October 29, 2017 19:16

ታላቋ ቺካጎ የመኢአድ እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመናብርትን የፊታችን እሁድ ኖቬበር አምስት ቀን ታስተናግዳለች። ትግሉ ያለው አገር ቤት ነው። ፓርቲዎቹ ፡

– አንደኛ በጋራና በትብብር እየሰሩ ነው። በቅርቡም ይዋሃዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡

– ሁለተኛ የነበረባቸውን ችግር በመፍታት አዲስ አመራሮችን በማምጣት ድርጅታዊ ጥንካሪያቸው ላይ እየሰሩ ነው። በቅርቡ ከአዲስ አበባ ወደ ክልል በመሸጋገር፣ በአዳማ አዲስ ጽ/ቢት የከፈቱ ሲሆን፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በአዋሳና በጎንደር በቅርቡ ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

– ሶስተኛ ህዝቡን ለመድረስ ጋዜጦችን በማተም ትልቅ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መስራት ጀመረዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ሁለት እተሞችን የታተሙ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ከነገረ ኢትዮጵያ ጋር የመኢአድ “አንድነት” ተብላ ትታወቅ የነበረችውም ጋዜጣ መታተም ትጀምራለች።

– አራተኛ ፓርቲዎቹ በከባድ ሁኔታም ቢሆኑም አገዛዙ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ ራሱን ካዋረደበት ምርጫ ጀመሮ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሕዝባዊ ስብሰባ የፊታችን እሁድ ኦክቶበር 30 ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው። እንግዲህ ሕዝብጋር ወርዶ ከህዝብ ጋር ከመመካከር የበለጠ ትልቅ ሥራ የለም።

– አምስተኛ የድርጅቱ መሪዎች በዉጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያዉያንን ለማስተባበርና የዲፕሎማሲ ሥራ ለመስራት በዉጭ አገር ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ነው። መሪዎች በዉጭ ቢሆኑም የድርጅቶቹ አመራሮች በአንድ ሰው ላይ ላይ ተመሰረቱ ስላልሆነ፣ በተቋም ላይ የተመሰረተ አመራር ስለሆነ ያላቸው፣ የአገር ቤቱ ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።

ወገኖች፣ ፓርቲዎች በከባድ ሁኔታ ዉስጥ ሆነው የተቻላቸውን እያደረጉ ነው። ሆኖም በስፋት ህዝብን ለማንቀሳቀስና አገዛዙን ተክቶ ለዉጥ ለማምጣት የሚችል ድርጅታዊ አቅም ገና የላቸዉም። ያ አቅም የሚኖራቸው በዋናነት በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም የተማረው ሃይል፣ የጎደለ ካለ እንዲሞላ፣ የተበላሸ ካለ እንዲስተካከል፣ ያልተሰራ ካለ እንዲሰራ የድርሻዉን ይወጣ ዘንድ፣ ለነዚህ ድርጅቶች ድጋፉን ሲሰጥ ነው፡፤ አብዛኛው ከዳር ሆኖ በተቀመጠበት፣ ትቂቶች ብቻ በራሳቸው ለዉጥ አያመጡም። የድርጅቶቹ መሪዎች ሁሉንም ነገር ለብቻቸው ሊያደረጉ አይችሉም። አገራዊ እንቅስቃሴ፣ አገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም ዜጋ መንቀሳቀስ አለበት።

በአገራችን በብሄር ላይ ያተኮሩ እንቅስቃሴዎች እያየን ነው። የአማራ ተጋድሎ፣ የኦሮሞ ተቃዉሞ ….ሆኖም ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ ሊያሰባስብ የሚችል የአንድነት የለዉጥ ሃይል ግን ቀዝቅዞ ያለበት ሁኔታ ነው የነበረው። ያንን ለመለወጥ ነው መኢአድ እና ሰማያዊ እየሰሩ ያሉት። መኢአድ እና የሰማያዊ ፓርቲ ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን ክፍት ናቸው።፡አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ሶማሌ፣ ትግሬ… .፣ ሙስሊም፣ ክርስቲያን የዋቆ ተከታይ ብሎ ነገር የለም። የመኢአድ እና የሰማያዊ ቤት የኢትዮጵያዉያን ሁሉ ቤት ነው።

ቺካጎና አካባቢው ያለን ኢትዮጵያዉያ ን በስብሰባው ተገኝተን ከነዚህ ለአገርና ለሕዝብ ሲሉ እየታገሉ ካሉ ወገኖች ጋር አብረን መስራት የምንችልበትን ሁኔታ እንመካከር።

አንርሳ አገራችን የሰማያዊ/መኢአድ መሪዎች ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ናት።