Share
Tweet
Pin
Email
Share

 

እንስማው ሐረጉ

ገና ጉብል ፣ በግምት 6 ዓመት እያለሁ፤ በልጅነቴ ጎረቤታችን መሪጌታው ቤት እዬሄድሁ ሀ ሁን እማር ነበር። መሪጌታውን “የኔታ” ብለን እንጠራቸው ነበር። የኔታ የጥበብ የመጀመሪያው አባቴ፤ያኔ ገና ጥበብን ማወቅ ስጀምር። የኔታ ቤት የነበረ “ጥብቅ ህግ” ምንግዜም የማልረሳው ደንብ ነበር። እሱም በትምህርት ሰዓት ከተማሪዎች መካከል አንዳችን ጥፋት ካጠፋን መጨቃጨቅ ወይም መደባደብ  ወይም መሳደብ ፈጽሞ ክልክል ነበር። የኔታ ቤት ወንድነት የሚባል ነገር የለም፤ የኔታ ቤት ወንድነት በፍጹም አያስፈልግም ነበር። ጀግንነት የጋን መብራት የሆነበት ቦታ ቢኖር የየኔታ ራስ አስተዳደር  ክልል የልጅነት ትምህርት ቤቴ ነው! የኔታ ቤት ስርዓት እና ስነምግባር ብቻ ናቸው የነበሩ። ዳኝነትና ፍርድም እንደወረደች በተግባር ትውላለች። ስለሆነም ጥፋት ያጠፋው አካል በቀጥታ ኮሽታ ሳያሰማ የኔታ ባሉበት ቦታ ሄዶ ጸጥ ፤ቀጥ፤ ጭጭ ብሎ የኔታ ካሉበት ሶስት ርምጃ ያህል ርቆ መቆም አለበት። ለየኔታ ማመልከቻ ይዞ መቅረብ የለም። ማመልከቻው “ጸጥ ፤ቀጥ ፤ጭጭ” ብሎ መታዬት ነው። አስታውሱ የኔታ ቤት የሚሄደው የተጎዳው አካል ሳይሆን ጉዳት ያመጣው አካል ማንም ሳያስገድደው እራሱን አሳምኖ ነው፤ ከሳሽና ተከሳሽ ብሎ ነገር የለም። አጥፊው ብቻ ሄዶ ለንስሃ የኔታ ፊት ይቀርባል እንጂ። የኔታም አይተው እንዳላዩ ዝም ብለው ይቆያሉ። በጣም የሚገርመው ቆይታቸው ለሰዓታት ሊሆን ይችላል። ቅጣቱ ከዚያ ነው የሚጀምር። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ነው እንጂ ቅሉ ለማለት የፈለግሁት ስለዝምታችሁ ነው። አብዛኛዎቻችን በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጠበቁ ነገር ግን በሰፊው የሚታዩ ትላልቅ ክስተቶችን እያየን እንዳላየን፤ ወይም መሳተፍ ካለመፈለግ ወይም “እኔ ምንም ለውጥ አላመጣም” ከማለት ወይም ካለመመቻቸት ሊሆን ይችላል ብቻ በተለያዩ ምክንያቶች “ጸጥ ፤ቀጥ ፤ጭጭ” ማለትን የመረጥን እንመስላለን። ሌሎቹ ደግሞ ሲጮሁ እያዬን ነው።

