6 November 2017

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር ሼክ መሐመድ አል አሙዲ በሳዑዲ ዓረቢያ በተጀመረው ፀረ ሙስና ዘመቻ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አንዱ መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ ሼኩ በአሁኑ ጊዜ በሳዑዲ ዓረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በሚገኘው ታዋቂው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል በቁም እስር ላይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር ከውስጥ አዋቂ ምንጮች እንዳረጋገጠው፣ ከቤተሰቦቻቸው መካከል ከአንደኛው ጋር ብቻ በሆቴሉ ስልክ እንደሚገናኙ ታውቋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያን ፀረ ሙስና ዘመቻ እንደሚመሩ የተነገረላቸው የአገሪቱ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ተወካዮች፣ በቁም እስር ላይ ከሚገኙት የመንግሥት ባለሥልጣናትና ታዋቂ የንግድና ኢንቨስትመንት ሰዎች ጋር እየተደራደሩ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የድርድሩ ዓላማ በውል ባይታወቅም፣ ሼክ አል አሙዲም የድርድሩ ተሳታፊ መሆናቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የቁም እስረኛ ያደረጋቸውን ሰዎች በተለያዩ ሥፍራዎች የሚገኙ ሀብቶችና ኢንቨስትመንቶች እንዲታገዱ መጠየቁ በተለያዩ ሚዲያዎች ተሰምቷል፡፡ ሼክ አል አሙዲ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሏቸው ኢንቨስትመንቶች ለ50 ሺሕ ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከመንግሥት ቀጥሎ ትልቁ የሥራ ዕድል ፈጣሪ ባለሀብትም አድርጓቸዋል፡፡ የእሳቸው በቁጥጥር ሥር መዋል ከተሰማ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መደናገርና መደናገጥ ተፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው የሚድሮክ ኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊዎች ግራ መጋባታቸውን ከመግለጽ ውጪ፣ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ቀረብ ያለ መረጃ ያላቸው የውስጥ አዋቂ ምንጮች ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር የሚደረገው ድርድር ተስፋ ሰጪ ነው እያሉ ነው፡፡

ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 .. የዳሸን ባንክ ባለ 21 ፎቅ ሕንፃ ሲመረቅ ሺክ አል አሙዲ እንደሚገኙ ቢጠበቅም፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ መውጣት ባለመቻላቸው ምክንያት ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

ሰሞኑን የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት 11 ልዑላንንና 38 ታዋቂ ባለሀብቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይታወሳል፡፡  ሁሉም የሚገኙት ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ውስጥ ነው፡፡