November 3, 2017 14:02

 

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት “በአማራ ትኩስ እሬሳ በባህር ዳር የለማ መገርሳ ሙገሳ!!!” በሚል አዲሱ የአቶ ለማ መገርሳን የኦህዴድ አመራር ከአማራው ክልል ጋር እያደረገ ያለዉን የመቀራረብ እንቅስቃሴ በተመለከተ የጻፈውን አነበብኩ።

“ለኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ትግል በምናደርገው እንቅስቃሴ የባህሪ አባታችንና የግንባራችን አባል ሕወሐት የምንመኘውን የኦሮሞ ነፃነት በገባው ቃል ኪዳን መሰረት ቃሉን አላከበረም፡፡ ስለሆነም የኦሮሞን ህዝብ ሙሉ ብሔራዊ ነፃነት ለማጎናፀፍ ከሕወሐት ጋር ለምናደርገው የውስጥ ትግል እንዲረዳን በስልት ደረጃ አማራን ከጎን ማሰለፍ የሚል ነው፡፡” ይህንን ስትራቴጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ በአማራ ስነ ልቦና በቀላሉ ተቀባይነት ያላቸውን ሃሳቦች ማለትም አንድነት፣የጥንታዊ ኢትዮጵያን ታላቅነት፣የሕወሐትን ጡንቻ ፈርተው በአደባባይ ባይናገሩትም ሕወሐት ከፋፋይ ስለሆነ ይህንን ተግባሩን ለማክሸፍ የኦሮሞ እና የአማራን ህዝብ አንድነት ማጠናከር ወዘተ የሚሉ የአየር በአየር ፕሮፓጋንዳ ይዞ ወደ አደባባይ መውጣት ነው” ሲል ኢንጂነር ይልቃል ከ”አማራው” ጋር ለማድረግ የታሰበው እንቅስቃሴ ከሕወሃት ጋር ኦህዴድ ባለው ውስጣዊ ትንቅንቅ ጊዜያዊና ታክቲካል እንደሆነ አድርጎ ነው ኢንጂነር ይልቃል ለመግለጽ የሞከረው። ኢንጂነር ያስቀመጠውን ሐሳብ የሚጋሩ ብዙ ወገኖች አሉ።
በሌላ በኩል የአንድነት ሃይል ውስጥ የነበሩ ለኦህዴድ አሁን ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወገኖች፣ እነ አቶ ለማ መገርሳ የሚንቀሳቀሱት ጊዜያዊ ሳይሆን በርግጥም የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከርና ያለፉት 25 አመታት የተፈጠሩ ቁርሾዎች ለማስወገድ ነው የሚል አስተያይት የሚሰጡም አሉ። እነርሱም በዋናነት ከአማራው ጋር ኦህዴድ መስራት እንዳለበት ይናገራሉ።

በኔ እይታ እንዲህ ነው ወይንም እንደዚያ ነው ብሎ አሁን መናገር የሚያስቸግር ይመስለኛል። እነ አቶ ለማ መገርሳ በአማርኛ ተተርጎሙ ከሚነገረን አንዳንድ አባባሎች ውጭ በተግባር በተለይም በኦሮሚያ ያሉ ሌሎች ማህበረሰባት መብትን በማክበር አንጻር ይሄን አደረጉ የምለው ነገር የለም። እንደውም በአንድ በኩል እዚያው ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖችን ጉዳይ ችላ ብለው ወደ ባህርዳር ማቅናታቸው ግብዝነትም ሊሆን ይችላል። ሁሉ ነገር መጀመር ያለበት ከቤት ነው። ባህር ዳር ንግግር ከማድረግ እዚያው አዳማ ከ80% በላይ የሚሆነውን አፋን ኦሮሞ ለማይናገረው ህዝብ መለክት ቢያቀርቡለትና የሚለውን ቢሰሙ ጥሩ ይሆን ነበር።
አቶ ለማ መገርሳ በቅርብ ነው ወደ ሃላፊነት የመጡት። ገና አንድ አመት አልሆናቸውም። የኢኮኖሚ ችግር፣ ስር አጥነት አለ። ከቁጥጥር ዉጭ የሆነው የቄሮዎች ተቃዉሞም አለ። ከሶማሌ ክልል ከግማሽ በላይ ህዝብ ተፈናቅሏል። ሌላው ቢቀር ክልሉ በራሱ በጣም ትልቅ እንደምሆኑ ለአስተዳደር አስቸጋሪ ነው። ክዚህም በተጨማሪ ከሕወሃት ጋር በኢሕአዴግ ውስጥ ትግል አለ። ይሄ ሁሉ ችግር ለጋው የአቶ ለማ አመራር ላይ በአንዴ ነው የተጫነው።

የባህር ዳር ጉዞ ጊዜያዊ ሆታ ከመፍጠሩ ውጭ ብዙ ፋይዳ የሚኖረው ጉዳይ አይደለም።ምን አልባት በጋራ ከኢሕአዴግ ወጥተን አዲስ መንግስት በሕገ መንግስቱ መሰረት መስርተናል የሚል ዜኖ ሊነግሩን ካልሆነ በስተቀር።
በኔ እይታ ለኦህዴዶች ልቤ ተከፍቷል። ትንሽ ጊዜ ልሰጣቸው እፈልጋለሁ። ሁለት ፣ሦስት ወራት እያልን ምንም የሚለወጥ ነገር ከሌለ፣ ያኔ እንተቻለን። በኔ እይታ የአቶ ለማ መገርሳንና ኦህዴድን አመራር ልቀበል የምችለው ሁለት መሰረታዊ በኦሮሚያ ያሉ ሌሎች ማህበረሰባት መብት ያስጠበቃሉ የምላቸው ሶስት ጥያቄ ሲመለሱ ብቻ ነው፡

1) በኦሮሚያ የሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰባት በኦሮሚያ ሕግ መንግስት ሆነ በአሰራር ፣ ከኦሮሞው እኩል መብት ሊኖራቸው ይገባል። ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ መሆኗ ቀርቶ የነዋሪዎችው መሆን አለባት። በአጭሩ ክልሉ የአንድ ብሄረሰብ/ብሄር/ዘርር መሆኗ መቆም አለበት።

2) አማርኛ ከአፋን ኦሮሞ ጋር አብሮ የክልሉ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት። ለምሳሌ በምስራቅ ሸዋ ዞን ወደ አንድ ሶስተኛው፣ በአዳማ ልዩ 85% አማርኛ ተናጋሪ ሆኖ፣ በነዚህ ዞኖች አገልግሎት በኦሮሞኛ ብቻ በአስተርጓሚ መሰጠቱ ተቀባይነት ሊኖረው አይችል። ይሄ እስተካከል አለበት።

3) የክልሉ መንግስት የኦሮሞዎች መንግስት ሳይሆን የነዋሪዎቿ መንግስት መሆኑን ማሳየት አለበት።፡ባህር ዳር መሄድ ሳይሆን በኦሮሚያ ያሉ ሌሎች ማህበረሰቦችን መወከልና ማገለገለ መጀምር አለበት።

እነዚህ ሶስት ጥያቄ ኦህዴድ የማያሟላ ከሆነ ለኔ የአሁኑ ኦህዴድ ከትላንትናው ኦህዴድ አይለይም ማለት ነው። እንኳን ልደግፈው አጥብቄ የምቃወመዉና የምታገእው ነው የሚሆነው።