በክቡር አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ የልዑካን ቡድን ባህር ዳር ከተማ ሊመጣ ነው


በየመድረኩ በሚያደርጉት መሳጭና ጣፋጭ በሆነው የአንድነት ንግግራቸው የሚታወቁት የኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ከ250 በላይ ከተለያዩ የኦሮሞ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የልዑካን ቡድን መርተው በ25/02/10 .ም ወደ አማራ ክልል መዲና ውቢቷ ባህር ባህር ዳር ሊመጡ መሆናቸውን ስንሰማ በእጅጉ ተደሰትን! እኛም ለኒህ የአንድነት አቀንቃኝ ለሆኑት ሰው ከተፈቀደ ለክብራቸው መድፍ ተኩሰን ካልሆነ ደግሞ ጨፌ ጎዝጉዘን በደስታ ለመቀበል ሽርጉድ እያልነ ነው፡፡ የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች እንግዳ ተቀብሎ በማስተናገድ እና ውብ የሆነች ከተማቸውን በማስተዋወቅ እጅግ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ የአማራ ክልል ህዝቦች እንግዳን ተቀብሎ ማስተናገድ ባህላችን ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የእንቦጭን አረም ለማስወገድ ከኦሮሚያ የመጡ ከ200 በላይ ወንድሞቻችንን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን በደስታ ተቀብለን አስተናግደን ላደረጉልን ወንድማዊ ድጋፍ ከልብ አመስግነን በሰላም ግቡ ብለን ሸኝተናቸዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ አባ ገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በክብር ተቀብለን ለማስተናገድ ዝግጅታችንን አጠናቀናል፡፡