የሙስና ክስ በተመሠረተባቸው ባለሀብቶች ላይ የቀረበው ንብረት አስተዳዳሪ ይሾም አቤቱታ ተቀባይነት አጣ

29 October 2017

ታምሩ ጽጌ

ዓቃቤ ሕግና መርማሪ ቡድን በጋራ እንዲቆጣጠሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል

በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙና በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ባለሀብቶች ንብረትና ተንቀሳቃሽ የባንክ ሒሳብ ታግዶ ንብረት አስተዳዳሪ እንዲሾም፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አጣ፡፡ አቤቱታውን የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት የንብረት ዕግዱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ አስተዳዳሪ እንዲሾም የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን በሰጠው 14 ገጽ ውሳኔ አሳውቋል፡፡

ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቻቸው፣ እንዲሁም የባንክ ሒሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ ዕግድ እንዲጣልለትና ንብረት አስተዳዳሪ እንዲሾምለት መርማሪ ቡድኑ ጠይቆ የነበረው በገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ በየማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ፣ በአሰር ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ በዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ ስህን ጎበና፣ መሠረት ዓለሙ፣ አብዶ መሐመድ፣ እውነቱ ታዬና ስንዱ ታደሰ በሚባሉ ባለሀብቶች ላይ ነበር፡፡

ዕግድ የተጣለባቸው ባለሀብቶች ከሚያገኙት ገቢ በላይ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ  ክምችት እንዳላቸው በመርማሪ ቡድኑ የተገለጹት የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች ምንም ዓይነት የሒሳብ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻላቸውን፣ የሠራተኞች ደመወዝ መክፈል አለመቻላቸውን፣ ቤተሰቦቻቸው የሚተዳደሩበት የቀለብ መሸመቻ እንደሌላቸው በመግለጽ በተለይ ተንቀሳቃሽ ሒሳባቸው ሊታገድ እንደማይገባ ጠቁመው መቃወሚያ አቅርበው ነበር፡፡ በተለይ ድርጅቶቹ ተንቀሳቃሽ ንብረት ታግዶ የሚዘልቅ ከሆነ ሊተካ የማይችል ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችልና እየደረሰም እንደሚገኝም በማመልከት፣ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው በመቃወሚያቸው አመልክተው ነበር፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩት ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ የማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ፣ አሰር ኮንስትራክሽንና ዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ከመንግሥት ተቋማት ጋር ውል ፈጽመው የተረከቧቸውና በመገንባት ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማስቀጠል ባለመቻላቸው ጉዳቱ የድርጅቶቹ ብቻ ሳይሆን፣ የአገርም ጭምር መሆኑን በመጠቆም የባንክ ሒሳባቸው እንዲለቀቅላቸውም አመልክተው ነበር፡፡

ሌላው ድርጅቶቹ ያቀረቡት መቃወሚያ፣ አስተዳዳሪ እንዲሾም መርማሪ ቡድኑ ያቀረበውን አቤቱታ ነው፡፡ ንብረቶቹን ያፈሩት ‹‹ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራት›› ወንጀል መሆኑን የሚገልጽ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በመሆኑና ሕግ ወደኋላ ተመልሶ ሊሠራ እንደማይችል ሲሆን፣ ቋሚ ንብረቶች እንዳይሸጡና እንዳይለወጡ ዕግድ መጣል የሚቻል መሆኑን በማስረዳት አስተዳዳሪ ሊሾም እንደማይገባም ተከራክረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ግን በሰጠው የመቃወሚያ መቃወሚ ሐሳብ እንዳስረዳው፣ ድርጅቶቹ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ያደረሱት ጉዳት በድምሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመሆኑ፣ ለጉዳቱ ማካካሻ የሚሆን ንብረት አሳግዷል፡፡ ንብረት አስተዳዳሪ ሲሾም የሠራተኛ ደመወዝ ክፍያና የፕሮጀክቶች ቀጣይነት እንደሚረጋገጥ በማስረዳት፣ ድርጅቶቹ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ አቤቱታው ላይ ውሳኔ እንዲሰጥለት ተከራክሮ ነበር፡፡

