የቀድሞው የኢትዮጵያ ወታደራዊ መሪ ረዳት ነበር የተባለው ግለሰብ የጦር ወንጀል የፍርድ ሂደት በኔዘርላንድስ ሄግ መታየት ጀመረ።

63 ዓመት ዕድሜ ያለው አቶ እሸቱ አለሙ የተባለው ግለሰብ ወታደራዊው መንግሥት ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተቀናቃኞቹን ለመምታት ባካሄደው የቀይ ሽብርዘመቻ ወቅት 75 ሰዎች እነዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል ተብሎ ነው የተከሰሰው።

የቀድሞው ኮሚኒስት መሪ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ረዳት ነበር የተባለው ይህ ግለሰብ በሰዎች ላይ ሰቆቃን በመፈፀምና በከፋ አያያዝ ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ጭምር ተከሷል። ነገር ግን የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ እንዳልፈፀመ ተናግሯል።

በቀረቡበት አራት የጦር ወንጀሎች ከ300 የሚበልጡ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስም ዝርዝርም ቀርቧል።

ኢትዮጵያ ውስጥም በሌለበት በቀረበበት ክስ ሞት ተፈርዶበታል።

አቃቤ ሕግ እንደሚለው ኢትዮጵያዊና የደች ጥምር ዜግነት ያለው አቶ አለሙ ጎጃም ክፍለ ሃገር ውስጥ የመንግሥቱ ኃይለማሪያም ቀንደኛ ደጋፊ በመሆን አገልግሏል።

በኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደቱ ሲከፈት አቶ እሸቱ አለሙ አቃቤ ሕግ የተሳሳተ ሰው ላይ ነው ክስ የመሰረተውሲል ተናግሯል።

አቃቤ ሕግ አደረግከው ብሎ ያቀረበውን ክስ ስሰማ በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ የቀረቡብኝን ክሶች በሙሉ አልፈፀምኩምበማለት ነበር ጉዳዩን ለሚመለከቱት አራት ዳኞ የተናገረው።

አቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ እንዳለው አቶ አለሙ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ 75 የሚሆኑ እስረኞች እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።የሟቾቹም አስከሬን በአንድ የጅምላ መቃብር ውስጥ እንዲቀበር አድርጓል ይላል ።

በተጨማሪም አቶ አለሙ ሰላማዊ ሰዎችን እና ትጥቅ የፈቱ ተዋጊዎችን ያለፍርድ እንዲታሰሩና በጭካኔ አያያዝ ስር እንዲቆዩ አድርጓልየሚል ክስ ቀርቦበታል።

በክሱ እስረኞች እጅና እግራቸው ታስሮ እንዲንጠለጠሉ በማድረግ የውስጥ እግራቸው በዱላ እንዲገረፉ አድረጓልም ተብሏል።

በዚህ የፍርድ ሂደትም የሰቆቃው ሰለባዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች በምስክርነት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።