October 31, 2017 22:59

ይድረስ ለተስፋዬ ደምመላሽ!

 

ይድረስ ለተስፋዬ ደምመላሽ!                                                «የሚስቅልህ ቀባሪህ፣ የሚስቅብህ መካሪህ»                                                                   ከተክሌ የሻው
«የሚስቅልህ ቀባሪህ፣ የሚስቅብህ መካሪህ»

ከተክሌ የሻው

ተስፋዬ ደምመላሽ በሚል ስም «የአ[ዐ]ማራው ህ[ኅ]ልውና ትግል ወርድና ሳፋት» በሚል ርዕስ የጻፉትን አነበብኩ። ጽሑፉን ካነበብኩ በኋላ ምን መልዕክት ሊያስተላልፉ ፈልገውነው ብየ ደጋግሜ አነበብኩት። የጽሔፋቸው ጭብጥ ለእኔ እንደገባኝ፣ ዐማራው እንደሰው የመኖር ችግር ገጥሞታል፣ በሕይዎት የመሮር ፣በመረጠው አካባቢ፣ ባሻው የሥራ መስክ፣ እንደሰው ራሱን የመተካት(የመዋለድ) ውስብስብ ችግሮች ገጥመውታል። የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሰለባ ሆኗል። በማንነቱ እንዲሸማቀቅና እንዲያፍር እየተደረገ ነው። ዐማራውን ከቻሉ ማጥፋት ፣ካልቻሉ ቁጥሩን አናሳ በማድረግ አንገት ደፊና ተዋራጅ እንዲሆን እየተደረገ ነው ብለው፣ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ተነስተው ይህ እንዳይሆን፣ ባመኑበትና በመሰላቸው መንገድ  ድምፅ የሚያሰሙ ፣ ድምፅ አልባ ለሆነው ዐማራ ድምፅ በመሆን በሚችሉት መንገድ የሚፍጨረጨሩ ግለሰቦችና ስብስቦችን ጥረት ለማጣጣል፣ ለማጥቃት፣ ሥራዎቻቸውን ጥላሸት ለመቀባት እና  ዐማራው አሁንም ታፍኖ ድምፁ እንዳይሰማና ጠላቶቹ እስካሁን ያደረጉት ሁሉ ያላዳች ሀግ ባይ እንዲቀጥልና በተለመደው «ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ስም» ዐማራው ያላንዳች ተከላካይ ጥፋቱን በሌለ «አንድነትና ተዋልደናል» ስም አምኖ እንዲቀበል የቀረበ ፣ ዝምበሉ ዐማራው መጥፋት አለበት፤ይህንም በፀጋ ተቀበሉ ዓይነት ሆኖ አገኝቸዋለሁ።
ተስፋዬ ደምመላሽ ከሀሳብ አደራደራቸው መገንዘብ እንደሚቻለው በትምህርቱ ዘርፍ የገፉ ይመስላል። እናም የዐማራው ኅልውና አደጋ ላይ ነው፤ ዐማራው ተደራጅቶ ኅልውናውን ያስጠብቅ እያሉ የሚጮኹ ወገኖችን የሰላ ነቀፋ ብቻ ሳይሆን፣ ልክ መለስ ዜናዊ በ1997 ዓም ለመብታቸውና ለነፃነታቸው ድምፃቸውን ለማሰማት ጎዳና ላይ የወጡትን ሰላማዊ ሰልፈኞች የተጠቀመበትን ቃላ በቀጥታ በመጠቀም «ነውጠኞች» በማለት ለማሸማቀቅ ሞክረዋል። ተስፋዬ ደምመላሽ ቀጥታ  ያሉትም እንዲህ ነው። «አማራ አክቲቪስቶችና ነውጠኞች» በማለት  የመለስ ዜናዊ አንደበት ሆኖ ቀርበዋል። እኔ ግን ይህን አባባል የማየው አባቶቻችን እንደሚሉት «የሚስቅልህ ቀባሪህ፣ የሚስቅብህ መካሪህ» በሚለው አተያይ ስለሆነ ስድብና ነቀፌታውን በፀጋ እቀበለዋለሁ። ዐማራው የዘር ጥፋት እየተፈጸመበት ነው። ከዘር ጥፋት እንዲድንም ራሱን ማደራጀት አለበት ብለን ከልብ የምናምን ሰዎችና ስብስቦች ራሳችን እንድናይ፣ ሌሎች ስለ እኛ ምን አደንደሚሉና እያሉም እንዳሉ ለማወቅ ስለሚረዳን ነቀፌታውን፣ ስድቡንና ስም ማጥፋቱን የምንመለከተው ከዓይናችን ሥር ያሉ ጉድፎችን እንድናይ በሚረዳን መልኩ ነው።
ተስፋዬ ደምመላሽ የዐማራው ኅልውናው አደጋ ላይ ነው፤ ራሱን አደራጅቶ ከጥፋት ይታደግ የሚሉ ወገኖችን በስሕተት መንገድ የተረጎሟቸውን ጉዳዮች አንድ ባንድ ከመተቸቴ በፊት፣ እንደ ተስፋዬ ደምመላሽ ያሉ ሰዎች ለትችና ለማፍረስ ከመነሳታቸው በፊት ገንቢ ፣ አሰባሳቢና እንዲህ ቢሆን፣ በዚህ በዚህ ምክንያቶች ይህ ቢሆን ይሻላል በማለት የማሳወቅና የማስተማር ሥራ ላይ  ቢያተኩሩ የተሻለ ይሆን ነበር። ተስፋዬ ደምመላሽ እርግጠኛ ነኝ ከኢትዮጵያ ከወጡ ቆይተዋል። የአገሪቱን ታሪክና ባለፉት 43 ዓመታት የተከናወኑትን ሁለንተናዊ ለውጦች በሚገባ ያውቋቸዋል ለማለት አልደፍርም። የኢትዮጵያዊነት አያያዥ ዕሴቶች ምን እንደሆኑና እነዚያ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ከምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚያስረዳን የታሪክ፣ የፖለቲካል ሣይንስና የመሰል የዕውቀት ዘርፎች