November 2, 2017 22:56

ፀጋዬ አራርሳ

ፀጋዬ አራርሳ

አስቀድሜ የተለመደውን ኢትዮጵያዊ ሠላምታ ላቅርብ ፤ የጽሑፉ ትኩረት የሆንከው ዶ/ር ፀጋዬ  ረጋሣ  አራርሣ   ከኦሮሞ አባት እና ከአማራ እናት መወለድክን፣ ከትግራይ ሴት ጋር መጋባትህን መረጃዎች  ያመለክታሉ  ።  የውልደት  ውጤት  የሆንከው  ዶ/ር  ፀጋዬ ምርጫ የለህም እና ይህንን ማንነት ይዘህ ትቀጥላለህ ። ከዚህ  ውጪ  ከሕይወህ  ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለምሳሌ ጋብቻ ፣ ዕምነት ፣ ፖለቲካ … ወዘተ በተመለከተ በፍላጎትህ    እና በምርጫህ ትወስናለህ ።

ስለ አንተ ምንነት እና ማንነት ለመናገር ወይም ለመጻፍ አመታት ይፈጃል ፣ ያን ያህል ፈጅቶም አንተን    አገኘሁህ ፣ አወኩህ ማለት ያስቸግራል ያም ሆኖ ስለማንነት  ፣ ስለአማርኛ ቋንቋ እና ስለአማራ እና ትግሬ መጤነት ከተናገርካቸው ላይ በማተኮር ትንሽ ልበል ። የምለው ሁሉ ከራሴ  ፍላጎት  ወይም  ስሜት  ወጥቼ  ከራስህ  አባባል  እና የተመዘገቡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነው ።

ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም

ዶ/ር ፀጋዬ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ብለሃል ፤ መታወቅ ያለበት እንደማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ፀጋዬም መጀመሪያ ሰው ነው ፣  ይህንም  ያገኘው  ከኦሮሞ  አባቱ  እና  ከአማራ እናቱ ነው ። ይህ ዕውነታ በዶ/ር ፀጋዬ ፍላጎት የሚቀየር  አይሆንም  ፣  እሱ  ግን ተፈጥሮውን ቀይሬዋለሁ እያለ ነው ። ከሁለት ብሔረሰብ አባላት መወለዱ የሚቆጨው ዶ/ር ፀጋዬ በራሱ ላይ የደረሰውን እና የማይመቸውን በልጆቹ ላይ እንዲደርስ ወዶ እና  ፈቅዶ የትግራይ ሴት  አገባ  ።  በነገራችን  ላይ  የዶ/ር  ፀጋዬ  ልጆች  ልጆቹ  እንጂ  ዶ/ር ፀጋዬ ባለመሆናቸው በራሳቸው መንገድ ማንነታቸውን እንደሚያገኙ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ።

የተፈጥሮ ማንነትን መቀበል ያቃተው የፈለገውን ማንነት የመረጠ ያልፈለገውን የተወዎ ፣ በራሱ ላይ እንዲደርስ የማይፈልገውን በልጆቹ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ፣ ለራሱ ክብር መቆም ያልቻለው ፣ በአጠቃላይ በማንነት ውThንብር ውስጥ የገባው ዶ/ር ፀጋዬ ወደ አደባባይ ወጥቶ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ላስተምር ፣ ልናገር ፣ ጥብቅና ልቁም ፣ ላደራጅ ፣ ልምራ ፣ ነፃ ላውጣ ቢል የሚነሳበትን የተአማኒነት ፣ የአቋም ፣ የዓላማ ፅናት

፣ ወገንተኝነት ፣ ሚዛናዊነት ፣ የሙያ ሥነ ምግባር ፣ የሞራል ብቃት ፣ ሕዝባዊነት ፣ የመርህ … ወዘተ ጥያቄዎችን የተገነዘበ አይመስልም ።

