደባባይ አልፎ እስር ቤት ዘለቀ፡፡

2010 ከባተ ገና ሁለተኛ ወሩን ያልጨረሰ በሆንም በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ ብቻ ያየን የሰማናቸው ነገሮች ፖለቲከኛ ነኝ ለለውጥ እየታገልኩ ነው የሚሉትን ቀርቶ ማናቸውንም ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ እንቅልፍ የማያስተኛ ነበር፡፡ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተፈጸመውን ሰምተን ከንፈር መጠን አጀኢብም ብለን ሳናበቃ (የእኛ ተቃውሞም ሆነ ቁጣ ከዚህ አይዘልም) ኢሉባቡር ላይ ሌላ ፍጅት ሌላ አልቂት ተፈጸመ፡፡ ይህኛውን ገና በወጉ አዝነንበት አይደለም አውርተንበት ሳንጨርስ ከትናንት በስቲያ አምቦ ላይ ሌላ የግፍ ግድያ ተፈጸመ፡፡በእኔ አረዳድ የአንቦው ሁለት መሰረታዊ ልዩ ገጽታዎች ተንጸባርቀውበታል፡፡ የመጀመሪያው የወያኔ ቅኝ ገዢነት የተረጋገጠበት ሁለተኛው የኦህዴድ ሰዎች ትእግስት በሉት ሎሌነት ወደ ጫፍ እየደረሰ መሆኑ መታየቱ ነው፡፡

የወያኔ ቅኝ ገዢነት፤ ይህን ሳስብ በ1980ዎቹ መጨረሻ ያነበብኳት ግጥም ትውስ አለችኝ፡፡ እንዲህ ትላለች፡፡

ወገንን ጨፍጫፊ ቆዳው የነጣ ነው፣

በአበሻ የሚጨክን ፈረንጅ ብቻ ነው

እያለ የሚያስብ የዋህ ፍጡር ማነው

ጨፈጫፊ ከሆነ አበሻም ጣሊያን ነው

እንቶኔም በተግባር ሲኞር እንቶኔ ነው፡፡ ይህን ያሉት ሰው ዛሬ በህይወት ካሉ ምን ይሉ ይሆን?

የአንቦ ከተማ መስተዳድር ቃል አቀባይ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛው ክፍል እንደገለጹት ገዳዮቹ ቀይ መለዮ የደፉና ሌሎችም የመከለካያ ሰራዊት አባላት ናቸው፡፡ከእኝህ ባለሥልጣንም ሆነ ከአይን እማኞች እንደተገለጸው የግድያው ምክንያት አንድ ኪሎ ስኳር 60 ብር መግባቱና በዚህም ዋጋ አንቦ ላይ ማግኘት ችግር በሆነበት ወቅት የስኳር ህገ ወጥ ንግድ መጧጧፉና ስኳር ጭነዋል የተባሉ ተሸከርካሪዎች በዛ መስመር እየተጓዙ መሆኑ መሰማቱን ተከትሎ ሰው አናሳልፍም ብሎ መከልከሉ ነው፡፡ ህገ ወጥ ንግድን መቃወም ይደገፋል፣ ይበረታታል፣ ያስመሰግናል፣ ሲሆንም ያሸልማል እንጂ እንዴት ጥይት ለመተኮስና ሰው ለመግደል ያበቃል፡፡ ይህ ነገር አውቆ ለተኛ ካልሆነ በስተቀር ለማንም ምሥጢር ሊሆን አይችልም፡፡ የተጫነው ስኳር የወያኔዎቹ በመሆኑ ነው እንዴት ተደፈርን በማለት እንደ ሮቦት የሚታዘዘውን ገዳይ ሀይላቸውን ልከው ማስገደላቸው፡፡