ሊቅ(ምሑር) የለም። የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ባህል፣ የሥልጣን አወጣጥና አጠባበቅ፣ የነገዶቹ አንድነትና ልዩነቶች፣ ኢትዮጵያ ከዘመነ ቅኛ አገዛዝ ራሷን ጠብቃ ለመቆየት ያስቻሏትን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ባሕላዊ የጋራ ዕሴቶች ምን እንደሆኑ ብትንትን አድርገው ያስተማሩን ኢትዮጵያዊ ሊቆቻችን እምብዛም ናቸው። የተስፋዬ ደምመላሽ ዓይነት ሰዎች በዚህ ዘርፍ ምን ያህል ሥራ እንደሠሩ የሚያውቁት ራሳቸው ናቸው። በጥቅሉ ተስፋዬ ደምመላሽ እና እርሳቸውን የመሰሉ ሰዎች የዐማራው ኅልውናን ጥያቄ አንስተው ከጥፋት እንታደግ የሚሉ ወገኖችን ከማብጠልጠል፣ ዕውነት እንደሚባለው ዐማራው የዘር ጥቃት እየተፈጸመበት ነው? ዐማራው በእርግጥ ኅልውናው አደጋ ላይ ነው? ከሆነስ ራሱን መከላከል የሚችለው እንዴት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ ተገቢ የመፍትሔ አቅጣጫ ማመላከት የምሑራን ተግባር ነበር። ይህን ሳይሠሩና ሙያዊና ዜግነታዊ ግዴታዎችን ሳይወጡ በዕቅድና በጥናት ቀርቶ፣ በደመነፍስ ዘራችን ሊጠፋ አይገባውም የሚሉ ወገኖችን ተግባር ለማጣጣልና ለመወንጀል አመልካችን እጣትን በሌሎች መቀሰር፣ ሦስቱ እጣቶች ወደ ራስ የሚቀሰሩ መሆኑን አለመገንዘብ ነው።
ለጽሑፌ መንደርደሪያ ይህን ካልኩ ፣ተስፋዬ ደምመላሽ ላነሷቸው ጉዳዮች ያለኝን የግል አስተያየቴን ላስረዳ። ተስፋዬ እንዲህ ይላሉ፦
1 « አክለው እንደሚሉት አጣዳፊው የአ[ዐ]ማራ ህ[ኅ]ልውና ትግል ቀደምትነት በሌሎች “ሁለተኛ ደረጃ“ የተቃውሞ ጥረቶች (ለምሳሌ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ ዙሪያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች) እና ጥረቶች አጃቢ በሆኑ ሌሎች ፖለቲካዊ “ቅንጦቶች“ መስተጓጎል የለበትም። አ(ዐ)ማራው “በመጀመሪያ ዙር“ለብቻው ራሱን የማዳን ትግል አድርጎ «ካሸነፈ በኋላ“ ነው ከሌሎች የአገሪቱ ማህ(ኅ)በረሰቦች ጋር በኢትዮጵያዊነት የሚተባበረው።»
በመጀመሪያ ደረጃ ተስፋዬ ደምመላሽ ከላይ የሠፈሩትን ሀሳቦች ከማንኛው የዐማራ ኅልውና ትግል አቀንቃኝ ፕሮግራም ወይም ሰነድ ወይም ተናጋሪ እንዳገኙ ስለማይገልጽ እንዲህ ነው ብሎ ልብን ሞልቶ ለመናገር ያስቸግራል። በእርግጠኝነት ግን እርሳቸው ባሉት ከላይ በሰፈረው መልክ ያሉ የዐማራ አክቲቪስቶችም ሆኑ ድርጅቶች አሉ ብየ ለመቀበል እቸገራለሁ። የዐማራው ነገድ አክቲቪስቶች፣ ስብስቦችና ድርጅቶች በሁለት የተከፈሉ ናቸው። አንዱ ዐማራው ተገንጥሎ «የዐማራው አባት አገር እንመሥርት » የሚለው ነው። ይህ ቡድን የራሱ የሆኑ መከራከሪያ ነጥቦች አሉት። ትክክል ነው ፣ ትክልል አይደለም ለማለት ሁለቱ ወገኖች ግራና ቀኝ ቆመው በሚያቀርቡት መረጃ ላይ በመመሠረት በሚሰጥ ውሳኔ የሚለይ ነው። ሁለተኛው ወገን፣ ዐማራው ተለይቶ፣ በፕሮግራም ተቀርፆ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመበት ነው። ከዚህ ጥፋት ለመዳን ዐማራው በማንነቱ ዙሪያ ተደራጅቶ በዘሩ ምክንያት ከሚፈጸምበት ጥቃት ይከላከል። ራሱ ኃይል ሆኖ ሲወጣ የሚጠሉት ይወዱታል፣ የናቁት ያከብሩታል፣ ይህም ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ላይ በመመሥረት ከሌሎች በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ ነገድና ጎሳ ድርጅቶችና ስብስቦች በዕኩለት ላይ በተመሠረተ አሠራር የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንወስናለን የሚለውና የዐማራው አገር ታላቋ ኢትዮጵያ ናት የሚለው ነው።  