ከ17 በላይ  ዜጎች አማራ ናችሁ ተብለው በአንድ ቀን ሕይወታቸው ረገፈ #ግርማ_ካሳ

 

October 28, 2017 15:32

ገዢው ፓርቲ ሕወሃት ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀመሮ ላለፉት 26 አመታት የጥቃት ኢላማ ካደረጋቸው መካከል በዋናነት ራሱን አማራ ብሎ የሚጠራዉን ማህበረሰብ አንዱ ሲሆን  ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወጣጣው አማርኛ ተናጋሪ የኢትዮጵያ ብሄረተኛ የሆነው ማህበረሰብ በቀዳሚነት የሚቀመጡ ናቸው። እነዚህን ማህበረሰባት ለማዳከም፣ ከጎንደር የሰሊጥ አገር የሆነችዋን ወልቃይት ጠገዴን ወስዶ ወደ ትግራይ ሕወሃት የጠቀለለ ሲሆን፣ የጎጃምን ግማሽ፣ የተወሰነ መሬትም ከወለጋ በመቁረስ፣ በበላይነት የሚቆጣጠረውን የቤኔሻንጉል ጉምዝ አዲስ ክልል ሸንሽኖ አውጥቷል። በአሁኑ ጊዜ የቤኔሻንጉል ክልልን በተዘዋዋሪ የሚቆጣጠረው ህወሃት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
ይህ ሕወሃት በበላይ በሚቆጣጠረው የቤኔሻንጉል ክልል፣ በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ የሚኖሩ ወገኖች፣  አማራ ናችሁ በሚል እንደተገደሉ፣ እንደተፈናቀሉ በስፋት ተዘግቧል። በኢሊባቡር አማራ ተብለው በገጀራ አንገቶቻቸው የቀሉ ወገኖች ደማቸው ገና ሳይደርቅ፣ አንድ ሳምንት ሳይሞላው፣ ቢያንስ አሥራ ሰባት የሚሆኑ ወገኖች አማራ ናችሁ ተብለው በቤኔሻንጉል ክልል፣ ከማሽ ዞን፣ በሎጅጋንፎይ ወረዳ በክልሉ የልዩ ሃይልና አክራሪዎች በግፍ መገደላቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች በስፋት እየወጡ ነው። የሟቾች ቁጠር ከአምሳ በላይ እንደሆነም አንዳንድ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ከአካባቢው ሰዎች በተገኘው መረጃ መሰረት፣ ዜጎች የተገደሉት በገጀራ፣ በቀስትና በቃጠሎ ሲሆን ከአራት መቶ በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል።ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ የቆሰሉ ሲሆን፣ ከቆሰሉት መካከል ሕጻናት ይገኙበታል። ከሶስት እስከ አራት አመት የሚሆኑ ሕጻናት ሳይቀሩ በጩቤ ምወጋታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ወደ አካባቢው የደረሰ ቢሆንም የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ኖኖ ከእኛ አቅም በላይ አልሆነም እያለ መጀመሪያ ላይ እንዲመለሱ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ግን ነገሮች የፌዴራል ፖሊስ ነገሮች ለማረጋጋት ሞክሯል። ሆኖም የፌደኤራል ፖሊስም ገብቶ ማረጋጋትና ዜጎች መጠበቅ እንዳልቻለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የብራና ራዲዮ አዘጋጅ ሙሉቀን ተስፋው እንደዘገበው፣  ከአንድ ቦታ ብቻ አሥራ ሰባት አስክሬኖች ተነስተዋል። ከሜዳ ላይ 7፣ ዉሃ ውስጥ የተጨመሩ 2 ፣ ጉድጓድ ውስጥ ተጥለው የነበሩ 3 ፤ ከጥሻ ውስጥ ደግሞ 5 አስከሬኖች ተለቅሟል። እንደ ሙሉቀን ዘገባ አንድ ሰው ብቻ ምነችል ሙሉ፣ ይቻላል ወርቄ፣ ዘላለም ይከበር፣ አትርሳው ቻሌ፣ ጌታቸው እንይ፣ አንዱአለምና አልማው ይባሉ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎችን አስክሬን ለቅሟል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የአማራው ክልል ሆነ የቤኔሻንጉል ክልል መንግስት ምንም አይነት አስተያየት እስከአሁን ያልሰጡ ሲሆን፣ ነዋሪዎች በትልቅ ፍርሃትና ስጋት ውስጥ እንዳሉም ለማረጋገጥ ተችሏል።