November 3, 2017 21:38

ሐራ ዘተዋሕዶ

ተገቢ ግንኙነት እንዲያደርግ መመሪያ ይተላለፍለት ዘንድ የክልሉን መንግሥት ጠየቀ
የዞኑ አስተዳዳሪ የደገፉት ጎጠኝነት፣ ለሀገረ ስብከቱ ህልውናና አንድነት ስጋት ኾኗል
“አፋጣኝ የአመራር ማስተካከያ አድርጉ ብለው ወገንተኛና ጣልቃ ገብ ደብዳቤ ጽፈዋል”
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕን ለማስነሣት፣በሕዝቡ ስም በቅ/ሲኖዶስ ላይ በፓትርያርኩ ቀርቧል
ብፁዕነታቸው ያስቀጧቸው አድመኞች፣ ጎጥ እየለዩና እየከፋፈሉ ከማወክ አልታቀቡም
†††
የአቡን ቤት ቅ/ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ እና የአጥማቂዎች አለመግባባት በግልጽ ያስረዳል
ሰበካ ጉባኤው፥የጠበል ቤት ገቢና የቅባ ቅዱስ ሽያጭ ያካተተ የቁጥጥር ርምጃ ወስዷል
ሰበካ ጉባኤውን በጎጥ ተቆጣጥሮ ደብሩን የመረከብና ከመዋቅር የማውጣት አድማ አለ
አለመግባባቱ፥ በቃለ ዐዋዲው፣ በገለልተኛ ሽማግሌዎች እና ታዛቢዎች ተጣርቶ ይፈታ
“እከሌ ሰሜን፣ እከሌ ደቡብ”እያሉ አንድነቱን በሚሸረሽሩት ወጣቱ ሊነቃባቸው ይገባል፤
†††

ከጎጠኝነት፣ ስርቆትና የቤተ ዘመድ አሠራር ጋራ በተያያዘ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በየቀኑ ግጭትና ሁከት እንደሚፈጠር የገለጸው የሰሜን ጎንደር ዞን፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ አፋጣኝ የአመራር ማስተካከያ እንዲያደርግ የጠየቀ ሲኾን፤ ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ፣ የዞኑ ጥያቄ ወገንተኝነትና ጣልቃ ገብነት እንደኾነ በመቃወም ተገቢውን ግንኙነት እንዲያደርግ መመሪያ ይተላለፍለት ዘንድ ለክልሉ መንግሥት አቤቱታ አቀረበ፡፡
ዞኑ፣ ባለፈው መስከረም መጨረሻ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፈው ደብዳቤ፥ ምእመኑን በጎጥ የሚከፋፍል፣ በስርቆትና የዘመድ አዝማድ አሠራር ሥር የሰደደ አመለካከትና ተግባር እንደሚታይ ጠቅሷል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሐሜትና አሉባልታ ነግሦ ኅብረተሰቡን በየቀኑ እያጨቃጨቀ፣ እያወከና እያጋጨ በመኾኑ ሰላምንና ጸጥታን ለማስከበር አስቸጋሪ እንዳደረገበት ገልጿል፡፡

ሕዝቡን ወደ ድጋሚ ብጥብጥና ሁከት ሊያስገባው ይችላል፤ የሚል ስጋት እንዳሳደረበትና የመልካም አስተዳደር ችግሩ በፍጥነት እንዲፈታ ጠቁሟል፤ መፍትሔውም አፋጣኝ የአመራር ማስተካከያ ማድረግ እንደኾነ አስታውቋል፡፡ “የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አፋጣኝ የአመራር ማስተካከያ እንዲያደርግ እየጠየቅን፣ ይህ ሳይኾን ቀርቶ በሚፈጠረው ችግር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለጸጸት የሚጥልና እኛም ሓላፊነት ለመውሰድ የምንቸገር መኾኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፤” ብሏል – የዞኑ ደብዳቤ፡፡

በቁጥር ማጎ01/142/ሥ-36፣ በቀን 30/01/2010 ዓ.ም.፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ሙሉ ዓለም ተፈርሞ በአድራሻ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የተጻፈው ደብዳቤ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ባጠናቀቀበት ባለፈው ማክሰኞ ከቀትር በፊት፣ በርእሰ መንበሩ ቀርቦ ምልአተ ጉባኤውን እንዳነጋገረ ተመልክቷል፡፡