የእኔ ሀሳብ የሚያጠነጥነው በዚህ ሁለተኛው  የዐማራ ኅልውና ቡድን አቀንቃኝ ዙሪያ ነው። ይህ ቡድን ተስፋዬ እንዳሉት ከዐማራው ኅልውና ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች አይነሱ ብሎ የሚያምን አይደለም። ለሁሉም ነገር ቅደም ተከተል አለው። ይህ ሲባል ግል እያንዳንዱ ነገር በብቸኝነት የቆመ፣ ዲያሌክቲካዊ ግንኙነት የሌለው ነው ማለት አይደለም። በመሆኑም ለዐማራው ኅልውና ስንታገል፣ ለኅልውናው መሠረቱና ዘላቂነቱ በራሱ ውስጥም ሆነ ከሌሎች ጋር ባሉትና ሊኖሩ በሚችሉ ግንኘነቶች ሁሉ የዲሞክራሲን  አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ዘንግተን ወይም ትተን አይደለም። በመጀመሪያ የዐማራው ኅልውና መረጋገጥ በራሱ ውስጥ በሚያሰፍነው የዲሞክራሲ አሠራርና ሂደት የሚወሰን ነው። በመሆኑም ተስፋዬ የዐማራውን ኅልውና አቀንቃኞች የኅልናውን ትግል ከዲሞክራሲ ነጥለው በሁለተኛ ደረጀ ፈርጀውታል የሚለው አባባል ተገቢም ትክክልም አይደለም። እያልን ያለነው ዐማራው የተጋረጠብህን የዘር ጥቃት ለመከላከል በማንነትህ ዙሪያ ተደራጅ ነው።  ሕዝብን ማደራጀትና ዲሞክራሲን ማስፈን ሁለቱም ሂደትን የሚጠይቁ ቢሆንም፣ ከጊዜ አንፃር ማደራጀት ቀዳሚ ነው። ይህን ሲባል ግን ዐማራውን በማደራጀት ሂደት ውስጥ የዲሞክራሲያዊ አሠራር የለም ማለት አይደለም። ዲሞክራሲ ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት ደግሞ በሂደት እንጂ፣ ባንድቀን ጀምበር ዕውን የሚሆን አይደለም። የዐማራው መደራጀትም አንዱ ግቡ ይህ በሂደትና እልክ አስጨራሽ የሆነ ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ መጣር ነው። ዲሞክራሲ ሥርዓት እንደመሆኑ መጠን፣ ከመደራጅት ውጭ የሚታሰብ አይደለም። ለዲሞክራሲ ማበብ የተደራጀ የሕዝብ እንቅስቃሴ የግድ ነው። ድርጅት ሳይኖር፣ ዲሞክራሲን ማሰብ፣«ከባል በፊት ልጅ ይስጥሽ» እንደማለት ነው። እና በዚህ በኩል የቀረበው ትችት ገንቢ አይደለም።  በሌላም በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ከ80 በላይ የሆኑ ነገድና ጎሳዎች ካንድ በላይ የነገድና የጎሳ ድርጅቶች አሏቸው። ኦሮሞው ከ14 በላይ፣ ትግሬው 4፣ ጉራጌው 3፣ አፋሩ 4፣ ወዘተ አላቸው። ዐማራው በማንነቴ ዙሪያ ልደራጅ ሲል ከሁሉም ቀድሞ የዐማራው  «ምሑራን ነን» የሚሉ ወገኖች ለምን ቅር እንደሚሰኙና ለጅማሮዎች መሰናክል ለመሆን እንደሚፈልጉ መጠናት ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል።

በሁለተኛ ደረጃ ከላይ በተስፋዬ የሰፈረው «የገለባ ያፈራል» አባባል ያልተለየው፣ አፍርሽ ትችት አ[ዐ]ማራው “በመጀመሪያ ዙር“ለብቻው ራሱን የማዳን ትግል አድርጎ «ካሸነፈ በኋላ“ ነው ከሌሎች የአገሪቱ ማህ[ኅ]በረሰቦች ጋር በኢትዮጵያዊነት የሚተባበረው።» የሚለው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ማሸነፍ የሚለው ቃል ትርጉም ያሻዋል። ማሸነፍ ስንል ያንዱን የበላይ የሌላውን የበታች ማድረግ ነው? አንዱን ዘር ፈጽሞ ማጥፋት ነው?  የአዱን ፍላጎት  በሌሎች ላይ መጫን ነው? የቱ ነው ማሸነፍ ስንል? እኛ ዐማራው ኅልውናውን ለማስጠበቅ ይደራጅ ስንል፣ ዐማራውን በአሸናፊና በተሸናፊ  ጎራ ለማቆም አይደለም። አሸናፊና ተሸናፊ ካሉ ትግላችን ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ብለን አናምንም። ትግላችን  ሁሉም የሚገባውን ድርሻውን አገኝቶ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር፣ ሁሉም የአሸናፉነት አክሊል ሊቀዳጅበት የሚችልበትን ሁኔታ ዕውን ለማድረግ እንጂ፣ አንዱ አጥቂ ሌላው ተጠቂ፣ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ፣ አንዱ አዛዥ ሌላው ታዛዥ፣ አንዱ ጀግና ሌላው ፈሪ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር አይደለም። በመሆኑም ተስፋዬ ደምመላሽ ከላይ ያሰፈሩት አባባል ዐማራው ኅልውና ይጠበቅ፤ እያልን የምንጮኽ ቡድኖችና ግለሰቦች ዓላማ ፍፁም ተጻራሪ ነው። እንዳውም  ወያኔ ኦሮሞንና ዐማራን እሳትና ጭድ በማድረግ የአገዛዝ ዕድሜየን አራዝማለሁ ብሎ የሰነቀው ሥንቅ፣ እየተሟጠጠ ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ሌሎች እንደተለመደው ዐማራውን በጠላትነት እንዲመለከተቱና የማጥፋት ዘመቻቸውን እንዲያጠናክሩ የሚገፋፋ ነው። አሸናፊና ተሸናፊ የሚለውን ቃል መሰንቀራቸው ወያኔ የሚፈልገው እንዲሆንለት፣ ዐማራው ተነጥሎ መመታቱ እንዲቀጥል የሚያመቻች ሆኖ አገኝቸዋለሁ። የዐማራው መጠንከር ለኢትዮጵያ ጥንካሬ ይሰጣል እንጂ፣ ድከመቷን አያሳይም። ዛሬ አገሪቱ ላለችበት መስቀልኛ መንገድ የዳረጋት የዐማራው ኃይል ሆኖ፣ ለኢትዮጵያዊነት መቀጠል ለሚሹ ወገኖች አለመድረሱ ነው።  