ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ሃሮ ዴዴሳ ቀበሌ የተቀሰቀሰውና ለሕይወት መጥፋት እንዲሁም ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነው ግጭት ግላዊ ጠብ የጫረው ነው ቢባልም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ግን ማንነታቸው ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ይናገራሉ።

በተለያዩ ጊዜያት ከምዕራብ ጎጃም ዞን ለስራ ወደአካባቢው አቅንተው ኑሯቸውን በመሰረቱ የአማራ ተወላጆች እና በጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ውጥረቶች እና ግጭቶች አዲስ ያለመሆናቸውን የሚያስረዱት የጥቃቱ ሰለባዎች ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸውን ይገልፃሉ፤ ከሟቾቹ መካከል የኦሮሞ ተወላጆችም ይገኙበታል ተብሏል።

በግጭቱ ማግስት የአማራ ክልል የብዙኃን መገናኛ ድርጅት የቤኒሻንጉል ክልል የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ መንግስቱ ቴሶን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ ክስተቱን ወደግል ጠብ ዝቅ አድርጎት እንደነበር ይታወሳል።

1997 .ም ከከሰላ አካባቢ ስራ ፍለጋ ወደስፍራው ካቀና በኋላ ኑሮውን በቀበሌው ደናባ ጎጥ የመሰረተው የ36 ዓመቱ ባይህ ታፈረ በግጭቱ የተገደሉ ሰባት ሰዎችን አስከሬን መመልከቱን ይናገራል፤ ሟቾቹ ስድስቱ የአማራ አንዱ ደግሞ የጉሙዝ ተወላጆች ናቸው ይላል።

ባይህ በደረሰባቸው ድብደባ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የገጠማቸውን የስምንት እና የአስራ አንድ ዓመት ልጆቹን በነቀምት አጠቃላይ ሆስፒታል በማስታመም ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደአገራችሁ እንመልሳችኋለንየሚል ዛቻ ከአገሬው ሰው ጎልቶ ይሰማ ነበር ይላል።

ይህ መንፈስም ከሌሎች ቦታዎች የመጡ ናቸው የተባሉ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲነጣጠር ምክንያት ሆኗል ሲል ያምናል።

በየጠላ ቤቱ፣ በየአረቄ ቤቱ ብናባርራችሁ መንግስት መለሳችሁ፤ አሁንም ግን ዋጋችሁን እንሰጣችኋለን ይሉናልሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፤ መንግስት መሳሪያችን ቢነጥቀንም ቀስትና ጩቤ አለን ሁሉ እንባላለን።ይላል ባይህ

የቤኒሻንጉል ክልል በሕገ መንግስቱ መሰረት ነባር ሕዝቦችናቸው በሚል ዕውቅና የሰጣቸው ለበርታ፣ ጉሙዝ፣ሽናሻ፣ ማዖ እና ኮሞ ብሔሮች ሲሆን መጤናቸው ከሚባሉ የሌላ ብሔር ተወላጅ ሕዝቦች ጋር ግጭቶች ሲፈጠሩ አሁን የመጀመሪያው አይደለም።

2006 .ም በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጥቃትን በመሸሽ ከአካባቢው ተፈናቅለው በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም አካባቢ ሰፍረው የቆዩ ሲሆን፤ ቆይቶም ወደክልሉ እንዲመለሱ መደረጋቸው ይታወሳል።

የቤኒሻንጉል ክልል የኮሚኒኬሽን ጽሐፈት ቤት ኃላፊው አቶ መንግስቱ የተከሰተው ግጭት የብሔር መልክ የለውም ይበሉ እንጅ፤ የሃሮ ደዴሳ ገብርዔል ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቄስ እንኳሆነ ቸሬ ምንም በማናውቀው ጉዳይ መደብደባችን ወገን ናችሁ ቢባል ነው እንጅበማለት

ለቢቢሲ ተናግረዋል።