የአንድ ሀገር መንግሥት ነኝ ባይ ሲጀመር በዝርፊያ ተግባር አይሰማራም፣ ከሆነም ደግሞ ሲነቃበት ማምለጫም ማሳለጫም መንገድ ይፈልጋል እንጂ በህዝብ ላይ ጥይት አያዘንብም፡፡ እንዲህ የሚያደርገው ቅኝ ገዢ ብቻ ነው፡፡ የሚገዛውን ሀገር ህዝብ ስለ ሰው ስለማይቆጥር፡፡ ይህም ነው እንግዲህ ከብዙዎቹ ሰይጣናዊ ተግባራቱ ጋር ተዳምሮ ወያኔን ቅኝ ገዢ ነው ለማለት ያበቃኝ፡፡በየቦታው በወያኔ ሀይል ስለሚፈጸመው ነገር የአካባቢው ባለሥልጣን ተብዬዎች የማያውቁ፣ ለማወቅ ቢፈልጉም የማይችሉ የማፈቅድላቸው መሆኑ ደግሞ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የለም የሚለውን መከራከሪያችንን የሚጠናክር ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ከሳምንት በፊት ወደ ሶማሌ ክልል የሚልፉ ምን እንደጫኑ ያልታወቁ መኪናዎችን የአካባቢው ነዋሪ አላሳልፍም ብሎ በማገዱ ግድያ ሲፈጸምበት የአካባቢው መስተዳድር ግድያውን መከላከል ቀርቶ መኪናዎቹ የጫኑትን ነገር ምንነት ተጠግቶ ለማየት ያለመቻሉን ከአካባው ስመ ባለሥልጣኖች አንዱ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡

ሁለተኛው የተለየ ገጽታ የታየበት ያልኩት በአምቦ የተፈጸመውን ግድያ እንዴትነትና የገዳዮቹን ማንነት ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የየገለጹት የአካባቢው መስተዳድር ቃል አቃባይ ከእንግዲህ የምንደብቀው ነገር አይኖርም እውነቱን ለሚመለከተው ሁሉ እንገልጻለን ያሉበት ነው፡፡ ከንግግራቸው በላይ ይህን ሲናገሩ ከውስጣቸው የሰማነው ስሜት ኦህዴዶች የወያኔ አገዛዝ ከሚሸከሙት በላይ እየሆነ ያንገሸገሻቸው ነው የሚመስለው፡፡ ግን አንድ ጥያቄ ላንሳ፡ እነርሱ በቃን ብለው ከወያኔ ጋር ያላቸውን የጋብቻ ውል ለመቅደድ ከዚህ በላይ ምን ሲፈጸም ማየት ይኖርባቸው ይሆን? ከአመት በፊት ይመስለኛል የብአዴንና የኦህዴደ አገላጋይነት እስከምን ድረስ የሚል ርእስ በሰጠሁት ጽሁፌ “…ብአዴንም ሆነ ኦህዴድ እንደ ድርጅት ሎሌነት በቃን ነጻነት እንሻለን ቢሉ፤ለየግል ጥቅማችን ስንል እንወክለዋለን የምንለውን ህዝብ ማስጠቃቱ ማስናቁ ይበቃል፣ ከእንግዲህ የህውሀትን የሞግዚት አስተዳደር አንሻም በህገ መንግስት ያሰፈርነው የክልሎች ነጻነት ተግባራዊ ይሁን ወዘተ ብለው ቢወስኑ ለሀጢአታቸው ስርየትን ለበደላቸው ይቅርታን ሊያስገኝላቸው ይችላል፡፡”ነበር ያልኩት፡፡ ይህን ማድረግም መሆንም ባለመቻላቸው እነርሱ ስመ ሥልጣን ይዘው በተቀመጡበት መንደር ድረስ እየዘለቁ ዛሬም ወያኔዎች ይገድላሉ ይደበድባሉ ያስራሉ፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖ እንጂ አነሳሴ እስከ አፍንጫቸው በደም ለተነከሩት ኦህዴዶች ዛሬም እንደ አምናው መልእክት ለማስተላለፍ አይደለም፡፡ከቢሮና ከማህተም እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ከመመዝገብ የዘለለ የፓርቲ አቅምም ቁመናም የሌላቸው ነገር ግን ለወያኔ መናጆነት አስፈላጊ በመሆናቸው ወያኔን ከበው እየተደራደርን ነው በማለት በህዝብ ደም ለሚያላግጡት ለዴሞክራሲ በሚደረገው ትግል ለሚቆምሩት ፖለቲከኛ ነን ባዮች የተሰማኝን ለመግለጽ ነው አነሳሴ፡፤

ገና ሀ ብሎ ስለ ድርድር ሲወራ ድረድሩ በሚል ርእስ የተሰማንን ገልጬ ነበር፡፡ አንዳንድ በውጪ የሚኖሩ ወያኔ ልብ ገዝቶ ከጥፋት ተመልሶ ስልጣን የምናገኝበትን ሁኔታ ይፈጥርልናል በሚል ከወያኔ ሰፈር ለሚሰማው ነገር ሁሌ አዲስ እየሆኑ የተካደውን ረስተው ለሚነገረው አፋቸውን የሚከፍቱ ድርድሩ ገና ሳይጀመር መቃወም ለምን አስፈለገ በሚል በተቃወሙት ጽሁፍ ውስጥ…
“..የሚሰጡት የሌላቸው፣ ወያኔን ወደ ድርድር ባመጣው የህዝብ ትግል ውስጥ ጠብታ አስተዋጽኦ ያልነበራቸው፤ በተናጠል ፓርቲ ለመባል የማይበቁ፣ በጋራ፣ የጋራ የመደራደሪያ አጀንዳ ቀርጾ ለመቅረብ የሚያስችል የትግል አንድነትም ሆነ የአንድ ሀገር ልጅነት ፍቅር የሌላቸው ምን ለማትረፍ ነው ወደ ድርድሩ መድረክ ያመሩት ብሎ መጠየቁ ተገቢ ቢሆንም እንደ ስማቸው ፍላጎታቸው የበዛ፣ እንደ ብዛታቸው መልካቸው የተዥጎረጎረ ነውና አንድ ወጥ የሆነ ምላሽ ማግኘት የዳግታል፡”በማለት የታየኝን ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡

ግድያን ማስቆም ያላስቻለ ድርድር፤ ተቀዋሚዎች ጋር አብረን እየሰራን ነው በሚለው ፕሮፓጋንዳ ቢያንስ አውቀው የሚታለሉትን የውጪ ኃይሎች እታለለና እያማለለ በመሸ በነጋ ዜጎችን ይገድላል ያሳቃያል፡፡ ምን ታመጣላችሁ ንቀቱ ገደብ አጥቶ ግድያው ከአደባባይ ወደ እስር ቤትም ተሸጋግሯል፡፡ በዚህ ወቅት ሌላው ቢቀር ሰው መግደላችሁን አቁሙ፤ግድያ የፈጸሙትን በግልጽ ስማቸውን ለህዝብ ይፋ አድርጉ ለፍርድም አቅርቡ፣ ይህ ባልሆነበት በድርድሩ ለመቀጠል እንቸገራለን ማለት አለመቻልና እየተሞዳሞዱ መቀጠል በግድያው ተባባሪነት በጭፍጨፋውም ደጋፊነት ሊያስጠይቅ እንደሚችል አልተረዱ ከሆነ በርግጥ እነዚህ ፖለቲከኛ ናቸውን ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል፡፡

