November 7, 2017 02:08

በወንድወሰን ተክሉ

በሰሜን ጎንደር በተለይም በአይከል ከተማ በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት በከተማዋና አካባቢዋ ውጥረት መንገሱ ተነገረ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄን እመልሳለሁ በማለት ባለፈው መስከረም ወር በስምንት ቀበሌዎች ውስጥ ሕዝበ ውሳኔን ያካሄደው ህወሃት መራሹ መንግስት በ7ቱ ቀበሌዎች ከተሸነፈም በሃላ በጉዳዩ ተስፋ ባለመቁረጥ የአይከልን ከተማ የቅማንት ዞን ዋና ከተማ ትሁን ብሎ በመወሰኑ ለህዝባዊው ተቃውሞና ለውጥረቱ መከሰት መንስኤ እንደሆነ ነው ማወቅ የተቻለው።

ከባለፈው ሐሙስ ጀምሮ ከትግራይ ክልልና ከፌዴራሉ የደህንነት ቢሮ የተላኩ ሃላፊዎች በአይከል ከተማ በመገኘት ሕዝቡን ከተማዋን እንደ የቅማንት ዋና ከተማነት እንዲቀበል ሲያባብሉና ሲያግባቡ ቢቆዩም ቅዳሜ እለት በተካሄደው ስብሰባ የከተማው ህዝባ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ስብሰባውንም ረግጦ እንደወጣ ማወቅ ተችላል።

ከሀይከል ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የያዙት ሙስሊሞች በቅዳሜው ስብሰባ ለባለስልጣናቱ “እኛ አብሮነትን ነው  እንጂ ብቸኝነትን አይደለም “በማለት የሀይከል ከተማን የቅማንት ዞን ዋና ከተማነት እንደማይመርጡ በመግለጽ ስብሰባውን በትነው እንደወጡ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

የትግራይ ክልል ባለስልጣናትና የህወሃት  ድርጅት ከያዙት የአማራን ለም መሬት የመቆጣጠር የረጅም ግዜ ዓላማን ለመፈጸም የቅማንትን ስም ይዘው እንደመጡ ነዋሪው እየተናገረ ሲሆን በሪፈረንደሙ ላይ ባልተካፈሉት አራቱ ቀበሌዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃንም ለአብነት በመጥቀስ ድርጊቱን ለቅማንት ተቆርቃሪነት ሳይሆን የታላቋ ትግራይ ምስረታን ከማለም ሲሉ ይገልጻሉ።

በባለፈው ሪፈረደም ላይ አራቱ ቀበሌዎች ከተቀሩት ስምንት ቀበሌዎች ጋር ሆነን በምርጫው የምንሳተፍበት ምክንያት የለም በማለትና አብሮነትን የመረጡ ሆነው ሳለ በቅርቡ ግን ከአራቱ ቀበሌዎች ውስጥ ሁለቱን በቅማንት አስተዳደር ስር ሆናችሃል መባላቸው ይታወሳል።

በሪፈረንደም ያልተካፈሉትን ሁለቱን ቀበሌዎች በግድ በቅማንት አስተዳደር ስር ሆናችሃል ያላቸው ስርዓት ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የሀይክልን ከተማ የቅማንት ዞን ዋና ከተማ ናት ብሎ ያወጀ ቢሆንም የከተማዋ ነዋሪ ግን ሀሳቡንና ውሳኔውን በማውገዛቸው የተነሳ ውጥረቱን እንዳባባሰ ነው መረዳት የተቻለው።

ከክልልና ከፌዴራል የሄዱት ባለስልጣናት ይህንን የነዋሪውን ውሳኔ እና ፍላጎት በመረዳት ዓላማቸውን በሃይል ለማስፈጸም በህዝቡ መከካል ግጭት እንዲፈጠር አሲራዋልና ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉም ነዋሪዎች ሴራውንም ይናገራሉ።

ዋና ጽ/ቤቱን በትግራይ ሽሬና መቀሌ ያደረገው የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ አስመላሽ ቡድን የቅማንት ህዝብ ከአማራው ጋር አንድነት የማይታይበትና ልዩ የሆነ ህዝብ ነው በማለት ከመቶ በላይ ቀበሌዎች የቅማንት ልዩ ዞን ተብሎ ይከለል በማለት የተነሳ ቢሆንም በ42ት ቀበሌዎች እንዲገታና ብሎም በ12ት ቀበሌዎች ላይ ደግም ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህንንም ውሳኔ 4ቱ ቀበሌዎች አያስፈልገንም በሚል ጽኑ ውሳኔ ያልተሳተፉበት ሲሆን ስምንቱ ግን ባደረጉት ምርጫ ሰባቱ አብሮነትን መምረጣቸው ታውቃል።

የአማራን ሕዝብ ለመምታት፣ለማዳካምና ብሎም ከጎረቤት ሱዳን ጋር በድንበር እንዳይዋሰን ለማድረግ የቅማንትን ስም ይዞ መሬታችንን ህወት ያለ አግባብ ልትቀማን ነው ሲሉ የአከባቢው ነዋሪዎች በስፋት ይናገራሉ።

በዚህም መስረት ቅዳሜ እለት በፌዴራል እና ክልል ባለስልጣናት ሰብሳቢነት የተሰበሰበው የአይከል ከተማ ነዋሪ ከተማዋ የቅማንት ዞን ዋና ከተማነት ተመርጣለች ተብሎ ሲነገረው ውሳኔውን በማውገዝና ብሎም ስብሰባውን በትኖ በመውጣት ተቃውሞውን ያሳየ ሲሆን በማግስቱም የፌዴራል ባለስልጣናት በየቤቱ እየዞሩ ከማስፈራራትና ለማስፈረም ከመሞከር በተጨማሪ በህዝቡ ውስጥ ግጭት ለመፍጠር ሲጥሩ ታይተዋል ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ።