እነ አቶ ለማ የፍቅርና የአንድነት!” ጉባኤ ያሉትን ጉባኤ ለማድረግ ወደ ባሕር ዳር ሲያቀኑ በመጽሐፈ ገጼ ላይ (ፌስ ቡክ) የሚከተለውን ሐሳብ አሰፈርኩ፦

የፍቅርና የአንድነት ጉባኤ???

እነ አቶ ለማ መገርሳ የፍቅርና የአንድነት ጉባኤ ለማድረግ ወደ ባሕር ዳር ከማቅናታቸው በፊት ሐሰተኛ ታሪክ ፈጥረው በኦሮሞ ሕዝብ ልብ የአማራ ቂምና ጥላቻ ለመፍጠር የገነቡትን ዘግናኝ የጥላቻ ሐውልት ይቅርታ ጠይቀው ማፍረስ ነበረባቸው!!! ይሄንን ሳያደርጉ የፍቅርና የአንድነት ጉባኤ!” የሚሉትን ነገር ለመታደም ባሕር ዳር መጓዛቸው የለበጣ ወይም የማስመሰል መሆኑን ያሳያል፡፡ እራሳቸውን ብቻ ካልሆነ በስተቀር በዚህ ተግባራቸው ሕዝብን ማታለል እንደማይችሉ ሊያውቁ ይገባል….!” በማለት፡፡

በእርግጥም ይህ የፍቅርና የአንድነት ጉባኤ ከልብ ከሆነ እንዲፈጸም የተፈለገው አስቀድሞ ወያኔ በጭንቅላታቸው ሲገነባው የቆየው ጥላቻ ለረጅም ጊዜ የቆየ ቢሆንም እነ አቶ ለማ መገርሳ ፍቅርና አንድነት እንደሚበልጥ እንደሚሻል አውቀውና አምነው የፍቅርና የአንድነት ጉባኤ ለማድረግ ወደ ባሕር ዳር ከተጓዙ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ወደ ባሕር ዳር ለመጓዝ የመጀመሪያዋን እርምጃ ሲጓዙ ገና ከውስጣቸው ተገንብቶ የነበረው የጥላቻ ግንብ ተንዷል ፈራርሷል፡፡ ስለሆነም የአኖሌንና የጨለንቆን ሐሰተኛ የጥላቻ ሐውልት ለማፍረስ ቅንጣት አይቸገሩም፣ ሰው እስኪያሳስባቸውም አይመብቁም ነበረ፡፡

ነገር ግን ይህ ጉዞ የይስሙላና ቀጥሎ በምገልጽላቹህ ዓላማ ምክንያት ወያኔ ያዘጋጀው በመሆኑ ሰላም ፍቅርና አንድነትን ለመመሥረት ወሳኝ እርምጃ የሆነውን የአኖሌን ሐሰተኛ ቂምና ጥላቻ ፈጣሪን ሐውልት ማፍረሱና ይቅርታ መጠየቁም አልታያቸውም አይፈልጉምም፡፡ አጀንዳው (ርእሰ ጉዳዩ) ራሱ የኦሮሞ ሕዝብንና የአማራን ሕዝብ የሚመለከት አይደለም፡፡ በሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ በኦሮሞ እና በአማራ ሕዝብ መሀከል ችግር የለም አልነበረምም፡፡ ችግሩ ያለውና ችግሩን የሕዝብ ለሕዝብ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ያሉት ወያኔ፣ ሸአቢያ፣ ኦነግ፣ ኦሕዴድና ብአዴን ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህ የፍቅርና የአንድነት የሚለው ጉዳይ በወያኔ/ኦሕዴድ/ብአዴን እና በአማራ ሕዝብ መሀከል ሊደረግ የሚገባው እንደሆነ ወይም መሆን እንዳለበት ነው እኔን የሚሰማኝ፡፡ እየሆነ ያለው ግን በወያኔ ትዕዛዝ በኦሕዴድ እና በብአዴን መሀከል ነው፡፡

