ዘመኑ ተናኘ – ለሪፖርተር ጋዜጣ/ዌብሳይት

ውዝግብ የተፈጠረባቸው የአማራና የቅማንት ማኅበረሰቦች ተቀላቅለው ይኖሩባቸው የነበሩ አራት ቀበሌዎች ላይ ውሳኔ ተላለፈ፡፡

በአማራ ክልል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአማራና በቅማንት ማኅበረሰቦች መካከል ውዝግብ በመፈጠሩ ምክንያት መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ያልተካተቱት የአራቱ ቀበሌዎች ዕጣ ፋንታ ውሳኔ አግኝቷል፡፡ እነዚህ ቀበሌዎች ላዛ ሹምየ፣ አንከራ አዳዛ፣ ገለድባና ናራ አውዳርዳ ናቸው፡፡ ላዛ ሹምየ በሚባለው ቀበሌ ላዛ የሚባለው ሥፍራ የአማራ ሕዝብ የሚበዛ በመሆኑ ወደ አማራ እንዲከለል መደረጉን፣ ሹምየ የሚባለው ደግሞ ወደ ቅማንት እንዲካለል ተደርጓል ብለዋል፡፡

ላዛ ሹምየ የሚባለው ቀበሌ ከዚህ በፊት ለዛና ሹምየ ተብሎ ለሁለት የተከፈለ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አየልኝ፣ ለአስተዳደር ይመች ዘንድ በቅርብ ጊዜ ላዛ ሹምየ ተብሎ እንደተሰየመ ገልጸዋል፡፡ የእነዚህን ቀበሌዎች ዕጣ ፈንታ ለመወሰን መንግሥት ዕቅድ ይዞ ሕዝቡን በሚወያየበት ወቅት፣ ከመንግሥት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ውሳኔ ከሕዝቡ መገኘቱንም አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው ቀበሌ አንከራ አዳዛ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አየልኝ፣ በዚህ ቀበሌ ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ኅብረተሰብ አማራ፣ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ደግሞ ቅማንት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በዚህ ቀበሌ ውስጥ አባ ለምለሟ የሚባል ጎጥ አለ፡፡ እሱ ከቅማንት ማኅበረሰብ ጋር ኩታ ገጠም ነው፡፡ አዳዛ የሚባለው ደግሞ እንደዚሁ አማራ ተብሎ ቅድም ከገለጽኩት ከላዛ ጋር ኩታ ገጠም ነው፡፡ ስለዚህ አባ ለምለሟ የሚባለው ዓለም ፀሐይ ከሚባለው ጋር አብሮ በቅማንት እንዲካለል፣ አዳዛ የሚባለው ሰፋ ያለ የሕዝብ ቁጥር ያለበት ስለሆነ ራሱን  ችሎ አንድ ቀበሌ እንዲሆንና ወደ አማራ  እንዲካለል ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

ገለድባ የሚባለው ቀበሌ ሦስተኛው እንደሆነና ይህ ቀበሌም ወደ አማራ እንደተካለለ አቶ አየልኝ አስረድተዋል፡፡ ቀበሌው አነስተኛ ከመሆኑ አንፃር ለቀበሌነት እንኳ የማይመጥን ነበር ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ ካሉት 300 ነዋሪዎች መካከል 254 የሚሆኑት ውይይት አድርገው ወደነባሩ የአማራ አስተዳደር ለመካለል መወሰናቸውን ገልጸዋል፡፡

አራተኛውና የመጨረሻው ቀበሌ ናራ አውዳርዳ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አየልኝ፣ ‹‹በዚህ ቀበሌ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው የቅማንት ማኅበረሰብ፣ አንድ ሦስተኛው ደግሞ የአማራ ማኅበረሰብ የሚኖርበት በመሆኑ ወደ ቅማንት እንዲካለል ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ቀበሌ ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ጎጦች ወደ አማራው ልንካለል ይገባል የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ጠቁመው፣ ጉዳዩ ከአስተዳደሩ መቋቋም በኋላ ይፈታል ተብሎ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የአማራና የቅማንት ማኅበረሰብ ተቀላቅሎ በሚኖርባቸው 12 ቀበሌዎች ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ታቅዶ በሁለቱ ወገኖች መካከል ስምምነት ባለመደረሱ፣ ተጨማሪ ውይይት ያስፈልጋል ተብሎ እንዲዘገዩ መደረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በስምንቱ ቀበሌዎች በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ኳቤር ሎምየ የሚባለውን ቀበሌ አዲሱ የቅማንት ማኅበረሰብ አስተዳደር ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህ ቀበሌ የሚኖሩ የአማራ ማኅበረሰቦች ቅሬታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረባቸውን አቶ አየልኝ ጠቁመዋል፡፡

ኳቤር ሎምየ ቀበሌ ተካሂዶ በነበረው ሕዝበ ውሳኔ የቀበሌው ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ድምፅ ሰጥተዋል የሚል ቅሬታ ተነስቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የእነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች ዋነኛ ምክንያትም ይህ እንደሆነ አቶ አየልኝ ገልጸዋል፡፡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅሬታቸውን ላቀረቡ ተወካዮች ምክሮችና ድጋፎች ከተደረገላቸው በኋላ መመለሳቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከተመለሱ በኋላም የዞኑ አመራር ከተወካዮችና ከአማራ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እንዳደረገና እስካሁንም ድረስ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል፡፡

የአማራና የቅማንት ማኅበረሰቦች አብረው የኖሩና የተዋለዱ በመሆናቸው ይህን መሰል ቅሬታ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ አየልኝ፣ አብዛኛው ሕዝብ መለያየትን የማይፈልግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል በተለይም በአራቱ ቀበሌዎች የሚቀሩ አነስተኛ ሥራዎች እንዳሉና እነዚህንም ከሕዝብ ጋር በመወያየት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ አራት ቀበሌዎች ሊካሄድ የነበረው ሕዝብ ውሳኔ የተራዘመው፣ በስምንቱ ቀበሌዎች የሚካሄደውን ምርጫ ሕዝቡ ካየ በኋላ ከዚያ ትምህርት በመውሰድ ወደ ሕዘበ ውሳኔው ይገባል በመባሉ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ምንጭwww.ethiopianreporter.com