በለንደን የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ

በቅርቡ ተማሪዎች በአስመራ ከተማ ያካሄዱትን የተቃውሞ ሰልፍ በመደገፍና መንግስት የወሰደውን የማሰር እርምጃ በማውገዝ፤ በለንደን የሚገኙ ኤርትራዊያን ለተቃውሞ ሰልፍ ወጡ።

ባለፈው ቅዳሜ ሕዳር 25 ቀን 2010 ዓ/ም በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅሕፈት ቤት ፊት ለፊት በመገኘት ተቃውሟቸውን ያሰሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያኑ ስደተኞች፤ የኤርትራ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ የሚያካሂደውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆምና የታሰሩ የሃይማኖት መሪዎችና ዜጎች በኣስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የዜጎች መብት እንዲከበርም ሰልፈኞቹ ኣሳስበዋል።

የኤርትራውያን ሴቶች ኔትዎርክ አስተባበሪ ወይዘሮ ከድጃ ዓሊ መሀመድ ኑር ለቢቢሲ እንደገለፁት የ93 ዕድሜ ባለፀጋ አዛውንት ሙሳ መሀመድ ኑር ከታሰሩ በኋላ ነው ተቃውሞዎች የተጋጋሉት ” ስርዓቱ በተኩስና በጉልበት ተቃውሟችንን ሊቀለብሰው በመሞከሩ ነው ለሰልፍ የወጣነው” ብለዋል።

“ትምህርት፣ሀሳብንም መግለፅም፣ እምነትና ተቃውሞ ሁሉም ሰብአዊ መብቶች ናቸው። ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት ይሄው ነው” ብለዋል።

መንግስት ባለፈው ሳምንት በዲያእ አልእስላምያ ትምህርት ቤት የመንግስትጣልቃ ገብነትን የተቃወሙትን አባት ማሰሩን ተከትሎ በአስመራ የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል። ይሄንንም ተከትሎ መንግስት በሰልፉ ተሳተፈዋል ያላቸውን ወጣቶችና ለእስር ዳርጓል።

በ1993 ዓ/ም ዲያእ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩትና በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉት አቶ ብርሃኑ መሀመድ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች ግብረ ገብነት ከማስተማርም ጭምር፤ በኣካዳሚ ትምህርትም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑ ይነገራል።

ሌላ በሰልፉ የተገኙት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ቄስ ሺኖዳ በተቃውሞ ሰልፍ ለተሳተፉትት ሰልፈኞች በኣረብኛና በትግርኛና ንግግር አሰምተዋል።

“የኤርትራ መንግስት እየገፋንና የእምነት ነፃነታችን ከነጠቀን ቆይቷል። እስላምና ክርስትያን ሳንል ፈጣሪ የስቃያችንን ጊዜ እንዲያሳጥረው መፀለይ አለብን” ብለዋል።

በተጨማሪም የኤርትራ መንግስት የተማሪዎቹ ተቃውሞ በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ብቻ የተደረገ እንደሆነ ለማስመሰል እያደረገው ያለው ጥረት ትክክል እንዳልሆነ ህዝቡ ጠንቅቆ እንዲያውቅም አስረድተዋል።

ከሊድስ ከተማ የመጡት አንዋር መሀመድ በበኩላቸው “መንግስት ባለፈው ጊዜ የኦርቶዶክስ ጳጰስን አስሯል። በእስልምና ላይም የተነሳው የማፈን ዘመቻ የመጀመርያው አይደለም። ለዚህም ነው ድምፃችን ማሰማት የፈለግነው” ብለዋል።

ሌላ በሰልፉ የተሳተፉ እናት በበኩላቸው “ስርአት ያልፋል፤ ህዝብ ግን ዘላለማዊ ነው። ሳንለያይ ሙስሊሙም ክርስትያኑም ከመቼም ጊዜ በበለጠ ዛሬ መደጋገፍ አለበት” ብለዋል።

የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪ የኤርትራውያን ሕብረት አባል የሆኑት ኣቶ ጳውሎስ መንግስተአብ ሚካኤል በበኩላቸው “ኤርትራውያን ሙስሊምም ሆንን ክርስትያን አንድ ነን የሚለየን የለም” ብለዋል።

“ህዝባችን የስርአቱ አምባገነንነት አንገሽግሾት በመቃወም ላይ ነው ያለው፤መንግስት የአንዲት ትምህርት ቤት ጉዳይ አድርጎ መመልከቱ ተገቢ ኣይደለም” ብለዋል።

እያንዳንዱ ኤርትራዊ ካለበት ሆኖ የተጀመረውን አመፅ ማቀጣጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ይህንን ሰልፍ ከመካሄዱ አንድ ቀን በፊትም በለንደን የሚኖሩ ኤርትራዊያን በኤርትራ ኤምባሲ ተገኝተው የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

በተመሳሳይም በስዊድን፣ በአሜሪካ፣አውስትራልያና በግብፅ እና ሌሎች አከባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።