ስለሆነም የዐማራው ኅልውና ትግል ራሱን ከጥፋት የመከላከል እንጂ፣ ሌሎችን ማግለል አይደለም።ሌሎችን በተሸናፊነት ለማቆም አይደለም። የበላይና የባታች መሥመር ለማስመርም አይደለም። ዐማራው በራሱ ማንነት ዙሪያ እንዲደራጅ የተፈለገውም ሌሎቹ እርሱን በመግደፍ(በመተው) በራሳቸው ዙሪያ ከመደራጀት አልፈው፣ ጠላታችን ዐማራ ነው በማለታቸውና እርሱን ለማጥፋት ብዙ ርቀት የተጓዙ በመሆኑ ነው። ለራሱ ኅልውና ያልቆመ ለሌሎች ይቆማል ተብሎ አይታሰብምና፣ ዐማራውም ለኢትዮጵያ አንድነት ለማሰብ በቅድሚያ የራሱ ኅልውና መረጋገጥ አለበት። ለዚህ አባባሌ የሚከተሉት ምሳሌዎች  ነቃሾቸ ናቸው።«መጀመሪያ የመቀመጫየን» ዝንጀሮ። «ሀ መጀመሪያ ራስክን  አድን!» የወታደራዊ ሳይንስ መመረያ። «ሌሎችን ለመርዳት ከመሞከረዎ በፊት ራሰዎን ያድኑ» የአየር በረራ መመሪያ።
2 የዐማራው « —-ህ[ኅ]ልውናው ምንጊዜም በኢትዮጵያዊነት የታቀፈና የተደገፈ ነው፤ በአገር ግንባታና እድገት መካከለኛ ሚና ተጫውቷል።» ይህ አባባል ብዙ አከራካሪ ነው። የመጀመሪያው አከራካሪ የሚሆነው« የዐማራው ኅልውና ምንጊዜም በኢትዮጵያዊነት የታቀፈና የተደገፈ ነው» የሚለው ዐረፍተ ነገር ነው። በእኔ አረዳድ፣ ግንዛቤ ወይም አባባሉ የገባኝ በሚከተለው መልኩ ነው።  ለግንዛቤየ መነሻ የሆነው ኃይለ ቃል «ምንጊዜም» የሚለው ነው። የዐማራው ኅልውና ምንጊዜም፣ መቼም ቢሆን ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሊኖር አይችልም። ካለኢትዮጵያ ዐማራ አይኖርም። የዐማራው ኅልውና መሠረቱ ኢትዮጵያ ተብላ የምትታወቅ አገር ናት የሚል ነው። ይህ አባባል በዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚሠራ እንዳልሆነ እያየን ነው። ዐማራው ኢትዮጵያ አገር አይደለችም ተብሎ፣ ከወለጋ፣ ከኢሉባቡር፣ ከሐረርጌ፣ ከከፋ፣ ከሸዋ፣ ከጎጃም(መተከል) ከጎንደር(ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት) ከወሎ (ራያና አዘቦ) መገፍና በግፍ መባረሩን እናውቃለን። ኢትዮጵያ በስም እንኳ እያለች ዐማራው አገርህ አይደለም ተብሎ ተፈናቃይ መሆኑን እያየን «ምንጊዜም» የዐማራው ኅልውናው ኢትዮጵያ ናት የሚለው አባባል ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አይደለም። ዐማራው በማንነቱ ዙሪያ እንዲደራጅና ኅልውናውን እናስጠብቅ ስንል፣ የዐማራው አገር ወያኔ የከለለው አጥር ሳይሆን፣ ሠፊዋ ኢትዮጵያ ስለሆነች፣ በዚያ የመኖር መብቱ እንዲከበር፣ አስከባሪውም ሌላ ማንም ሳይሆን ራሱ በራሱ በአገሩ የመኖር ተፈጥሮአዊ መብትና ጥቅሞቹን እንዲያረጋግጥ ነው።
ከላይ በተገለጸው በተስፋዬ ደምመላሽ በአገር ግንባታና እድገት  ሂደት ውስጥ ዐማራው መካከለኛ ሚና ተጫውቷል የሚለው፣ ዘመነኞቹ የትግሬ ወያኔዎችና የኦሮሞ ብሔርተኞች ከሚሉት የተዛባ አመለካከት የተቀዳ ሆኖ ነው የተሰማኝ። ይህንም እንድል ያሰኘኝ የኢትዮጵያ አገር ግንባታ መቸ ተጀመረ? ማን ጀመረው? እንዴት ተጀመረ የሚሉትን ጥያቄዎች ሳነሳ የማገኛቸው መልሶች ከተባለው የተለየ ሆኖ ስለማገኘው ነው። ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ የራሷ ሕገ-መንግሥት (ፍትሐ-ነገሥት) አዘጋጅታ፣ በራሷ ቋንቋ ፊደል ቀርፃ፣ የራሷ መለያ ሰንደቅ ዓላማ አቁማ ፣በየዘመኑ ከነበሩ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ጋር( ባዛንታይን፣ ሮማውያን፣ ግሪካውያን፣ ፐርሻውያን፣ ግብፃውያን፣ ፖርቹጋላውያን ወዘተ) የንግድና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረተች አገር መሆኗ በግልጽ ይታወቃል። ይህም ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስርና የፀና ፖለቲካዊ ማንነት የገነባች አገር እንድትሆን