ጥቅል ሃሳብ

————–
የሞተዉ ወገን መከፋት ሲገባዉ ሞትህ በመነገሩ ለምን ትንፍሽ ትላለህ ብሎ ሰዉን መዉቀስ አስደማሚ ነዉ። ገዳይ እና አስገዳይን መዉቀስ እና መገሰጽ ቢቻልም ተባብሮ ለፍርድ ማቅረብ ሲገባ ለምን የሞተዉ ሰዉ ተገደለ ብለህ ትናገራለህ ብሎ ስለፍትህ የሚጮህን ሰዉ መክሰስ አስደናቂ ብቻ ሳይሆን በአለም ላይ የመጨረሻዉ የግፍ ግፍ ነዉ። አማራ ህዝብ ላይ ከሚደረገዉ የግድያ ወንጀል የበለጠዉ ግፍ ለምን የአማራ ህዝብ ሞት ተዘገበ ብሎ በድፍረት መናገር ነዉ።
———————-

ሰሞኑን ከማስተዉላቸዉ አስገራሚ ነገሮች የአማራ ህዝብ በየቦታዉ ሲታረድ ለምን ታረደ፣ ተገደለ፣ እያላችሁ ትዘግባላችሁ የሚል ነዉ። በተለይም ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋዉ ጊዜዉን ሰጥቶ የአማራን ህዝብ በየቦታዉ መታረድ እና መገደል እየዘገበ ሰነበተ። እናም ዘይገርም የሚባለዉ ነገር የሚከተለዉ ታዲያ ይሄኔ ነዉ።

የአማራ ህዝብ ሞቱ መዘገቡ ዘረኝነት ነዉ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት ነዉ የሚል ትችት በብዛት ይደመጣሉ። የአንድ ህዝብ መገደል፣ መታረድ እና መሰደድ አለመዘገቡ ለሀገር አንድነት ፍቱን መድሃኒት እንዴት ሊሆን እንደሚችል ደጋግሜ ባስበዉም ጠብ የሚል ምክንያት አላገኘሁም።

በኢልባቦራ ቤቶቻቸውንና ንብረቶቻቻቸው ከተቃጠሉባቸው የአማራ እናቶች አንዷ

የዛሬ አራት እና አምስት አመት በአንድ ቀን ግማሽ ሚሊዮን አማራ ከጉራ ፋርዳ ሲባረር እና ሲገደል አንድ ሽህ ገጽ መረጃ አዘጋጅተን የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ነጻ ነን የሚሉ ሀሰተኛ ነጻ ሚዲያዎች መግለጫ እንዲያወጡበት አሰራጭተን ነበር። ሁሉም በአንድ ድምጽ የተነጋገሩ እስኪመስል ጸጥ ብለዉ ነበር። መኢአድ፣ ሰማያዊ ፓርቲ እና ከግል ጋዜጦች ደግሞ በተመስገን ደሳለኝ የሚመራዉ ጋዜጣ ብቻ መግለጫ አወጡ። ሌላዉ ቀርቶ በዉጭ መንግስታት የሚንቀሳቀሱ የሬዲዮ ጣቢያዎች እንኳን ተፈናቃዮች እንዲያነጋግሯቸዉ ሲጠየቁ እስከ ሶስት ሽህ ብር ክፍያ እንደጠየቁ ትዝ ይለኛል። ተፈናቃይ እና ተሳዳጅ ወገንህን ሶስት ሽህ ብር ስትከፍለኝ ነዉ ሞትህን እና ብሶትህን እምዘግብልህ ማለት መሆኑ ነዉ። እንዲህ ያደረጉ ጋዜጠኞችን ዝርዝር አስተማማኝ ቀን እና ሁኔታ ሲመጣ በወንጀል መክሰስ ተገቢ መሆኑን ግን በልባችን ዘግበንዋል። በህዝባችን ጉዳይስ እጅግ ቂመኞች ነን። በህዝባችን ላይ የስድብ ቃል የተናገረ ሁሉ በልባችን እያንዳንዷን ቃል እንድምንከትባት ሊያዉቅም ላያዉቅም ይችል ይሆናል።