ኦሕዴዶች እነ አቶ ለማ መገርሳ የፍቅር እና የአንድነት ጉባኤ!” በሚል ተሠይሞ ከብአዴን ጋር እንዲተውኑት በወያኔ የተደረሰላቸውን ድራማ (ትውንተ ኩነት) ለመተወን ባሕር ዳር ከገቡና ትወናውን መተወን ከጀመሩ በኋላ በጣም የሚገራርሙ ቃለ ተውኔቶችን እያሰሙን ይገኛሉ፡፡ ከዓመታት በፊት በአንድ አሁን ርእሱን በማላስታውሰው ጽሑፌ ላይ ወያኔ ከምርጫ 97 ማግስት ባሕር ዳር ላይ አድርጎት በነበረው የኢሕአዴግ ስብሰባ ላይ ዳድቶት የነበረውን ሁኔታ በማስረጃነት በማስታወስ ወያኔ ሥልጣኑን በሕዝባዊ ዐመፅ እንዲለቅ የሚገደድበት ሁኔታ ከተፈጠረ ውጤቱ ከማንም በላይ ለራሱ እንደሚከፋ ስለሚያውቅ ወደ መጨረሻ ይሄንን የአንድነት የፍቅር የኢትዮጵያዊነትን ካርድ (ክርታስ) በመሳብ እድሜውን ለማራዘም እንደሚጥር መግለጤ ይታወሳል፡፡

ይሄው ዛሬ ጊዜው ደረሰና ወያኔ የከፋፍለህ ግዛ የአገዛዝ ስልቱ የአገልግሎት ጊዜ ሲያበቃበት ሌላ አዲስ የመጫወቻ ካርድ (ክርታስ) መዞ ፍቅር አንድነት!” እያለ ሌላ 27 ዓመት ለመግዛት በማሰብ ሒደቱን ሀ ብሎ መጀመሩን ሕልውናየ በሁለቱ አንጋፋ ብሔረሰቦች በአማራ እና በኦሮሞ መለያየት፣ መባላት፣ መናከስ፣ ጠላትነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሁለቱ ከተግባቡ፣ ከተስማሙ፣ ከተፋቀሩ፣ አንድ ከሆኑ እኔ ለመግዛት ፈጽሞ ዕድል አይኖረኝም!” ብሎ ሲያባላቸው የቆዩትን አማራንና ኦሮሞን እርቅ፣ ፍቅርና አንድነት መመሥረት እንዳለባቸው አማራንና ኦሮሞን እንወክላለን በሚሉት አሻንጉሊት አገልጋዮቹ አንደበት በባሕር ዳሩ የአንድነትና የፍቅር ጉባኤ ላይ እንዲያስተጋቡ እያደረገ ይገኛል፡፡

ጉባኤተኞቹ በጉባኤው ላይ ቀድሞ እንደመርገም ጨርቅ ይጠሉትና ይጸየፉት የነበረውን፣ ሊያጠፉትም ብዙ የጣሩበትንና ብርቱ ጉዳት ያደረሱበትን ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን በቻሉትና አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን አጉልተውና አድምቀው ለማስተጋባት ጥረት አድርገዋል፡፡ ወያኔ ጉባኤው የሕዝብ ተአማኒነትንና ተቀባይነትን እንዲያገኝ ለማድረግ በማሰብ ሆን ብሎ የጉባኤውን ቅኝት ፀረ ሕወሓት እንዲመስል አድርጎታል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ በሀገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በኦሕዴድና ብአዴን ባለሥልጣናት ወያኔ እየተወገዘ፣ ጣት እየተጠቆመበት፣ እየተላከከበት ይገኛል፡፡ ይሄም ደግሞ በመንግሥት የብዙኃን መገናኛዎች እየተላለፈና የኢትዮጵያም ሕዝብ እንዲሰማው እየተደረገ ይገኛል፡፡