ድርጅቶቹም ሆኑ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የገቢና ወጪ ዝርዝር፣ እንዲሁም ዕግድ የተጣለባቸውን ንብረቶች ዝርዝር ያቀረቡና ቢሮውም ታገዱ ያላቸውን ንብረቶች ዝርዝርና ግምታቸውን ያቀረበ ቢሆንም፣ በምን ሁኔታና አግባብ እንዳቀረበ የወንጀል ምርመራ ቢሮው ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ማስረጃ እንደሌለ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎቹ ንብረቶችና የባንክ ሒሳቦች ላይ የተጣለው ዕግድ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም? ባለቤቶቹ በንብረቶቹ የመጠቀም መብት ውስንና የባንክ ሒሳቦች ላይ የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተከትሎ የሚነሱ የሦስተኛ ወገን መብቶችና የድርጅቶቹ ህልውናና አጠቃላይ እንቅስቃሴ በምን አግባብ ይመራ? ንብረት ጠባቂስ ሊሾም ይገባል ወይስ አይገባም? ሊሾም ይገባል ከተባለስ ለምንና እንዴት? የሚሉ ጭብጦችን በመያዝ ክርክሩን መመርመሩን በውሳኔው አሳውቋል፡፡

በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 8(1) እና 9(1) መሠረት ተከሳሽ በሙስና ወንጀል ያገኘው የማይገባ ጥቅም፣ ወይም የደረሰ ጉዳት ለመድረሱ በመሃላ የተደገፈ አቤቱታ ከቀረበ ተጣርቶ ሊታገድ እንደሚችል በመደንገጉ፣ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 882/07 አንቀጽ 9(1) መሠረት በተጠርጣሪው የትዳር ጓደኛና 18 ዓመት በሆኑ ልጆች ስም የተመዘገበ ንብረትና የተቀመጠ ገንዘብ ካለ ዕግድ እንደሚጣልበት ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውሷል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ ያቀረበውን ንብረትና የባንክ ሒሳብ ይታገድልኝ አቤቱታ ተቀብሎ ዕግድ መጣሉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ንብረቶቹና የባንክ ሒሳቦች እንዲታገዱ የተደረገው ተጠርጣሪዎቹ በተመሠረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ፣ በፈጸሙት ወንጀል ምክንያት ያገኙት ጥቅምና ያደረሱት ጉዳትን ለማካካስ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ሕጉ ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልግ የዕግድ ትዕዛዝ መስጠት እንደሚቻል የደነገገ ቢሆንም፣ ምርመራ ከተጀመረበት የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት አለ ወይስ የለም የሚለው ማስረጃ የሚመዝነው በመደበኛ ችሎት በሚደረግ ምርመራ መሆኑን፣ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡ የተሰጠው ዕግድም ሊነሳም ሆነ ሊሻሻል የሚችለው በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 16(3) መሠረት መሆኑን ጠቁሞ፣ በተመሠረተው ክስ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ባልታወቀበት ሁኔታ ዕግዱን ማንሳት የሕጉ ዓላማን የሚያሳካ ነው ተብሎ ስለማይታመን፣ ‹‹ዕግዱ ይነሳልን›› የሚለውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

ዕግድ የሚሰጥበት ንብረት በወንጀል ተገኘ ከተባለው የማይገባ ጥቅም ወይም ደረሰ ከተባለው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 9 እና አዋጅ ቁጥር 882/07 አንቀጽ 9 ሥር መደንገጉን ፍርድ ቤቱ ጠቁሞ፣ ተጠርጣሪ ወገኖችና የወንጀል ምርመራ ቡድኑ የየራሳቸውን መከራከሪያ ሐሳብ ያስረዱ ቢሆንም፣ ንብረቶቹ የወንጀል ፍሬ መሆን አለመሆናቸውን ወይም ተጠርጣሪዎቹ ጥቅም ብቻ ነው ያገኙት ወይስ ጉዳትም አድርሰዋል የሚለውን ዕልባት መስጠት ያለበት መደበኛ ችሎት መሆኑን፣ የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በውሳኔው አስረድቷል፡፡