ከሁሉም በወቅቱ እስካሁን የሚገርመኝ ነገር አንድነት የሚባለዉን ፓርቲ ስለ አማራ ህዝብ መግለጫ እንዲያወጣ ሲጠዬቅ መግለጫ አላወጣም ሲል የሰጠዉ መልስ ነበር። እኔም አንዳንድ የፓርቲዉ አባላትን ለምንድን ነዉ መግለጫ የማታወጡት የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር። የሰጡኝ መልስ ደግሞ ይበልጥ አስደማሚ ነበር። ከሰጡኝ መልስ ዉስጥ ታዲያ አንድነት የአማራ ፓርቲ እንዲባል አንፈልግም የሚል መልስ ነበር። እኛም ስለ አማራ ህዝብ ሞት መግለጫ ማዉጣት እንዴት አድርጎ ነዉ የአማራ ፓርቲ የሚያስብላችሁ የሚል ጥያቄ አቅርበን ነበር። በወቅቱ እነ አስራት አብርሃም ከአረና ፓርቲ ወጥተዉ ወደ አንድነት ፓርቲ እንዲገቡ እግዚዮታ ተይዞ ነበር። እናም የአማራ ሞቱ በአንድነት ፓርቲ በኩል መዘገቡ እነ አስራት አብርሃምን እንዳያስቀይም ተብሎ እነ ስዬን አብርሃን እንዳያስቀይም ተብሎ አንዘግብም ሲባል ነበር። ግን እዉን የአማራ ህዝብ የትግራይ ፖለቲከኞችን እና ምሁራንን እንዲህ በጥልቅ ጠላትነት እንዲፈርጁት የሚያበቃ በደል አድርሶባቸዉ ይሆን? እኔ እንጃ። እኔ ትግሬ ስላልሆንኩ በነዚህ የትግራይ ፖለቲከኞች እና ምሁራን ቦታ ሆኜ ምንም መናገር አልችልም። ሆኖም የልባቸዉ ጭካኔ እና ጥጣሬ ግን ሁሌም ያስገርመኛል። እጅግ በጥልቁ።ከትግራይ ፖለቲከኞች በላይ የሚያስደምመኝ ግን አስራት አብርሃም እንዳይቀዬም ብለዉ የአስራት አብርሃምን ወዳጅነት ለማትረፍ ሲሉ የአማራን ሞቱን አንዘግብም የሚሉት የአማራ ፖለቲከኞች ናቸዉ። የነዚህኞቹ ጉዳይ ደግሞ እራሱን የቻለ አንድ መጽሃፍ ይወጣዋል።

አማራ ከታረደ እና ከተፈናቀለ ከአመት እና ከሁለት አመት ብኋላ ግን የአንድነት ፓርቲ የአማራ ፖለቲካ አትራፊ መሆኑን ሲያዉቅ የመግለጫ ጋጋታ ማዉጣት ጀመረ። በስሜት ከመግለብለብ የዘለለ እዉነታዎችን አጣርቶ ማዬት የማይችለዉ ዲያስፖራም …… እዚህ ጋ ነገር ልቁረጥ መሰለኝ። ሃሃሃ…. አዎን ቆረጥቁት።

እናም ለመተዛዘብብ ያበቃን ዘንድ ሰሞኑን ሶስት የትግራይ ሰዎች በወለጋ ተጎዱ ተባለ።እናም እነ አስራት አብርሃም በንዴት ግለሰባዊ እና የፓርቲ መግለጫ ጋጋታ ማዉጣት ጀመሩ። ግማሽ ሚሊዮን አማራ ሲታረድ፣ ሲገፋ እና ሲገደል መግለጫ ማዉጣት እንደ ነዉር ሲቆጥር የነበረ እንዲሁም አስራት እንዳይቀዬም የአማራ ሞቱ አይዘገብለት ሲባልለት የነበረ ሰዉ የሶስት ሰዉ መጎዳት ግን ወደ መግለጫ እንዲገባ አስገድዶታል። የትግራይ ሰዉ ተጎዳ፣ ተገደለ፣ ተሰደድ ሲልም ምሬቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ አቅርቧል። እኔም ንጹህ የሆነ የትግራይ ሰዉ አንድም እንኳን እንዲጎዳ አልፈልግም። በፖለቲካዉ ዉስጥ የሌለ ንጹህ የትግራይ ሰዉ በምንም መልኩ መገደል የለበትም።ምን በወጣዉ?

ሆኖም ምንም የማያዉቀዉ እና ንጹሁ ግማሽ ሚሊዮን አማራ ሲገደል እና ሲሰደድ አትዘግቡ: መግለጫ አታዉጡ ሲል የነበረ ሰዉ የሶስት ሰዉ ሞት ወደ መግለጫ እንዲያመራ እንዴት ሊያስገድደዉ ይችላል? የዘር ነገር ነዋ። ይሁን ዘሩን ይዉደድ።ግን ኢትዮጵያዉያን ሁሉ አንዱ ሲጎዳ አንዱ ስለሌላዉ ለመጮህ እንዲህ ልቡ የጨከነዉ እንዴት ነዉ?

በተለይም አስገራሚዉ ነገር የሚከሰተዉ በአማራ ጉዳይ ላይ ሲሆን ነዉ። የአማራ ሞቱ ሲዘገብ ወንጀል ነዉ። አማራ ሲገደል አማራ ሞተ ማለት ወንጀል ነዉ።አማራ ተፈናቀለ ማለት የኢትዮጵያን አንድነት ያናጋል የሚል ሀሰተኛ ማላዘን ይከሰታል።

