በኤርትራ የአሜሪካ ኤምባሲ ሰላማዊ ሰልፈኞች አስመራ ከተማ ውስጥ ድምፃቸው እያሰሙ እንደሆነና የጥይት ድምፅ ከየቦታው እንደተሰማ አስታውቋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገፃቸው እንደገለጹት ሰላማዊ ሰልፎች ቢታዩም ምንም ዓይነት ረበሻ የለም። አነስተኛ ሰላማዊ ሰልፍ አስመራ በሚገኝ አንድ ት/ቤት ቢስተዋልም ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስ ተበትኗልሲሉ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል። ሰልፉን ያካሄዱት ደያእ አል ኢስላም የተሰኘ የሕዝብ ት/ቤት ተማሪዎች መሆናቸውም ታውቋል። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተቃወሙ የት/ቤቱ አስተዳዳሪዎች መታሰርን በመቃወም ነው ተማሪዎቹ ሰልፉን ያከናወኑት። መንግሥት በት/ቤቱ ሂጃብ መልበስ እንዲቆም፤ ሀይማኖታዊ አስተምህሮት እንዲቀር እና ፆታ ተቀላቅሎ ትምህርት እንዲሰጥ ማዘዙን ተከትሎ ነው ተቃውሞ የተሰማው። ቢቢሲ የማስታወቂያ ሚኒስቴሩን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ሆኖም ከአስመራ አንድንድ ምንጮች እንደገለጡት ከሆነ ከአመፁ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች አሉ። በኤርትራ የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞቹ መሰል ሰላማዊ ሰልፎች ሊከናወኑ በሚችሉባቸው የከተማዋ ክፍሎች እንዳይሰማሩ አስታውቋል።

በአስመራ አንዳንድ ክፍሎች መንገዶች ሊዘጉ ይችላሉ። ፖሊስም ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል። ሰልፈኞቹ ሰላማዊ ቢሆኑም ወደ ግጭት ሊቀየሩ ይችላሉሲል መግለጫው ያትታል። በሌላ በኩል በአስመራ የጣልያን ኤምባሲን አግኝተን ለማረጋገጥ እንደሞከርነው ሰላማዊ ሰልፉ ዕለተ ማክሰኞ 11 ሰዓት አካባቢ ነው የተካሄደው። ኤርትራ ውስጥ መሰል ተቃውሞዎች መመልከት እጅግ ያልተለመደ ነው፤ የሃገሪቱ ሕገመንግሥትም ሰላማዊ ሰልፍን የሚፈቅድ አንቀጽ አልተካተተበትም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ኤርትራን ሰብዓዊ መብት እየጣሰች ነው ሲል በተደጋጋሚ ይወቅሳል።