ወያኔ በመሰረታት የኢትዮጵያ አስተዳደር ክልሎች የወቅቱ የኦሮምያ ክልል መሪ የሆኑት ወጣቱ አቶ ለማ መገርሳ ወደ ሌላኛው ወያኔ ሰራሽ ክልል የአማራ ክልል አጃቢዎቻቸውን ይዘው ባህር ዳር እንደከተሙ እያዬን ነው። የአባይን ድልድይ በእግራቸው እዬተንጎማለሉ፤ ፈንዳ ጎላ ፤ ሲሉ አዬን፤ እኛም ደስ አለን። እኛ የአንድነት ኃይሎች ስንመኘው የነበረ ይህንኑ ስለነበር። ጉብኝታቸው በዩቱበ የምናዬውን የድሮውን የአጼ ኃ/ስላሴን ሽርጉድ ይመስላል ነገር ግን ልዩነት አላቸው። የአጼው አባታዊ ፍቅር ያለበት ህዝቤ በሚሉት በመላው  አገርና ወገናቸው ነበር። የዚህኛው ደግሞ ጥርጣሬ የቋጠረ፤ “ወደነሱ ክልል” የሚል  የባኧድ መንፈስ ያለበት፤ ተልአኮው በቅጡ ያልታወቀ፤ እንደማይተዋወቁ ሁለት የተለያዩ አገር ህዝቦች የማቀራረብ ነገር ይመስላል። የአቶ ለማ መገርሳ ጉብኝት የተለያዬ መላምት ቢያሰጥም አብዛኛዎቻችን ግን ይሁን ብለናል። አንዳንዶች ወያኔ በስትኋላ አለበት፤ ጉብኝቱ የወያኔ አጀንዳ ነው በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል። ሌሎቻችን ደግሞ ወያኔ ኖረበትም አልኖረበትም ጉብኝቱ በጄ መባል አለበት ምክንያቱም ህዝቡን እስካቀራረበ ድረስ። ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ወደ አንድነት እንዲመጣ አጀንዳ ቀርጾ ከሆነ ተገዶ እንጂ ወዶ ሊሆን አይችልም። ተገዶ ካደረገው ድግሞ ጥሩ ነገር ነው። ምንም ይሁን ምን እንደዚህ ያለ የእንድነት ተግባር መደገፍ አለበት ምክንያቱም የለጦች ሁሉ መጀመሪያው አንድነታችን ስለሆን።

ጉብኝቱን የተቃወሙት ወገኖች መከራከሪያ ሃሳቦችን አንስተዋል። ከነዚህም ውስጥ በጥቂቱ ከተባሉት እነሆ። አቶ ለማ መገርሳ ከልባቸው ከሆነ የሚከተሉትን ያድርጉ ብለዋል።
ሀ) የአኖሌን ሃውልት መጀመሪያ ያፍርሱ፤
ለ) ለተፈናቀሉት አማራ ወገኖች ርዳታ ይስጡ፤ የጉብኝቱ ወጪም ለተረጂዎች ይሰጥ ጉብኝቱ ይቅር፤
ሐ) ከልባቸው ከሆነ አማራም ኦሮሞም ሌላውም በእኩል የሚኖርባት እትዮጵያ መሆኗን ይናገሩ
መ) ወያኔ እንዳልላካቸው ማረጋገጫ ይስጡ፤ ወዘተርፈ ብለዋል።