“አፋጣኝ የአመራር ማስተካከያ አድርጉ” በማለት የዞኑ አስተዳዳሪ የጠየቁት፣ “ሊቀ ጳጳሱን አንሡልን” ማለት እንደኾነ ወዲያው ነበር የታወቀው፡፡ የጎንደር ሕዝብ ብፁዕነታቸውን እንደከሠሠና ተቃውሞውም የሕዝቡ እንደኾነ አድርገው ያቀረቡት ፓትርያርኩ፣ “ከሕዝቡ ጋራ ተስማምተው መሥራት አልቻሉም፤ መነሣት አለብዎት፤” በማለት መናገራቸው ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችንና ምላሾችን ጋብዟል፡፡ ከሌሎች ብፁዓን አባቶች ጋራ እየተናበቡ የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና ያስከበሩት የክፍሉ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕም በታወቀው ትዕግሥታቸውና ብልሃታቸው የከሣሾቻቸውን ማንነት ነው የጠየቁት፤ ልኡክ ተመድቦ ጉዳዩ እንዲጠና በተወሰነው መስማማታቸውም ቀናነታቸውንና ቀጥተኝነታቸውን አረጋግጧል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጻፉትን ደብዳቤ በመያዝ ትላንት፣ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ባሕር ዳር ያመሩት የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ለክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ባሰሙት የተቃውሞ አቤቱታ፣ ዞኑ ከሀገረ ስብከቱ ጋራ ከጎጠኝነት የጸዳና ሕገ መንግሥቱን ያከበረ ግንኙነት ያደርግ ዘንድ መመሪያ እንዲተላለፍለት ጠይቀዋል፡፡

የ85 ዓመት የዕድሜ ባዕለጸጋው ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ካሉን ጥቂት አንጋፋ ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ ናቸው፡፡ ለኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ ከበቁበት ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ፥ በጅማ፣ በጋሞጎፋ፣ በደቡብ ጎንደር እና ከመጋቢት 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን ጎንደር አህጉረ ስብከት ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን ለ40 ዓመታት ገደማ በትጋት እየተወጡ ያሉ ኖላዊ ትጉህ ናቸው፡፡ ከደቡብ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ለብዙዎች የክህነት አባት ናቸው፡፡ በፀረ ተሐድሶ ተጋድሏቸው በቀዳሚነት የሚጠቀሱትን ያህል፣ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽና በቡራኬም ያልረገጡት አጥቢያ የለም፡፡ ፎቶው፣ በረሓ ወርደው የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እብነ መሠረት አስቀምጠው ሲመለሱ ያሳያል፡፡

ችግሮች እንዲፈቱ መጠየቅና በጋራ መሥራት ተገቢ ኾኖ ሳለ፣ “አፋጣኝ የአመራር ማስተካከያ አድርጉ” በማለት በቅዱስ ሲኖዶስ የተመደቡት አንጋፋ ሊቀ ጳጳስ እንዲነሡ መጠየቅ፣ መርሕን የጣሰ ጣልቃ ገብነት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ “ይህን ካላደረጋችሁ ችግር ይፈጠራል” ብሎ ማስፈራራትም፣ ሓላፊነት ከሚሰማው አስተዳደር የማይጠበቅና የአንድ ወገንን ፍላጎት ለማስፈጸም ከመፈለግ የመነጨ ጫና ማሳደር በመኾኑ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡

ሕግንና አሠራርን ባለመጠበቅ የሚፈጠርን የመልካም አስተዳደር ችግርና የገንዘብ ብክነት፣ ሀገረ ስብከቱ በየጊዜው እየተከታተለ በመፍታት የሥራ ሒደቱን ሰላማዊ ለማድረግ እየጣረና ባልተሰጣቸው ተልእኮ ራሳቸውን ሠይመው ዕንቅፋት መፍጠራቸው በማስረጃ በተረጋገጠባቸው ጎጠኞች ላይ ርምጃ እየወሰደ ባለበት ኹኔታ፣ አለመግባባቶች ጨርሶ መፍትሔ እንዳላገኙ አስመስለው የዞኑ አስተዳዳሪ መጻፋቸው በእጅጉ እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ተመድበው ከመጡበት ከመጋቢት ወር 2001 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የራቀውን በማቅረብና የተጣላውን በማስታረቅ በሚሰጡት አባታዊ ምክርና መመሪያ ሀገረ ስብከቱ አንጻራዊ ሰላም አግኝቶ መቆየቱን ጽ/ቤቱ አውስቷል፡፡ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በማባባስ ሁከት የሚፈጥሩት፣ ሕግንና አሠራርን ለማስከበር የሚደረገው ቁጥጥር ያላስደሰታቸው ጥቅመኛ አካላት እንደኾኑና “እከሌ ሰሜን ጎንደር፤ እከሌ ደቡብ ጎንደር” እያሉ እየከፋፈሉና ጎጥ እየለዩ የሀገረ ስብከቱን ህልውናና የሕዝቡን አንድነት እየተፈታተኑት እንዳሉም አብራርተዋል፡፡