ዶ/ር  ፀጋዬ  ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚባል   የለም ፣ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ፣ ኦሮሞነት የማንነት መገለጫዬ ነው ፣ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ብሏል  ።  ከዚህ  አነጋገር  መረዳት የሚቻለው ዶ/ር ፀጋዬ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም ብሎ ተነስቶ አለ ብሎ እንደደመደመ  ነው ። ዶ/ር ፀጋዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ካለ ኢትዮጵያ  ሀገሬ  ናት  የሚል  ሁሉ  ዶ/ር  ፀጋዬን ጨምሮ ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ሀገር አላቸው ማለት ነው ፣ ሀገር የጋራ
ማንነት መነሻ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን የመጀመሪያው የጋራ ማንነት መገለጫቸው ናት ።
አገራዊ ማንነት የተወሰነ ወርድ እና ስፋት ያለው ጉዳይ ሳይሆን ከዜግነት ከእኩል መብት      እና  ግዴታ  ፣  ከዲሞክራሲ  ፣  ከፍትህ  ፣  ከእኩልነት  ፣  ከነፃነት  ፣  ከውክልና  … ወዘተ ጋር ተያይዞ በሚዳብር የጋራነት የአገራዊ ማንነት ይዘት እየተሟላ ይሄዳል ።  ኢትዮጵያዊ ማንነት መኖሩ ግልጽ ነው ፣ጥያቄው ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነት የሁሉንም  ፍላጎት ያስተናግዳል አያስተናግድም የሚለው ነው ። ይህም በመነጋገር መስተካከል የሚችል ጉዳይ  ነው ።

አገራዊ ማንነት ከመንግሥት አወቃቀር ፣ አደረጃጀት እና አሠራር ጋር ብቻ  የተያያዘ አይደለም ፣ በሕዝብ መካከል ሰፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የአግድሞሽ ግንኙነት አለ ፣ ይህ ግንኙነት የቋንቋ እና የባህል መወራረስን ፣ የእርስ በርስ ጋብቻን ፣ እንደ እድር
፣ እቁብ … የመሳሰሉ ማህበራት ምሥረታን ያስከትላል ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ በረጅም ጊዜ የጋር ማንነት እና ሥነልቦና ይፈጠራል ፣ ይዳብራል ።

አማራ እና ትግሬ መጤዎች ናቸው

አማራ እና ትግሬ መጤዎች ናቸው ፣ አይመቹኝም ፣ የአቢሲኒያ ኢምፓየር መሠረት እንደመሆናቸው  ለደረሰው  ሁሉ  ተጠያቂ  ናቸው  ይላል  ፣ የዶ/ር ፀጋዬ        የመጀመሪያው ሥህተት አገዛዝ እና ሥርዓትን ከሕዝብ መለየት አለመቻል ሲሆን ፣ ሁለተኛው ስህተት የገዢዎች ፍላጎት መግዛት እና ማስገበር እንደመሆኑ አልገዛም  አልገብርም  ባለው  ላይ ዱላው በቅድሚያ የሚያርፈው  በአካባቢው ሰው ላይ መሆኑን ካለመረዳት አማራን እና ትግሬን የሥራዓቱ ተጠቃሚ እና ተጠያቂ እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባል ።

ሥልጣን በተለያዩ አደረጃጀት በየአካባቢው ይፈጠራል ። የሥልጣን መገለጫ የጎበዝ አለቃ
፣ ንጉሥ ፣  ሱልጣን  ፣  አባ  ገዳ  ፣አሚር… ወዘተ  ሊሆን  ይችላል  ።  ሁሉም  የበላይ ለመሆን ስለሚፈልጉ ግጭት ይፈጠራል ፣ አቅም ያለው ሥልጣን ይጠቀልላል ።  ይህ የሥልጣን መነጣጠቅ ጉዞ ከአክሱም ንጉሥ  ኢዛና  ጀምሮ  ወደ  ዮዲት  ጉዲት  ፣  ዛጉዌ ሥርወ መንግሥት መልሶም ወደ  ሰለሞናዊ  ሥርወ  መንግሥት  ፣አህመድ  ግራኝ  እያለ ወያኔ እጅ ገባ ። በሌላ  በኩል  በገዳ  ሥርዓት  ላይ  የተመሠረተው  የኦሮሞ  የሥልጣን ፍላጎት እንቅስቃሴ ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሰሜን  እና  ምዕራብ  ኢትዮጵያ  ከ16ኛው መ.ክ. ዘ. ጀምሮ ይደረግ ነበር ። ይህ ጉዞ የተለየ  ቅርጽ  እና  ይዘት  ቢኖረውም የመጨረሻ ግቡ መግዛት ማስገበር ነው ። በተጨማሪም ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ወደ መሀል  ሀገር እና ሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው  የአህመድ  ግራኝ  የልግዛ  ላስገብር  ጦርነት  እንደ ሌሎቹ የሥልጣን ሽሚያዎች ተመሳሳይ ባህሪ  ያለው  ነው  ።  በሁሉም  የሥልጣን  ሽሚያ ጉዞ ብዙ ሕይወት ጠፍቷል ፣ ንብረት ወድሟል ፣ ሕዝብ ተፈናቅሏል ፣ አዲስ የሕዝብ አሰፋፈር ተፈጥሯል ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየው የሕዝብ አሠፋፈር የሁሉም የሥልጣን ሽሚያ ጉዞ እና በየአቅጣጫው የተደረገ ፍልሰት ውጤት ነው ።