ለምታስተዉሉ ሰዎች እኔ ግን እንዲህ እላለሁ። ኢትዮጵያ የእግዚአብሄር ሀገር ነች። እግዚአብሄር የሚወደዉ ህዝብ ነዉ ስንል ደግሞ እያንዳንዱን ሰዉ ነዉ። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሲታረድ ሲገደል: ሲፈናቀል መግለጫ ሊወጣለት ይገባል። አማራም ቢሆን፣ ኦሮሞም ቢሆን፣ ትግሬም ቢሆን ሶማሌም ቢሆን ወይም ከኢትዮጵያዉያን ወይም ከሰዉ ዘር ዉስጥ አንዱ ሰዉ በማንነቱ እና ያለወንጀሉ ሲጎዳ ዜና ሊሰራለት እና ሞቱም ለአዳም ልጆች ሊነገርለት ለሰበአዊ እርዳታም ወገኖቹ እንዲደርሱለት ጥሪ ሊቀርብለት ይገባል። መበደሉ እና መገፋቱ በዝርዝር ሊነገርለት ይገባል።በስፋት ሊዘገብለት ይገባል። እንዲህ የሚያደርጉ የህዝብን እና የሰዎችን በደል የሚዘግቡም ሰዎችም ሊመሰገኑ ይገባል። የእግዚአብሄር ህዝብ የሆነዉን ኢትዮጵያዊ የሚያገለግሉ ተብለዉም ሊሞገሱ ይገባ ነበር።

ነገሩ ወደ አማራ ህዝብ ሲመጣ ግን አስደማሚ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ አርምሞ ዉስጥ ይከታል። ሁሉም ሚዲያ ስለ አማራ ህዝብ ላለመዘገብ: መጽሃፍ ላለመጻፍ በወሰነበት ወቅት የአማራን ህዝብ መከራ በመጽሃፍ አዘጋጅቶ እንዲሁም ሚዲያ አቋቁሞ ህዝቡ ላይ እየተደረገ ያለዉን ግፍና መከራ ለመዘገብ ደፋ ቀና የሚል አንድ ሰዉ ድንገት ብቅ ቢል በዚህ ሰዉ ላይ ዉግዘቱ ለጉድ ቀጥሏል። የሚያስደንቀዉ ዉግዘቱን የሚያዘንቡበት ደግሞ እራሳቸዉ አማራ ነን የሚሉት ጭምር መሆናቸዉ ነዉ።ለምን የአማራን ሞት ዘገብክ። ዘረኛ ነህ።አማራ ሲታረድ ዝም በል።ምን አገባህ።የወያኔ ቅጥረኛ ነህ። በማለት ጋዜጠኛ ሙሉቀንን መከራዉን ያበሉታል።

የሞተዉ ወገን መከፋት ሲገባዉ ሞትህ በመነገሩ ለምን ትንፍሽ ትላለህ ብሎ ሰዉን መዉቀስ አስደማሚ ነዉ። ገዳይ እና አስገዳይን መዉቀስ እና መገሰጽ ቢቻልም ተባብሮ ለፍርድ ማቅረብ ሲገባ ለምን የሞተዉ ሰዉ ተገደለ ብለህ ትናገራለህ ብሎ ስለፍትህ የሚጮህን ሰዉ መክሰስ አስደናቂ ብቻ ሳይሆን በአለም ላይ የመጨረሻዉ የግፍ ግፍ ነዉ። አማራ ህዝብ ላይ ከሚደረገዉ የግድያ ወንጀል የበለጠዉ ግፍ ለምን የአማራ ህዝብ ሞት ተዘገበ ብሎ በድፍረት መናገር ነዉ።

ይሄን ሁሉ አስተዉዬ ወደ ጥልቅ አርምሞ እገባና ኢትዮጵያዉያኖች መካከል እዉነት እና ሀሰት፣ ግፍና ፍትህ፣ ሰበአዊነት እና ኢሰበአዊነት እንዴት እንደሚመዘን በማንሰላሰል ዝምታን እመርጣለሁ። ዝምታ ግን ምንም አይፈይድም። ዝምታ እዉቀትም ለወገን አያካፍልም። እናም እዉነትን እና እዉቀትን ለመመርመር ለምትተጉ ወገኖቼ ቢያንስ ጥያቄ ላቅርብላችሁ። የአማራ ህዝብ ሞቱ ሲዘገብ እንዴት ሆኖ ነዉ ወንጀል የሚሆነዉ? ጋዜጠኛ ሙሉቀንስ የአማራን ሞቱን በመዘገቡ ወንጀሉ ምንድን ነዉ? እንዴት ሆኖ ነዉ ዘረኝነት የሚሆነዉ? በምን መልክስ ነዉ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋዉ? የኢትዮጵያ አንድነት ሲባልስ ምን ማለት ነዉ? አንዱን በሞቱ እንኳን እንዳይተነፍስ ማፈን ሌላዉን በአንቀልባ ማንዘልዘል ማለት ነዉ?

ሃሃሃ…ድከም ብሎኝ ነዉ ለካ።ማንም ይሄን ጥያቄ የሚመልስልኝ የለም።ግን ጥያቄ መጥዬቅ ለተጋ መልስ ባይሆንም ለእዉቀት ፍንትዉታ መነሻ ሊሆን ይችላል ብዬ ይሄን ጥያቄ አቀርብሁላችሁ።