በሰላም የሚሠራውንና የተለያየ ተወላጅነት ያለውን የጽ/ቤቱን ሠራተኛ በሤራ የሚከፋፍሉ ግለሰቦች ተገምግመው በተገኘባቸው የሥራ ግድፈት ከሓላፊነታቸው ቢነሡም፣ በአምሳላቸው ያዋቀሯቸው “ቅሬቶች”፣ በደብረ ምሕረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፣ አንዳንድ ፀበልተኞችንና ግለሰቦችን በማደራጀት ሰላም እየነሱ እንደሚገኙ ሀገረ ስብከቱ በተቃውሞ አቤቱታው አስፍሯል፡፡

“አጥማቂዎችና ፀበልተኞች አፈናና ጠለፋ ተካሒዶባቸዋል፤” ሲሉ ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ ያቀረቡት አቤቱታ፣ በፖሊስ እንዲጣራና በሕግ እንዲታይ እየተሠራ እያለ፣ በሕገ ወጥ ስብሰባ ባቋቋሙት ኮሚቴ እየተሰለፉ ስም በማጥፋታቸውና በመረበሻቸው ሀገረ ስብከቱ እንደማያውቃቸው ጠቅሶ፥ ለከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ለጸጥታና አስተዳደር መምሪያና ለፖሊስ መምሪያ በጻፈው ደብዳቤ መንግሥት ጸጥታ እንዲያስከብርለት ጠይቋል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘውና ኹለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ ሲመረጥ የተረከበውን 400ሺሕ ብር ተቀማጭ ወደ ሦስት ሚሊዮን ብር በማሳደግ በሀገረ ስብከቱ ተሸላሚ እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡ አጥማቂዎቹና ግለሰቦቹ በበኩላቸው፣ “ሰበካ ጉባኤው ገንዘብ አጥፍቷል፤ ይጠየቅልን”  በማለት እንዳመለከቱና ይህም በቃለ ዐዋዲው መሠረት እንዲሁም በገለልተኛ የሀገር ሽማግሌዎችና የመንግሥት ታዛቢዎች ሊታይ እንደሚችል ተገልጾላቸዋል፡፡ ሰበካ ጉባኤው ለመጠየቅ ዝግጁ እንደኾነ ሲያስታውቅ ሀገረ ስብከቱም፣ “ከሣሽ ተከሣሽ ይለዩ” ብሎ ችግሩ እንዲረግብና በመነጋገር እንዲፈታ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ግለሰቦቹና ቡድኖቹ ግን፣ ሕገ ወጥ ድርጊታቸውን ለሰባት ተከታታይ እሑዶች እንደቀጠሉና ምእመኑን ከማወክ እንዳልተቆጠቡ፤ አስተዳዳሪው መልአከ ኃይል አባ ገብረ እግዚአብሔር ደምሌም፣ ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ታግደው እንዲቆዩ መደረጉን ገልጿል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ ለፓትርያርኩ ያደረሱት ደብዳቤ፣ ኹኔታው በዚህ ደረጃ እያለ መኾኑና በዚህም ኾነ ከከተማው ውጭ በሚመሯቸው ወረዳዎች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ከብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ አንዳችም ሳይነጋገሩና ሳይመካከሩ በቀጥታ መጻፋቸው “ጣልቃ ገብነትን ያሳያል፤”ብሏል፡፡ ከቁጥጥር ያልወጣ አጠቃላይ ችግር ሳይፈጠር እንደተፈጠረ በማስመሰል፣ “ጉዳዩ ካልተፈታ የዞናችን ሕዝብ ድጋሚ ወደ ብጥብጥና ሁከት ሊገባ ይችላል፤” ያሉትንም የማይኾን ትንቢት” ሲል ተገርሞበታል፡፡

አድማውን የሚመሩ ግለሰቦች በአጣሪ ኮሚቴ አባልነት መግባታቸውን ሀገረ ስብከቱ ለሰላም ሲል ተቀብሎ የማጣራቱ ሥራ እንዲጀመር ደብዳቤ ቢጻፍም፣ መዋቅሩን ለመናድ ከመንቀሳቀስና ከመሳደብ እንዳልቦዘኑ የዞኑ አስተዳደር እያወቀ ምንም እንዳላደረገ መታዘቡንም በአቤቱታው ጠቅሷል፡፡ ከዚህ አንጻር፣ “የአመራር ማስተካከያ አድርጉ” በሚል የዞኑ አስተዳደሪ የጻፉት ደብዳቤ፣ በሀገረ ስብከቱና ከሀገረ ስብከቱ ውጭ፣ “ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር” እያሉ የመለያየትን ሐሳብ የሚያራምዱ ግለሰቦችን የሚደግፍ ኾኖ አግኝነተነዋል፤ ብሏል፡፡

ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ እንደኾኑ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው እንደተጠበቀ ኾኖ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮች በጋራ ምክክር እየተፈቱ እንደቆዩ ያስታወሰው አቤቱታው፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ የሚከተሉት አሠራር የተለየ ነው፤ ሲል በጣልቃ ገብነታቸው ቅር መሰኘቱን ገልጿል፡፡ መርሕን የጣሰው ደብዳቤያቸው በብዙዎች እጅ ገብቶ የደብረ ምሕረት አቡነ ቤት ቅዱስ ገብርኤል ችግርን እንዳባባሰውም ወቅሷል፡፡

እርሳቸው የጻፉት ደብዳቤ በእያንዳንዱ ግለሰብ እጅ ተይዞ፣ በአንድ በኩል፣ መንግሥት ከእኛ ጋራ ነው፤ እያሉ፤ በሌላ በኩል፣ ሕዝበ ክርስቲያን በተሰበሰበበት፣ መንግሥት የለም፤ የሚል የዐመፅ ስብከት በዐውደ ምሕረት እንዲነገርና መዋቅር በኃይል እንዲፈርስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሕጓና በደንቧ እየተመራች ሕጋዊ አሠራር እንዲሰፈንባት፤ በዐመፅ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፤ የዞኑ አስተዳደር ከቤተ ክርስቲያንና ከሀገረ ስብከቱ ጋራ ያለው ግንኙነት መርሕን የተከተለና አግባብነት ያለው ሊኾን እንደሚገባ አቤቱታው አስገንዝቧል፡፡ ስለዚህም የክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ቢሮ፥ ለማዕከላዊ ዞን ጸጥታና አስተዳደር መምሪያ፣ ለጎንደር ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽ/ቤት ተገቢው መመሪያ እንዲያስተላልፍ ሀገረ ስብከቱ በተቃውሞ አቤቱታው ጠይቋል፡፡

የተቃውሞ አቤቱታውን የተቀበለው ቢሮው፣ የዞኑ አስተዳደሪ ለፓትርያርኩ የጻፈው ደብዳቤ እንዳሳዘነው ለሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች መግለጹ ተነግሯል፤ “እንመካከርበታለን፤ መመሪያም እንሰጣለን፤” በሚል ተስፋ እንዳሰናበታቸውም የጽ/ቤቱ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

በደ/ም/አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ሰበካ ጉባኤና በአጥማቂዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት፣ የዞኑን አስተዳደር የመርሕ ጥሰት አጉልቶ ቢያሳይም፣ “ዋናው ጉዳይ የጎንደርን ሕዝብ አንድነት ለመሸርሸር የተፈጠረ እንደኾነ መታየት አለበት፤” ሲሉ ይመክራሉ የጉዳዩ ታዛቢዎች፡፡ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ አጥማቂዎቹ በግማሹ የሚወስዱትን የጠበል ቤት ገቢ በመቆጣጠሩና በረዳት ስም በመቃብር ቤት የሚያኖሯቸውን ዘመዶቻቸውን አስወጥቶ ሥርዓት በማስከበሩ፣ “ለምን ተነካን” በሚል የጎጠኝነት አጀንዳ መራገቡ ይህንኑ እንደሚያረጋግጥ ታዛቢዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ጎጠኝነት፣ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ጉባኤ ቤት ሕንፃ ሥራም ላይ ዕንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁንም በአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፣ በአንድ ጎጥ የተደራጀ ሰበካ ጉባኤ በማስመረጥ፣ ደብሩን ለመረከብና ከመዋቅር ለማስወጣት የሚንቀሳቀሱ ሊከለከሉና ሊጋለጡ እንደሚገባ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ከመጋቢት ወር 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ሀገረ ስብከቱን በሰላም በመምራት ላይ ያሉት አንጋፋው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ የዋህ፣ ደግና እውነት ተናጋሪ አባት በመኾናቸው ሊከበሩ ሲገባ፣ በእኒህ ወገኖች በመድረክ የተዘለፉትም፣ “ከፖሊቲካም ከጎጥም ስለሌሉበት ነው፤” ብለዋል ታዛቢዎቹ፡፡ ሥራ አስኪያጁን ሊቀ አእላፍ ቀለመ ወርቅ አሻግሬን ባላደረገው ነገር ማሳሰራቸው ሳይበቃ አሁን ደግሞ፣ “የአመራር ማስተካከያ” በሚል ብፁዕነታቸውን ለማንሣት በዞን አስተዳደር ደረጃ መታሰቡ፣ “የሀገረ ስብከቱን ህልውናና አንድነት የሚፈታተኑ አካላት ድርጊት ነው፤” ሲሉ ኮንነውታል፡፡

በሀገረ ስብከቱ፣ የአመለካከትና የሥነ ምግባር ችግር የሚታይባቸው ሓላፊዎች የሉም፤ ባይባልም፣ ምእመኑ በተለይም ወጣቱ፣ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ከሀገራዊ አንድነቱና ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ መጠበቅ አንጻር በስክነት እያጤነ አቋም ሊወስድ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