ይሄንንም ነገር ተከትሎ አንዳንዶች የዋሃን ወገኖች የኦሕዴድና የብአዴን ባለሥልጣናት ይሄንን እያደረጉ ያሉት ሕዝቡ ለችግሮቹ መፍትሔ ያገኘ መስሎ እንዲሰማው በማድረግ የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ ሕዝባዊ እንቢተኝነትና ዐመፅን ለማብረድና ለማክሰም በዚህም ወያኔ ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሆነ ባለመረዳት ኦሕዴድና ብአዴን ይሄንን እያደረጉ ያሉት የወያኔ አገዛዝ እንዳበቃለት ስላወቁ ከሕዝብ ጋር በመወገን እራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን፣ ነጻ ለማድረግ ነው!” እያሉ ይገኛሉ፡፡

እነኝህ ወገኖች ምን የዋሃንና ማገናዘብ ቢርቃቸው ይሄንን ሊሉ ሊያስቡ እንደቻሉ በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ልክ ወያኔ ከሀገር እንደሌለ ወይም ጥሎ እንደወጣ ወይም ጠቅልሎ ትግራይ እንደተከተተና ብአዴንና ኦሕዴድም ከወያኔ ፍጹም ነጻ እንደሆኑ ነው እየተሰማቸው ያለው፡፡ ሌላው ሁሉ ይቅርና በወያኔ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የመንግሥት የብዙኃን መገናኛው እንዴት እነኝህን በወያኔ ላይ ያነጣጠሩ፣ በወያኔ ላይ የሚያላክኩ፣ ወያኔን ጠላት የሚያደርጉ የኦሕዴድ እና የብአዴን ባለሥልጣናት ንግግሮችን ለሕዝብ ሊያስተላልፍ ቻሉ?” ብለው እንኳ እራሳቸውን ቢጠይቁ ይህ ነገር የወያኔ እጅ እንዳለበት፣ ኦሕዴድና ብአዴን ወያኔ የደረሰላቸውን ትውንተ ኩነት (ድራማ) እየተወኑ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት የሚችሉት ጉዳይ በሆነ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ ኩነት) ያሉ ወያኔ የነጻ መረጃ ፍሰት ቀበኞች ይሄንን የኦሕዴድና የብአዴን ወያኔን ከሳሽ፣ ወቃሽ፣ ወንጃይ ንግግሮች እንዲያስተላልፉት ከወያኔ ትዕዛዝ ስለተሰጣቸው እንጅ እንዲህ ዓይነቱን የገዛዘፈ አደገኛ ጉዳይ አይደለም ተራ የግለሰብ ንግግሮችን እንኳ ሳይቀር ነው በቅድመ ምርመራ መነጽራቸው መንጥረው በመፈተሽ የወያኔን ጥቅም የሚጻረር ነገር እንደሌለበት እያረጋገጡ እንዲተላለፍ የሚያደርጉት፡፡

አሳዛኑ ነገር ግን ወያኔ በሚከተለው ሉዓላዊ ሥልጣንን ለማዕከላዊ መንግሥትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ለየጎሳዎችና ለየብሔረሰቦች በሰጠው በአግላዩ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዜግነትን በሚፈጥረው በጎሳ ፌደራሊዝም (ራስገዝ) ሥርዓት መለያየትን፣ ጎጠኝነትንና ጠባብነትን እንጅ ፍቅርን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን መስበክ፣ ማራመድ፣ ማምጣት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑ ነው፡፡ እርግጠኛ ሆኘ ወያኔ እና አጋሮቹ የጀመሩት ይህ ነገር ድራማ (ትውንተ ኩነት) ነው፣ ማስመሰል ነው የምላቹህም ለዚህ ነው፡፡

ወያኔና አጋሮቹ ባሕርዳር ላይ እያስተጋቡት እንዳለው ከልብ የእውነታቸውን የአቋም ለውጥ አድርገው ከሆነና ለማስመሰል ለማታለል ካልሆነ ኢትዮጵያዊነትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን እየሰበኩ እያስተጋቡ ያሉት እንግዲያውስ የሚከተሉት የጎሳ ፌደራሊዝም ሥርዓታቸው ይሄንን ለማድረግ አያስችላቸውምና፣ አይፈቅድላቸውምና በቅድሚያ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይሄንን የአሥተዳደር ዘይቤን መጣል ነው፡፡ ወያኔ ግን ይህ የአሥተዳደር ዘይቤው የህልውና መሠረቱ በመሆኑ መቸም ሊጥለው አይችልም፡፡