በማድረጉ፣ በዘመነ ቅኝ አገዛዝ ዘመን፣ ሌሎች የአፍሪካና የእስያ አገሮች በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ሲወድቁ፣ ኢትዮጵያ አልበገር ብላ በነፃነት እንድትቆይ ማስቻሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ባጭሩ ሌሎቹን የሩቆቹን ትተን ከወንድማማቾቹ አብርሃና አጽብሃ ዘመን ጀምረን ወደ ፊት ብንቆጥር የአገር አንድነቱ ግንባታ በአገሪቱ በሚኖሩ ነገዶች የየወቅቱ የነቁ ግለሰቦች ጥረት ውጤት እንጂ፣ የዐማራው ብቻ እንዳልሆነ እንረዳለን። የአጋዛያውያን፣ የአገው፣ የትግሬ፣ የአፋር፣ የኦሮሞ፣  የሀዲያ፣ የከንባታ፣ የዐማራው ወዘተ ነገዶች ቅብብል ውጤት እንጂ፣ የአንድ ነጠላ ነገድ ጥረት ነው ለማለት ያስቸግራል። የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገራዊ ግንባታም ቢሆን፣ ጀማሪው ጎንደሬው ካሣ (ቴዎድሮስ) ይሁኑ እንጂ፣ በቅብብል፣ አገው  ዐፄ ተክለጊዮርጊስ(ጎበዜ ገብረመድኅን)፣ ትግሬው ካሣ ምርጫ (ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ)፣ ሸየው ዳግማዊ ምኒልክ፣ ሸየውና ወሎየው ልጅ ኢያሱ ሚካኤል፤ ወሎየዋና ሸዉዋ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ፣ ሸየው ተፈሪ መኮንን(ቀኃሥ) መሪነት  በተከታታይ ያከናወኑት ነው። የእነዚህ መሪዎች ማንነት ደግሞ የአንድ ነጠላ ነገድ ማንነት የተላበሱ እንዳልሆኑ ይታወቃል። ከበርካታዎቹ ነገድና ጎሳዎች የተወለዱ ናቸው። ባጭሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ይህ ሐቁ ነው።
ተስፋዬ ደምመላሽ «ዐማራው በአገር ግንባታው እድገት መካከለኛ ሚና ተጫውቷል »የሚሉት አባባል፣«ገንፎ ሲምርበት ተንሸራቶ ቅቤ ማሰሮ ውስጥ ይገባል» የሚሉት ዓይነት ነው የሆነብኝ። ምክንያቱም ሌሎቹ እያሉን ያሉት ዐማራው «ቅኝ ገዝቶናል፤ ጭሰኛ አድርጎናል፤ ጨቋኝ ነው፤ ጨቋኝ ብሔረሰብ ነው፤» ለሚሉት ደንጋይ የማቀበል ያህል ሆኖ ተሰምቶኛል። ዐማራው በቁጥሩ ብዛትና በቋንቋው የመንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ከመሆኑ ውጭ ፣ይህ ደግሞ በሌላ በምንም ምክንያት የሆነ ሳይሆን፣ ቋንቋው የራሱ ፊደል ባለቤት ከመሆኑ የተነሳ ለአገልግሎት ራሱን ያቀረበ በመሆኑ ካልሆነ በቀር በሌላ ምክንያት አለመመረጡ ግልጽ ነው። እናም ይህ በሆነበት ሁኔታ ዐማራው ማዕከላዊ የአገር ግንባታ ሚና ተጫውቷል የሚለው ሌሎችን ያገለለ የሚያስመስል ከመሆኑም በላይ፣ የጠላቶቹን ፕሮፓጋንዳ ማራገብ ሆኖ ተሰምቶኛል።ለምሳሌ  የሐረሩ ኢሚር ኑር ዓሊበ1552 ዓም ላይ የገላውዲዎስን ጦር ድል ነስቶና የንጉሡን አንገት ቆርጦ ድል ለማብሰር ወደ ድል ወንበራ በድል መንፈስ ወደ ሐረር ሲገሠግሥ፣  በምችሌ ገዳ የሚመራው ኦሮሞ ተዋጊ ኃይል፣ ደዋሮ ውስጥ ሀዘሎ ከተባለ ቦታ ላይ ደፈጣ በማድረግ፣ የኑር ዓሊን ሠራዊት በመግጠም ድል ማድረጋቸው ይታወቃል። ይህ ድል የሐረር ኢሚሮች በክርስቲያን ንጉሦች ላይ ያነሱት የነበረውን ተከታታይ ጦርነት እስከ ወዲያኛው እንዲያቆም እንዳደረገው ይታወቃል። በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ ድል፣ ከ14ኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በዐምደጽዮንና በይፋት ወላስማዊ ሡልጣኖች መካከል ማለትም በክርስቲያንና እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል እስከ 1540ዎቹ የዘለቀውን የሥልጣንና የሃይማኖት ማስፋፋት ጦርነቶች ፍጻሜ እንዲያገኝ አድርጓል። ይህም ለኢትዮጵያ አንድነት መጠናከርና ወደፊት መግፋት እንዲችል ማድረጉ ይታወቃል። ይህ ደግሞ ካለምችሌ ጦር ድል አድራጊነት ውጪ የሚታሰብ አይደለም። ይህም ኦሮሞዎቹ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ምስረታም ሆነ ሥልጣን አያያዝ የተገፉ ሳይሆኑ ማዕከላዊ  ቦታ የነበራቸው መሆኑ ግልጽ ነው።
