November 5, 2017 07:45

 

የሚሊዮኖች ድምጽ
የአንድነት ሃይሉ የበለጠ እየተሰባሰበ ነው። የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራርሮች መደበኛ አባላት ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ለመቀላቀል ወሰኑ። የአንድነት ፓርቲ በሕወሃት የፖለቲካ ዉሳኔ የምርጫ ቦርድ እውቅናውን ከተነፈገ በኋላ፣ አባላቱና አመራሩ የተወሰኑት ከሁለት አመታት በፊት ሰማያዊን የተቀላቀሉ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን በፓርቲ ማእቀፍ ሳይታቀፉ ቆይተው ነበር።

ሆኖም ዛሬ በመኢአድ ጽ/ቤት ባደረጉት ስብሰባ፣ አዲስ ድርጅት ከማቋቋም ያሉትን በማጠናከርና ከነርሱ ጋር በመስራት ትግሉን እንቀጥላለን በሚል የሰማያዊ ፓርቲ ለመቀላቀል በሙሉ ድምጽ ወሰነዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ና መኢአድ ለመዋሃድ የዉህደት ኮሚቴ አቋቁመው በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል። የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አባላትና ደጋፊዎች ይሄንን ስብስብ ከተቀላቀሉ፣ አገር ቤት ያሉ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው የአንድነት ሃይሎች ተሰባሰቡ እንደማለት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ትግል መዉደቅ መነሳት ያለበት ነው። በተለይም አገራችን አሁን ባልችበት ትልቅ ፈታና ፣ የዘር ፖለቲካው ብዙ ወገኖቻችን ለሕልፈትና ለመፈናቀል እየዳረገ ባለበት ሁኔታ የአንድነት ሃይሉ መሰባሰቡ፣ ኢትዮጵያዉያንን ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ በስብእና በኢትዮጵያዊነት ብቻ ማደራጀቱ ብቸኛ የሌለው ለአገር መፍትሄ የሚሆን አማራጭ ነው።