BEKELE GERBA/FACEBOOK

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ በቀለ ገርባ በ30ሺ ብር ዋስትና ከእሰር እንዲወጡ የሰጠው ውሳኔ መታገዱን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ። የአቶ በቀለ ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን እንደተናገሩት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ውሳኔው መሰረታዊ የህግ ስህተት አለው በማለት ያቀረበውን አቤቱታ መሰረት በማድረግ ነው የአቶ በቀለ ገርባን ዋስትና የታገደው።

የአቶ በቀለ ገርባ ቤተሰቦች የተጠየቀውን የ30ሺ ብር ዋስትና በማቅረብ ከእስር እንዲለቀቁ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ጥረት ቢያደርጉም ማረሚያ ቤቱ የመዝገብ ቁጥር ልዩነትን በመጥቀስ ሳይለቃቸው ቆይቷል። የአቶ በቀለ ጠበቃ ጨምረው እንዳሉት ለዋስትናው መታገድ አቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት፤ ግለሰቡ ከእስር ቢለቀቁ ከሃገር ሊወጡ ይችላሉ የሚልና ሰዎችን ለአመፅ ሊያነሳሱ ይችላሉ በማለት እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ አብዱልጀባር ጨምረውም ሌሎች ምክንያቶች ከሌሉ በስተቀር የተጠቀሱት ምክንያቶች መሰረታዊ የህግ ስህተትን የሚያሳዩ አይደለም ብለዋል።

ውሳኔው ለአቶ በቀለም ሆነ ለእርሳቸው እንዳልደረሰ የተናገሩት አብዱልጀባር ውሳኔው ከደረሳቸው በኋላ ዝርዝር መልስ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። አቶ አብዱልጀባር ሰኞ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፍርድ ቤቱ ብይኑን ከሰጠ በኋላ፤ የአቶ በቀለ ገርባ ቤተሰቦች የተጠየቀውን ገንዘብ ሲፒኦ እያሰሩ ነው። የተለየ ነገር ከልተፈጠረ በቀር አቶ በቀለ ዛሬ (ሰኞ) ይፈታሉ ብለን እንጠብቃለንሲሉ ተናግረው ነበር።

የዋስትና ጥያቄው በሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎት ውሳኔ የታገደ ሲሆን፤ አቶ በቀለ ገርባም ኅዳር 14/2010 .ም መልስ እንዲሰጡ ታዘዋል። ባሳለፈነው ነሃሴ አቶ በቀለ ገርባ ያቀረቡትን የዋስ መብታቸውን ጥያቄ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። ከዘጠኝ ዓመት በፊትም 8 ዓመት ተፈረዶባቸው ከሶስት ዓመት የእስር ቆይታ በኋላ ነበር የተፈቱት።

አቶ በቀለ ገርባ ኅዳር 2008 .ም ነበር በድጋሚ ተይዘው የታሰሩት።