November 2,2017

የኦሮሚያ ክልል ‹‹ልዩ ኃይል›› የሚባል የታጠቀ ፖሊስ እንደሌለው አስታወቀ

የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ተብሎ የሚጠራ የታጠቀ ፖሊስ እንደሌለው አስታወቀ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኮማንደር አዲስ ጉተማ፣ ‹‹በክልሉ መንግሥት የተደራጀ ልዩ ኃይል የሚባል ሠራዊት የለም፡፡›› ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው ልዩ ኃይል የሚባል ፖሊስ ሳይሆን፣ የአድማ በታኝ ኃይል ነው፡፡ ‹‹ይህን ኃይል በተለምዶ ልዩ ኃይል ብሎ የመጥራት ሁኔታ አለ›› ያሉት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ አዲስ ጉተማ፣ የአድማ በታኝ ኃይሉም ቢሆን በመደበኛው የፖሊስ ሰራዊት ስር የተደራጀ ኃይል መሆኑን በመጥቀስ፣ ክልሉ ልዩ ኃይል የሚባል ሰራዊት እንደሌለው ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው የአማራ እና ሶማሌ ክልል ኃላፊዎች ጥያቄውን ከመመለስ ተቆጥበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ አህመድ ከጋዜጣው የቀረበላቸውን ጥያቄ ካዳመጡ በኋላ፣ ምላሽ እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ጥያቄው የቀረበለት የአማራ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ ለጥያቀው ምላሽ መስጠት አልፈለገም፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ ሰዒድ ‹‹የደኅንነት ጉዳይን የተመለከተ በመሆኑ የክልሉን የፖሊስ አረጃጀት መናገር አልችልም፡፡›› ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በተለይ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ግጭት ወቅት ከፍተኛ እልቂት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ ኃይል በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ ኢሌ የሚታዘዝ ሲሆን፣ በተመሳሳይም ህወሓት ከአዲስ አበባ ትዕዛዛ በመስጠት ልዩ ኃይሉን እንደሚያዘው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳንምት ፓርላማ ቀርበው ለተነሱላቸው ጥያቄ በሰጡበት ወቅት፣ የክልሎችን ልዩ የፖሊስ ኃይል የተመለከተ ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል መካከል የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ ሲመልሱ፣ ‹‹በቅርቡ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የሁለቱም ክልሎች ልዩ የፖሊስ ኃይሎች አመርቂ ሥራ ቢያከናውኑም፤ አንዳንዶቹ ግን በሕዝቦች ላይ ቃታ በመሳብ ሕይወት አጥፍተዋል፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ ልዩ ኃይል የሚባል የፖሊስ አደረጃጀት የለኝም ብሏል፡፡ የትግራይ ክልል እና የህወሓት ልዩ ኃይል አግኣዚ መሆኑ ይታወቃል፡