3 «–የኢትዮጵያ ነገዶች ማህ[ኅ[በረሰባዊና ባህላዊ ተጽዕኖዎች ተለዋውጠውም በጋራ አብዮታዊ ልምድ የዘር ሳይሆን፣የመደብ ትግል አካሂደውም አገሪቱን በአንድነት እንደለወጡ የምንዘነጋው ነገር አይደለም። የዛሬን የወያኔን ሞገደኛ አገር ከፋፋይና አሰናካይ አገዛዝ አያርገውና በኢትዮጵያ የዘመናት እድገትና ዘመናዊ አብዮታዊ ለውጥ ትስስራቸው፣ አንድነታቸው፣ ይበልጥ እየተጠናከረና እየተሻሻለ በመምጣት ላይ እንደነበር ይታወሳል።» ተስፋዬ ደምመላሽ በዚህ መልክ በሁለት አሳሪ አንቀጾች የቋጩትን ሀሳባቸውን ጭብጥ ለመረዳት ብዙ ማሰብ ይጠይቃል። እንደኔ ያለ ተራ አንባቢ ሊረዳው የሚችል አይመስለኝም። ቁልፍልፍ ቃሎችና ጽንሰ ሀሳቦች የተጋመዱበት ስለሆነ። የመጀመሪያው ማኅበረሰባዊና ባህላዊ ተጽዕኖዎች የምንላቸውን ማፍታታቱና ትርጉም መስጠቱ አስቸጋሪ ይሆናል። ማኅበራሰባዊ ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ የራሱ ትርጉም የሚሻው ነው። ቀጥሎ «–በጋራ አብዮታዊ ልምድም የዘር ሳይሆን፤» የሚለው ትንሽ ግር ያሰኛል። እነዚህ ግርታዎች የአረዳድ ችግር ካልፈጠሩብኝ በቀር ፣ በእኔ እይታ በሀሳቡ የሚከተሉትን ችግሮች አስተውያለሁ።
በተስፋዬ አባባል ባለፉት 40 እና ከዚያም በላይ የተካሄዱት ለውጦች አብዮታዊ እንደሆኑ፤ ለውጡም ሁሉም ነገዶችና ጎሳዎች በአንድነት የተካፈሉበት መሆኑን፣ወያኔ እስከ መጣ ድረስ የኢትዮጵያ የዘመናት እድገት እና ዘመናዊ አብዮታዊ ለውጥ የነገዶቹን ትስስር፣ አንድነታቸውን ይበልጥ እያተጠናከረ እና እያሻሻለ የመጣ እንደነበር በማስረገጥ፣  የዘመነ አብዮት ዓመቶች አዎንታዊ እንደሆኑ ያምናሉ። እንደ እኔ ለዐማራ ኅልውና እንደሚታገሉ ሰዎች እይታ ግን ፣ተስፋዬ «የዘመናዊ አብዮታዊ ለውጥ ትስስራቸው፣ አንድነታቸው ይበልጥ እያጠናከረና እያሻሻለው» ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ አንድነት ምሠሦ የነበሩ የወል ዕሴቶችን፣ የአንድነትና የወል መገለጫ የሆኑ ተቋሞች የተናዱባቸው፣ አገሪቱ ዛሬ ለምትገኝበት እንደአገር ለመቀጠል ወደ ማትችልበት መስቀልኛ መንገድ እንድታመራ ሠፋፊ በሮችን የከፈተ እንደሆነና ለዘረኛው የትግሬ ወያኔ ሥልጣን የማያረገርግ መሰላል የሠራ አድጌነው የምመለከተው። ምክንያቱም አብዮቱ  ማመጽን፣ የነበረውን ማፍረስ፣ ሁሉን ነገር አፍርሶ ከዜሮ መጀመር በሚል ያለፉትን ሁሉ በመጸየፍ በጥቅሉ መናድን መርሕ አድርጎ የተንቀሳቀሰ ስለነበር፣ ጥፋትን እንጂ ልማትን ያላመጣ ለመሆኑ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ ያሳያል። ሁሉም አብዮተኞች «በመርሕ ሥር ነቀል ለውጥ» የሚያምኑ ስለነበር፣ እንዳሉት አብዮቱ የአገሪቱን መሠረታዊ የወል ዕሴቶችና ነባር ተቋሞችን ከሥራቸው አፈለሳቸው። ይህ ሥርነቀል ለውጥ ሕዝቡን በአጠቃላይ ደኃ ከማድረግ አልፎ፣ አገር አልባ በማድረግ ከፊሉን ተሰዳጅ ሲያደርግ፣ ከፊሉን ደግሞ በአገሩ ሠርቶ የመኖር መብቱን ከመገፈፍ አልፎ የዘመንተኞቹና«የወርቆቹ» ልጆች የበይ ተመልካች አድርጎታል።
ሌላው የአብዮታውያኑ እምነት የተመሠረተው የመደብ ጠላትን ማጥፋት በሚል ላይ ያተኮረ ስለነበር፣ በጨቋኝ መደብ ስም በአብዛኛው በየትኛውም ቦታ እንዲጠፋ የተደረገው  ዐማራው ነበር። በሌላ በኩል አብዮታውያኑ ከመደብ ጭቆና በተጨማሪ የብሔር ጭቆናም አለብ ብለው ያምኑ ስለነበር፣ አሁንም ጨቋኙ ዐማራ ነው በማለት ግራ ቀኙ በዐማራ ላይ የጥፋት ክንዳቸውን በማንሳት በስበብ አስባቡ በተገኘበት ውግዘትና ጭፍን ጭፍጨፋ ተካሄደበት። የአብዮታውያኑ መሪ መፈክር «መሬት ላራሹ» የሚል እንደነበር ይታወቃል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠትም መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ሆነ ተባለ። ይህም ለአራሹ ገበሬ የጌታ ለውጥ ከማምጣት በስተቀር የመሬቱ ባለቤት አላደረገውም። እንዳውም በከፋ መልኩ ሁሉም ገበሬ በሐምሌ በነሐሴ ለችግሩ የቀጠና ወሮቹ ለልጆቹና ለራሱ ጉርስ ያበድሩት የነበሩትን የቅርብና የሩቅ ጌቶቹን በጠላትነት አቁሞ፣ ሊያየው ወደማይችል ከሰማያት ሰማያት በራቀ የአንድ መንግሥት የሚባል ተቋም ጭኛ አደረገው። ይህም የገበሬውን ሕይዎት ከድጡ ወደ ማጡ የቀየረ እንደነበር ይታወቃል።  