ዶ/ር ፀጋዬ አፉን ሞልቶ አማራ እና ትግሬ መጤዎች  ናቸው  ይላል  ።  ሰው  በሀገሩ እንዴት መጤ ይሆናል ? ዛሬ የሚታየው የኢትዮጵያ የሕዝብ አሰፋፈር ከሞላ ጎደል የዘመናት የሕዝብ የሀገር ውስጥ ፍልሰት ውጤት መሆኑ እየታወቀ እንዴት አንዱ መጤ

ሌላው ነባር ይሆናል ? በአንድ ሀገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሕዝብ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳል ፣ ይፈናቀላል ፣ ይሠፍራል ፣ ይኖራል ፣ ችግሩ ከአለፈ በኋላ በመረጠው ሕይወቱን ያስቀጥላል ፣ ይህ አባባል ከሰሜን ወደ ደቡብ ፣ ከደቡብ ወደ ሰሜን እና ከምሥራቅ ወደመሐል ሀገር እና ሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገውን እንቅስቃሴ በእኩልነት ይመለከታል ። በዚህ ሁኔታ አማራን እና ትግሬን ነጥሎ መጤ ማለት ሚዛን ያልጠበቀ
፣ተጨባጭ ሁኔታውን ያላገናዘበ ፣ ከሙያ ሥነምግባር የወጣ ፣ጭፍን ስሜታዊነት እና ወገንተኝነት ነው ። የኦሮሞ መስፋፋት ኦሮሞን ከደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ ሰሜን መዕራብ ኢትዮጵያ ጫፍ አድርሶታል፤ለምሳሌ በደቡብ ጎንደር የጋራ ጀልዱ ፣ በጎጃም የኢልማ እና ዴንሳ ፣በወሎ የራያ ፣  በሰሜን  ሸዋ  የከሚሴ  ኦሮሞዎች  በሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ነዋሪ በእኩልነት ስለሚኖሩ አንድም ቀን መጤ ተብለው አያውቁም ።
አማርኛ ቋንቋ በዕቅድ ፣ በሕግ ድጋፍ ነው የሥራ ቋንቋ የሆነው

ዶ/ር  ፀጋዬ  ፣ አማርኛ    የመንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነው በአጋጣሚ ሳይሆን በዕቅድ ፣ በአዋጅ  ፣  በሕግ  እና  በተቋም ተደግፎ እንደሆነ        ይናገራል ። አሁንም  እውነቱን ከመረዳት ፍላጎቱን እና ስሜቱን  አስቀደመ  ፣  አማርኛ  የሥራ ቋንቋ  መሆኑ  ፣  የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ባልሆኑ ላይ መጫኑ እውነት ነው ። የሆነው ግን ዶ/ር ፀጋዬ  ባለው መንገድ አይደለም ።

በ13ኛው መ.ክ. ዘ. በዛግዌ ሥረወ መንግሥት ጊዜ በኤርትራ በሚገኘው ሎጎሳርዳ ወረዳ የአካባቢ ሕግ በትግርኛ ተጽፎ ቢገኝም አማርኛ በ12ኛው መ.ክ. ዘ. መጨረሻ ጀምሮ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ ።

የመጀመሪያው ገዢ በራሱ ምክንያት  አማርኛን  የመንግሥት  የሥራ  ቋንቋ  ሊያደርገው ችሏል ። ከዚያ በኋላ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ገዢዎች ተፈራርቀዋል ። እነዚህ  ፈላጭ  ቆራጭ ገዢዎች ላገዛዛቸው የማይመቻቸውን ሁሉ ያለ ርህራሄ ያስወግዳሉ ።  ሁሉበእጃቸው በደጃቸው የሆነላቸው ዓፄዎች በአማርኛ ቋንቋ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ አቅም አልነበራቸውም ማለት አይቻልም ፣ ማለት የሚቻለው የራሳቸውን ቋንቋ ጨምሮ አማርኛን ተክቶ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ለመሆን የሚችል አማራጭ በማጣታቸው ሳይወዱ በግድ አማርኛ እንዲቀጥል  አድርገዋል  ።  አማራጭ  ቋንቋ  ቢኖራቸው  ኖሮ  ዛሬ  ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀድሞ ፕሬዚደንት ኦባማ ጊዜያት የተላለፉ እና  የማይፈልጓቸውን ውሣኔዎች እየቀየሩ እንዳሉት ሁሉ አማርኛን አህመድ ግራኝ  በአረብኛ  / ሱማሊኛ  ፣አፄ ዮሀንስ እና መለስ ዜናዊ በትግሪኛ ፣  ትልቁ  ራስ  አሊ  ፣  ተፈሪ  መኮንን  ጋዲሳ  እና መንግሥቱ ኃይለማሪያም ወልዴ አያኖ በአፋን ኦሮሞ ሥልጣን እንደያዙ እንደሚቀይሩ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል ። ምርጫ ባለመኖሩ ግን ሁሉም የአገዛዛቸው  እና የሥርዓታቸው የደም ሥር የሆነው አማርኛ ቋንቋ እንዲቀጥል ፣ እንዲያድግ በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ እንዲሆን ገዢዎች አስፈላጊውን ሁሉ አድርገዋል ።