በመሆኑም ወገኖቸ እንዲያው እንቅጩን ልንገራቹህ ከወያኔ መቸም ጊዜ ቢሆን በምንም ተአምር ቢሆን መልካም ነገርን አትጠብቁ፡፡ ሰይጣን በቃ ሰይጣን ነው አለቀ፡፡ ለተንኮሉ፣ ለጥፋት ዓላማው፣ እስኪያጠምድ ድረስ ለጊዜው መልአክ ሊመስል ይችላል እንጅ ፈጽሞ መልአክ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዝምብም ማር አይጠበቅም፡፡ ይሄንን አውቀን መበርታቱ ነው የሚበጀን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ የኦሮሞ ጉዳይ ላይ ያገባናል ከሚሉ ጋር በመደራደር እነሱን አግባብቶ ከጎኑ በማሰለፍ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ሰላም፣ ፍቅርና ስምም ለመሆን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሄኛው ከተሳካለት ወያኔ አማራ ላይ እንደመረረ ለመቀጠል ነው እያሰበ ያለው፡፡ ከተሳካለት ያለጥርጥርም ከነበረው በከፋ መልኩ ወያኔና አጋሮቹ በአማራ ላይ ከፍተው የሚመሩ ይሆናል፡፡ ካልተሳካለት ግን ይሄንን የጀመረውን የፍቅርና የአንድነት አስመሳይ ጉዞውን አጠናክሮ የሚገፋበት ይሆናል፡፡

ወያኔ በዚህኛው በፍቅርና አንድነት አስመሳይ ጉዞው የሚገፋበት ከሆነ ቆይ ታያላቹህ ኧረ አንዳንዶቹ እንዲያውም ከወዲሁ ጀምረውታል፡፡ ከዚህ በኋላ በጣም የሚያስቸግሩት እነማን እንደሆኑ ታውቃላቹህ? የሕዝብ አመኔታ ወይም ተቀባይነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ፣ ተቃዋሚ መሆናቸው የሚታወቁ ግለሰቦችም ጭምር ናቸው የሚያስቸግሩን፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ወያኔ እየደለለና እያታለለ የሚያዘምትብን እነኝህን ነው፡፡ በቃ እኛ የምንፈልገው ፍቅርን አንድነትንአይደል?” እያሉ ወያኔ ከየአቅጣጫው ከውጭም ከውስጥም ከገባበት ጭንቅ ለማምለጥ ሲል የሚያደርገው የሚፈጽመው መስሎ የነገራቸውን የማይፈጸም ቃል እያስተጋቡ ሕዝቡ አርፎ እንዲቀመጥ ብሎም ለአገዛዙ ድጋፉን እንዲሰጥ እንዲወተውቱ ማዝመቱን ይቀጥላል፡፡ ተጠንቀቁ! ማንንም ግን እንዳታምኑ እንዳትቀበሉም፡፡ ወያኔ የዚህን ያህል ኃላፊነት የሚሰማው፣ የተጸጸተ፣ ከጥፋቱም መመለስ የሚፈልግ ከሆነ በአስቸኳይ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ይፍቀድና ሥልጣኑን ለሽግግሩ መንግሥት ያስረክብ!!! አለቀ ከዚህ ውጭ ከወያኔ ጋር በምንም ጉዳይ ላይ አንደራደርም! አንስማማምም!!!

ወያኔ በፈጸማቸው ወንጀሎች፣ ግፎች፣ የሀገር ክህደቶች እንዳይጠየቅ ሆኖ፣ የዘረፈውንም ሀብት እንደያዘ ሥልጣን ለመልቀቅ ቢፈልግ ተስማምተን እንሸኘው!” የሚለው እጅግ ያልበሰለ አስተሳሰብ የፍትሕን የበላይነት የሚጻረር አስተሳሰብ ከመሆኑም በላይ ይህ አሁን በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ ያለው የሕወሓትና የትግሬ ኢፍትሐዊ የኢኮኖሚ የበላይነት እንዳለ ይቀጥል!” ማለት ስለሆነ ፈጽሞ አንቀበልም!!! አለቀ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com