በጥቅሉ አብዮቱ ኢትዮጵያን  ኢትዮጵያ ያሰኟትን ነባር ተቋሞቿን ማለትም የአንድነትና የሥልጣን ምንጭ የነበረውን ዘውዳዊ ሥርዓት፣ የዘውዳዊ ሥርዓቱ እና የአብዛኛው ሕዝብ ሃይማኖታዊና ርዕዮታለማዊ ክንድ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትና ራሱን በነገድ ዙሪያ ያላደራጀ፣ በሠፊዋ ኢትዮጵያ ማንነቱን የሚገልጽ ዐማራ የተሰኘ ነገድ ነጣጥሎ ማጥፋት የሚል መርሕ ቀምረው ያስታጠቋቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች በትብብር ያቀናበሩት አብዮት ስለነበር አጥፊ እንጂ፣ ዓልሚ ነበር ለማለት ያስቸግራል።
4 «ይህ ታሪካዊና ወቅታዊ እውነታ በተለይ ባገሪቱ  ሁለት ታላላቅ ማኅበረሰቦች በከፊል ተደራራቢ የሆነ ህ(ኅ)ልውና፤ ማለትም በአ[ዐ]ማሮችና ኦሮሞዎች ማንነቶች ተወራራሽነትና ትስስር ጎልቶ ይታያል። እውነታው እርግጥ ኦ[ዓ]ይኔን ግንባር ያርገው ላሉ የጎሳ ፖለቲካ አክራሪ ወገንተኞች ስ[ሥ]ውር ይሆን ይሆናል። ብዙውን ጊዜ እንዲያውም ጠበው ህ[ሕ]ዝብ አጥባቢ በሆኑ ዘረኞች፣የኢትዮጵያን ህ[ኅ]ብረተሰብ በከፋፋይ ክልሎች አጉረውና አሽገው በሚጨቁኑ ወገንተኛ-ጎሠ[ሰ]ኛ ሊህቃን ህ[ሕ]ዝባዊ ትስስሩ የይካዳል(ይካዳል ለማለት ይሆናል)። ሆኖም በዚህ ጠባብ ወገንተኞች መካዱ ተጨባጩን ታሪካዊና ወቅታዊ ሁኔታ ፈጽሞ እንዳልነበረና እንደሌለ አያደርገውም።»  ይህ በአራት አንቀጾች የተቅጨ  የተስፋዬ ደምመላሽ ሀሳብ ለየትኞቹ የጎሳ ድርጅቶች ሊሂቃን እንደተሰነዘረ ለመለየት ያስቸግራል። ከርዕሱ ከተነሳንና ዐማራው ተደራጅቶ ኅልውናውን ያስጠብቅ ለሚሉት ሊመስል ይችላል። መነሻው ስለዐማራው ኅልውና ትግል ነውና! አዎ ለዐማራው ኅልውና አቀንቃኞች ነው ብለን ከተስማማን ደግሞ፣ በነገድ ወይም በጎሳ መደራጀትን ቀድመው የጀመሩ የዐማራው ኅልውና መጠበቅ አለበት የሚሉት እንዳልሆኑ ተስፋዬ ይስቱታል አይባልም። በዚህ ረገድ ትችቱና ነቀፌታው በዐማራው ኅልውና አቀንቃኞች ከሆነ፣«አህያውን ፈርቶ፣ ዳውላውን » እንላቸዋለን።
ተስፋዬ የተለያዩ የማኅበረሰብ ሣይንስ ተመራማሪዎች የሆኑ ምሑራን፣ ደጋግመው ያስረዱንን፣ የኢትዮጵያ ነገድና ጎሳዎች በፍልሰት፣ በጦርነት፣ በንግድ፣ በጋብቻ፣ በተፈጥሮ ገፊና ሳቢ ኃይሎች አማካኝነት የተዋሐዱና አንድ ኢትዮጵያዊ የዜግነት መለያ የገነቡ እንደሆነ ያረጋገጡልን ሐቅ፣የትኞቹ የጎሳ ድርጅት ሊሂቃን ይህን እንደካዱ ሳይገልጡልን በድፍኑየዐማራውና የኦሮሞው ነገዶች ትስስር የላቸውም ብለው እንደሚያምኑና እንደሚክዱ ገልጸዋል። ፊደል የቆጠረና የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ታሪኮች ያነበቡ ሁሉ ያጡታል የማይባለውን የዐማራና የኦሮሞ,ነገዶች ትስስር የጎሳ ሊሂቃኑ ይክዳሉ ይሉናል። እንዲህም ይሉናል፣ «እውነታው እርግጥ ኦ[ዓ]ይኔን ግንባር ያርገው ላሉ የጎሳ ፖለቲካ አክራሪ ወገንተኞች ስ[ሥ]ውር ይሆን ይሆናል» ይሉናል። ይህን የኦሮሞውና የዐማራውን ትስስር ለሚያራምዱት ፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ትስስሩ እንደሌለ ለመካድ የሞከሩ ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህም ቢሆን በዛሬው ነባራዊ ሁኔታ «ሲከፋኝ ብመለስ» ማለታቸው ይታወቃል። የካዱትም ቢሆኑ፣ ትስስሩ የበላይና የበታች አድርጎናል ነው እንጂ፣ ትስስር አልነበረንም፣ የለንምም ያሉ አይመስለኝም።  በሌላ በኩል የዐማራ ኅልውና አቀንቃኞች የሁለቱን ነገዶች ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ነገዶችና ጎሳዎች ከትስስር አልፈው አንድ የወል ማንነት የገነቡ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ሰነዶቻቸው ያሳያሉ። ለዐማራ ኅልውና የቆሙት የነገዶቹን ትስስር ክደው ወይም ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን፣ በሚከተሉት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው።