ዶ/ር ፀጋዬ ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ለሁሉም ይሰራል ፣ ጥያቄ የሚነሳው ይህን መብት ስንጠቀም ከስሜት ውጪ  ሆነናል ፣     ምን ያህል ሚዛናዊነትን ጠብቀናል ፣ የሞያ ሥነምግባርን አስከብረናል ፣ መረጃን መሠረት አድርገናል ፣ ሰብዓዊ ሆነናል ፣

ከወገንተኝነት ርቀናል ፣ ከድብቅ ፍላጎት ወጥተናል ፣ የሕዝብን ፍላጎት አክብረናል …
ወዘተ የሚሉት ናቸው ፣ ሁላችን ለራሳችን መልስ እንስጥ ።

ዶ/ር ፀጋዬ ማንነትህን በውስጥህ ይዘህ ፍለጋ ወጣህ ፣ አላገኘኸውም ። ለራስህ ክብር ሳትቆም ለሌላው አትቆምም ፣ በራስህ ላይ እንዲደርስ የማትፈልገውን በሌላው  ላይ አድርገሃል ፣ ተፈጥሮህን እቀይራለሁ ብለህ ግማሽ አካልህን ጥለህ በግማሽህ መኖርን መርጠሃል ። በአጠቃላይ ማንነትህን በማጣትህ በዘውገኝነት ተደብቀሃል ። የኦሮሞ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ መሆን አለመሆን ምርጫው ያንተ ፣  ዳኝነት  የኦሮሞ  ብሔረሰብ እንጂ እኔን ጨምሮ የማንም አይደለም ። ጃዋር በአማራ ድምጽ ራዲዮ ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ አንድነት ግዴታ ነው ፣ ኦሮሞ የሠራውን ቤት አያፈርስም  ፣  ዶ/ር  መስፍን አብዲ ኦሮሞ በደሙ እና በእንባው የገነባትን አገር ኢትዮጵያ ስትፈርስ ዝም  በሎ አይመለከትም ፣ ብቻውንም  ሆነ  ከሌሎቹ  ጋር  ይታደጋታል  ፣  ዶ/ር  ዲማ  ነገኦ  አማራ እና ኦሮሞ አሸዋ እና ሲሚንቶ ናቸው ፣ የኦሮሞ ወጣቶች ጣና  ኬኛ  ፣ ዶ/ር  አብራሃም ዓለሙ ኦሮሞን አታሳንሱ አታዋርዱ ፣ ባሪያ ሆኖ አያውቅም ፣ ኦሮሞ ያልተሳተፈበት መንግሥታዊ ሥርዓት የለም ፣ ዶ/ር ጳውሎስ ሚልኪያስ በኢትዮጵያ ላይ የኦሮሞ አሻራ ያላረፈበት የለም … ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል  ፣  የሚሉትን  ዶ/ር  ፀጋዬ  የራስህን ማንነት እና አቋም መለስ ብለህ ለማየት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮልሃል ብዬ አምናለሁ ።

የነሱን አባባል በሚዛኑ  አንድ ጎን የአንተን በሌላው ጎን አስቀመጠህ አመዛዝነው ። ዶ/   ር ፀጋዬ ፣ የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመረዳት የአንተን የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፍ እንድናነብ ጋብዘሃል ፣ ግብዣህ ጥሩ ነው ግን አንተ የጽሑፉ ጥሩ መስታወት በመሆንህ ገለፃህ ፣ ትረካህ እና ትዋኔህ ጽሑፍህን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ብዬ  አምናለሁ  ፣  እኔ በሃይጅን ፈተና መቶ ከመቶ አግኝቶ እጁን ሳይታጠብ እንደበላው  ተማሪ  ነኝ  ካላልክ በቀር!

ከሠላምታ ጋር