አንድ የወረዳ መስተዳድር ቃል አቀባይ የኦህዴድ አባል ምሬቱ በዝቶበት አይኑ ስር የሚፈጸመውን ግድያ እያየ የሚልፍበት ህሊናው ለምን እንዴት በሚል ተፈታትኖት ከእንግዲህ ምንም የምንደብቀው ነገር የለም ማለት ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ እልቂት በነገሰበትና የወያኔ ቅኝ ገዢነት በገሀድ በታየበት ብሎም ፌዴራላዊ አስተዳደር ብሎ ነገር አለመኖሩ በራሳቸው አድራጎት በተረጋገጠበት ወቅት ይህን ሁሉ ጆሮ ዳባ ብሎ ድርድር እያሉ ማላዘኑና ወያኔን አጅቦ እሽኮለሌ ማለቱ ከወያኔ ባላነሰ ህዝብን መናቅ ነው፡፡

አምቦ ላይ የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ ፈጥኖ መግለጫ ያወጣው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ወገኖቻችን የተገደሉበትን ምክንያት የማያውቅ ሆኖ አይደለም ዜጎች ሀሳባቸውን በነጻነት የሚገልጡበት ሁኔታ እንዲኖር እናሰምርበታለን ቅብጥርሴ የሚል ለዘብተኛ መግለቻ ያወጣው፡፡

አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ኃያላን የሚባሉት ጉልበተኛ መንግስታት ከወያኔ ጋር ያላቸውን ፍቅር ህዝብ ምን ይለናል በሚል ትንሽ የማስመሰያ ለወጥ እንኳን ለማድረግ ያልበቁት ወያኔ እናንተን አሰልፎ ማጫወት በመቻሉ መሆኑ አልገባችሁ ይሆን? ወይንስ ከወያኔ የምታገኙት ትርፍ በህዝብ አልቂት እንድታፌዙ የሚያበቃችሁ አልያም የሚያስገድዳችሁ ሆኖ፡፡
እኛም ሆንን የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ ሁሉ ወያኔም ጭምር ምንም የሌላችሁ ምንም ማድረግ የማትችሉም እንደሆናችሁ እንውቃለን፣ ያውቃሉ እናንተም ታውቃላችሁ፡፡ ነገር ግን ወያኔ በእናንተ አጫዋችነት በሚያካሂደው ጨዋታ እየገደለም እያሰረም የውጪው ርዳታና ብድር ሳይነጥፍበት የወዳጆቹም ፊት ሳይጠቁርበት ለመኖር ስላስቻለው በእጅጉ ይፈልጋችኋል፤ የወያኔ ወዳጆችም ወያኔን ተጠግተው ከኢትዮጵያ የሚያገኙት ጥቅም እንዳይነጥፍባቸው የወያኔን እኩያ ባህሪይና ህገ ወጥ ድርጊት አይተው እንዳላዩ ለማለፍ እናንተን ጥሩ ከለላ አግኝተዋል፡፡ ህዝቡ ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን ምንም የማድረግ አቅም የለውምና በመስዋዕትነቱ እየቀለዳችሁ በደሙ እየነገዳችሁ ስትኖሩ በትዝብት ይመለከታል፡፡ለሁሉም ግዜ አለው በሚለው ሀይማኖታዊ ቃል እየተጽናና ግዜ ይጠብቃል፡፡በፈጣሪ ቸርነት ያች ቀን እውን የሆነች እለት ግን ስለሚሆነው አሁን መተንበይ አይቻልም፡፡አሁንም ግን ቢረፍድም አልመሸምና ግዜውን ተጠቀሙበት፡፡

በመጨረሻ ለጋዜጠኞች በተለይም ለአሜሪካ ደምጽ አማራኛው አገልግሎት፤ ተደራዳሪ የምትሉዋቸውን ሀገር አቀፍ ፓርቲ እያላችሁ መጥራታችሁ ተክክል አይደለም፡፡እስቲ ዝርዝራቸውን አውጡና (ከሌላችሁም ጠይቁ እንሰጣችኋላን) አይታችሁ አረጋግጡ፡፡የሚነገራችሁን ብቻ አየር ላይ ማዋል የእናተንም የራዲዮ ጣቢያችሁንም ደረጃ አይመጥንም፡፡