የመጀመሪያው የትግሬ ወያኔ ዘረኛ ቡድን ዐማራውን በአውራ ጠላትነት ፈርጆ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሲፈጽምበት፣ ለምን ያሉ ኅብረ-ብሔራዊም ሆኑ፣ ብሔራዊ ድርጅቶች አለመኖር፣«ባለቤቱ ካልጮኸ ጎረቤት አይደርስማና» ዐማራውን ከዘር ጥቃት ለመከላከል ባለቤቱ ቀድሞ መጮኽ ስላለበት እየተፈጸመበት ካለው የዘር ጥቃት ራሱን የመከላከል ተፈጥሮአዊ መብት እንዲጠቀም የነገዱ ልጆች ማሰባቸውና ዐማራውን በማንነቱ ዙሪያ እንዲሰባሰብ መወሰናቸው አንዱ ነው።
ሁለተኛው ሰብአዊ የሆነ ሰው፣ አምሳያው በግፍና በገፍ የዘር ጥቃት ሲደርስበት ለምን? ማለት ሰብአዊነት በመሆኑ፣ በሰብአዊነታችን የዘር ጥቃት ሰለባ ለሆነው ዐማራ ለምን ብለን ነገዱ በማንነቱ ዙሪያ ራሱን አደራጅቶ ጥቃቱን እንዲመክት ማድረግ ዘረኝነት ሳይሆን፣ ሰብአዊነት ስለሆነ ለዚህ መቆማችን ነው።
ሦስተኛው በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ በነገዱ ዙሪያ ያልተደራጀው ዐማራው ብቻ ነው። ሁሉም ተደራጅተዋል። ሲደራጁ ደግሞ ጠላታችን ነው ብለው የፈረጁት ዐማራውን ነው። ዐማራው ባለመደራጀቱ ሁሉም እንደወደቀ ዛፍ ካናቱ ላይ ምሳሩን ያሳርፍት ጀመር። በየትኛውም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ስብስብ ዐማራው ሆን ተብሎ ተገደፈ። መገደፍ ብቻም ሳይሆን፣ተዋራጅና ተሸማቃቂ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ የሥነ-ልቦና ቅስቀሳ ተከፈተበት። ይህን ዓይነቱን የተቀነባበረ የዘር ጥቃት ለመመከት ከመደራጀት ወዲያ ሌላ ፍቱን መሣሪያ ባለመኖሩ በነገዱ ላይ ያነጣጠረውን  ዕልቅት ቀድመው የተረዱን ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስና የእርሳቸው ተከታዮች ዓርማቸውን አንግበው ዐማራውን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ መነሳታቸው ናቸው።  ይህም በመሆኑ የዐማራው ኅልውና አቀንቃኞች ተስፋዬ እንዳሉት  ማኅበረሰቡን በክልል የከፋፈልን አይደለንም። በእርግጥ እርሰዎ በስም ጠቅሰው ይህን አላሉም። ርዕሰዎ ግን በዐማራው ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ መልዕክተዎ ለዐማራው ይሆናል በሚል እሳቤ ነው። ከፋፋዮቹ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረዐማራ የሆነው የትግሬ ወያኔ ቡድንና ተባባሪዎቹ «ዴድዎች» ናቸው። እና መልዕክተዎ ዒላማውን የሳተ ይመስላል። ስቷልም።
በአጠቃላይ እንዲህ እያልን የተስፋዬ ደምመላሽን ጽሑፍ ፍሬ ነገሮች በታትነን ለማየት ብንሞክር ከላይ የተገለጹት ዓይነቶች ሕጸጾች ነቅሶ ማውጣት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ ተስፋዬ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ሲነሱ ለማስተማር፣ ስሕተቶችን ለማሳየት ቢሞክሩ ኖሮ፣ለመስማትና ለመማር ዝግጁ በሆን ነበር። ሲጀምሩ የእኛን በፍላጎታችን፣ በመሰለንና ባመንበት መንገድ የመደራጀታችን መብት አወገዙ። በከፋፋይነት ፈረጁን። የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እንደማናውቅ እርሳቸው ግን እንደሚያውቁ  አድርገው አበላለጡን። የጋራ መድረክ ተከፍቶ ስለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና ስለታሪኳ ውይይትና ክርክር ቢደረግ ማን ለዕውነታው እንደቀረበና እንደራቅ ሕዝብ ሊመዝነን ይችል ነበር። ከተለላዩ ምንጮች ለመረዳት እንደሞከርኩት፣ ተስፋዬ ደምመላሽ በዚህ ወቅት ይህን ጽሑፍ ሊጽፉ የፈለጉት በአገር ቤቱ በተነሳው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ትኩሳት ተጠቅመው እኔም አለሁ በማለት ከመሰላቸው እንስት አክቲቪስት ጋር በመሆን የፖለቲካ ድርጅት ለመመሥረት ዓላማ ስላላቸው እንደሆን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የፈለጉትን ድርጅት መመሥረት መብታቸው ነው። ነገር ግን የራስን ሥብዕና ከፍ ለማድረግ የሌሎችን ዝቅ ማድረግ የምሑርነት መለያ አይመስለኝም። ክብርና ዝና በራስ ጥረት የሚገኝ እንጂ፣ ሌሎችን በማውገዝና ያለስማቸው ስም በመስጠት አይመስለንም።