ከፈረሱ ጋሪው አይነት ነገር እንዳይሆን ሰጋሁ። በእኔ ግምት እነዚህንና የመሳሰሉትን መከራከሪያዎች የሚያቀርቡት ወገኖች አገሪቱ ያለችበትን የ27 ዓመት ምስቅልቅል ጉዞ እንደ ቀላል ከማየት የመጣ ነው ብዬ አስባለሁ። አንዳንዶቹ ደግሞ መቃወም የለመዱ በተቃውሞ መቀጠል የፈለጉ ይመስላል። ስንቃወም በምክንያት እንጂ ያለ ምክንያት መሆን የለበትም። ለመሆኑ ከላይ ያሉትን ጥያቄዎችና የመሳሰሉትን ጥርጣሪ የሚያጭሩ ሁኔታዎችን ግልጽ መልስ ለመስጠት መቅደም ያለበት የአቶ ለማ የተግባር የአንድነት ጥሪ  ወይስ ሀገ መንግስት መጻፍ? መነጋገር ሳይመጣ  ማዶ ለማዶ በጥርጣሬ እንደ ጠላት እተያዩ እንዴት ችግር  ይቀረፋል? አንዳንዶቹ በጭፍን የማንነት ወጥመድ በመግባት እጅግ ሲጨቃጨቁ እያዬን ነው። ይህ ወያኔ ያሳደረው የፍርሃት መንፈስ ወይም በእንግሊዝኛው ሲይንድሮም (syndrome) መሆኑ ነው። እኔ አማራ ቅንጅት ስለሆንሁ አቶ ለማ  ደግሞ ኦሮሞ  አኦህዴድ ስለሆኑ በመካከላችን  የፖለቲካ እምነት ልዩነትና የቋንቋ እንጂ ምንም የኢትዮጵያዊነት ልዩነት የለም። አቶ ለማ እኔ የያዝሁትን የፖለቲካ እምነት የ”አንድነት” ጥሪ ደወል ከእኔ ተቀብለው ደወል ማሰማት ከጀመሩ በፖለቲካችን ተስማማን ማለት ነው። በመካከላችን ችገር የፈጠረው ቋንቋችን ሳይሆን የፖለቲካ እምነታችን ልዩነት ነው። ስለዚህ ኦሮሞው ለማ መገርሳ የወያኔን ከፋፋይ ፖለቲካ አራግፈው ጥለው ወደ አንድነቱ ከመጡ የኔ የአማራው ጠቅላይ ሚንስትር ቢሆኑ አይከፋኝም።

አንዳንድ የወያኔ ፖለቲካ ለዘለዓለም እንዲቀጥል የሚመኙ በአንዳንድ የኦህዴድና የብአዴን መብት ተከራካሪ መሪዎች ላይ የስድብ ናዳ ሲያወርዱ እያዬን ነው። ወያኔን ለሚቃወም፤ የወያኔ የበላይነት አለ ብሎ ለሚናገር  ካድሬ ፤ስድብ ምርቃቱ እንዴት ይሆናል? እንዚህን ለድርጅታቸው ልእልና እዬሞገቱ ያሉትን ፤ወጣ ወጣ እያሉ ያሉትን ደፋር መሪዎች፤ የወያኔ ደጋፊዎች ቅንጅታዊያን ፤ የቅንጅት መርፌ የወጋቸው በሽተኞች ናቸው እያሏቸው ነው። የወያኔ ደጋፊዎች ሽንፈት ሲገጥማቸው የሚያስለፈልፋቸው ነገር የቅንጅት መንፈስ ነው። ምን አይነት መንፈስ? አዎ የቅንጅት መንፈስ ደዌን ያነጻል። የዘረኝነት ደዌን። የቅንጅት መንፈስ የአንድነት፤ የፍቅር ጥሪ ደወል ነው። ስለሆነም እነዚህ አደብ ገዝተው ወደ ህዝብ የወገኑትን ወይም የመጡትን ወገኖች ደዌያቸውን አራግፈው ንስሃቸውን ከተቀበሉ እጃችንን ዘርግተን ልንቀበላቸ ይገባል ወግን ናቸውና። ወያኔዎች አቅም ካገኙ መስደብ ብቻ ሳይሆን ወደ መግደልም ይሄዳሉ። እኛም ለውጥ ፈላጊዎች ደግሞ አይናችንን ጨፍነን መቃወም የለብንም። ግትር መሆን የለብንም። ነገሮች በፍጥነት ሲለዋወጡ መረዳት አለብን። ችግሮቻችን እጅግ ብዙና ጥልቅ ናቸው። የጉዞ መጀመሪያው አንድ ርምጃ ነው። አንድ ርምጃ አይተናል እስኪ ስራችንን እየሰራን ነቅተን እንከታተል። በአንድ ለሊት ሁሉም ነገር አይቀረፍም። ግዜ ለኩሉ ኩሙ ብሏል ጠቢቡ።

መልካም ሰንበት!!!
እንስማው ሐረጉ