በባንክ ሒሳቦቹ ላይ የተሰጠውን ዕግድ ተከትሎ በሦስተኛ ወገን መብቶች፣ ድርጅቶች ህልውናና የሠራተኛ ደመወዝ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የጠቆመው ፍርድ ቤቱ የባንክ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ ማገድ፣ ክፍያዎች እንዳይሰበሰቡና እንዳይከፈሉ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የዕግዱ ዋነኛ ዓላማ ገንዘቡ ከውሳኔ በፊት እንዳይጠፋ ለማድረግ እንጂ፣ የንግድ ድርጅቶች ሥራቸውን እንዳይሠሩ ለማድረግ ባለመሆኑ ሒሳቦቹን ሙሉ በሙሉ ማገድ ምክንያታዊ አለመሆኑን አብራርቷል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 9(2) እና አዋጅ ቁጥር 882/07 አንቀጽ 9(2 እና 3) መሠረት ተጠርጣሪ በታገደ ንብረቱ የመጠቀም መብቱ እንደማይነካ፣ እንዲሁም የመጠቀም መብት እንደሌለው የተደነገገ ቢሆንም፣ አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ሊጠቀምበት የሚገባን መጠን ወስኖ ሊፈቅድለት እንደሚችልም ችሎቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡ በመሆኑም የድርጅቶቹ የሒሳብ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ማድረግ ከሕግም ሆነ ከፍሬ ነገር አኳያ ተገቢ አለመሆኑንና በድርጅቶቹ ላይ የተጣለው ዕግድ ሊሻሻልና እንቅስቃሴያቸው አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገበት ህልውናቸው ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡

ንብረት አስተዳዳሪ መሾምን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ እንዳብራራው፣ የተጠርጣሪዎች ወኪሎች በችሎት ቀርበው የሥራ መሪነት ሚናቸውን እንደሚወጡና ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስዱ አረጋግጠዋል፡፡ ንብረቶቹ በእነሱ እጅ ቢቆዩ ጉዳት ይደርስባቸዋል ቢባልም፣ ተጠርጣሪዎቹ የንብረቶቹ ባለቤትነታቸው በሕግ እስካልተወሰደ ድረስ የማስተዳደር ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ ጥፋተኛ ናቸው ተብሎ ውሳኔ ከመስጠት በፊት ነፃ ሆነው የመገመት መብት ያላቸው በመሆኑ፣ ንብረቶቹ በእጃቸው ቢቆዩ ጉዳት ይደርስባቸዋል ተብሎ እንደማይታሰብ ገልጿል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 13 እና 17 እስከ 21 ያሉት ድንጋጌዎች መሠረት ጥናትና ማጣራት ሳይደረግ አዲስ ንብረት ጠባቂ መሾም ተገቢ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ ድርጅቶቹና የሚያንቀሳቅሱዋቸው ሠራተኞች ብዛት ያላቸው ከመሆናቸው አንፃር፣ አዲስ አስተዳዳሪ ከመሾም ይልቅ ባሉበት ቢቀጥሉና ድርጅቶቹ አመራሮች ኃላፊነት እንዲወስዱ ማድረጉ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ የሚረዳ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዳመነበትም በውሳኔው ገልጿል፡፡ የድርጅቶቹ የሥራ እንቅስቃሴ እየታየ በሒደት ትዕዛዝ የሚሰጥበት በመሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ ወይም ዓቃቤ ሕጉ ንብረቱን ከጉዳት ለመከላከል አስተዳዳሪ ይሾምልን በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበለው ገልጾ፣ መርማሪ ቡድኑ ወይም ዓቃቤ ሕግ በጋራ በድርጅቶቹ የሚከናወኑ ገቢና ወጪዎችን ንብረቱን ከጉዳት ለመከላከል በሚጠቅም መንገድ እንዲቆጣጠሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

Source    –   Reporter