November 7, 2017 08:20

 

 

ኢትዮጵያዊነት የራሱና የጋራው በሆኑ ባህሎች፣ ወጎች፣ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ትውፊቶችና ጠንካራ የአብሮነት እሴቶች ጥምረት ድርና ማግ ሆኖ የተሠራ የከበረ ማንነት ነው – ያሬድ ጥበቡ

“የኦሮሞና አማራ የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት”

ሰሞኑን በእነ አቶ ለማ መገርሳ የተመራው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባለስልጣናትና አባገዳዎች ምክር ቤት ወደ አማራ ክልል ባህርዳር ከተማ በመጓዝ ጉብኝት ማድረጋቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ተከታትለናል። ከኦሮሚያ የሄዱ “የልዑካን አባላትን” የአማራ ክልል ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እንደተቀበላቸው የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የልዑካኑ ቡድኑ ጉዞ ሁለቱ የክልል መንግስታት የተለያዩ አገራት አስመስሏቸዋል፣ መነጋገሪያ ሆኖም ሰንብቷል።

ከህወሃት ደጋፊዎች በስተቀር አብዛኞቹ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች በዚህ “ትስስር” ደስታቸውን ቢገልጹም፣ ሁኔታው ይህን ያክል አፅንዖት ሊሰጠው የሚችል መሆን አልነበረበትም። በአማራና በኦሮሚያ ክልል “የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት” የሚለው የኢህአዴግ አዲስ ስትራቴጂ የተጀመረው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደረግ ጥቃት ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።

ህዝብን ከህዝብ የማቀራረብ አጀንዳ የማን ነው?

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የጀመሩት የኢህአዴግ/ህወሃት “ከፋፍለህ ግዛ” አገዛዝ የመረራቸው የአማራና የኦሮሚያ ወጣቶች ናቸው።  ባለፈው አመት በአማራ ክልል በባህርዳር እንዲሁም በጎንደር ከተማ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የእኔ ደም ነው” በሚል ወጣቶች ይዘውት የወጡት መፈክር እንዲሁ በአዳማና በሌሎች ከተሞች በተደረጉ በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ኦሮሞዎች ለአማራ ያሳዩት አጋርነት የአገዛዙን አባላት አስደንግጧል። በጊዜው በሁለቱም ክልል ወጣቶች አማራንና ኦሮሞን የሚያቀራርቡ ሃሳቦች መቅረባቸው በተለይም በህወሃት አባላት ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል። በአማራና በኦሮሚያ ህዝቦች መካከል የታየው አጋርነት ህወሃት በዋነኛነት የሚያቀነቅነው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ችግር እንደገጠመው ግልፅ ሆኗል። በተለይም በኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የአማራ ወጣቶችን የሚያወድሱ ሰልፈኞች መገኘታቸው፣ በኋላም የኦሮሞ ወጣቶች ወደ አማራ ክልል በመሄድ ጣና ሃይቅን የወረረውን አረም ለማስወገድ መዝመታቸው ለህወሃት አባላት ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።

የህወሃት/ ኢህአዴግ አዲስ መዝሙር – ኢትዮጵያዊነት?

ጊዜ የማያሳየው ነገር የለም እና የኢህአዴግ አባላት ስለኢትዮጵያዊነት ሲሰብኩ መስማት ቻልን! አቶ ለማ መገርሳ በተለያዩ ጊዜያት የሚናገሯቸው ንግግሮች ባለፉት 26 አመታት ከየትኛውም የኢትዮጵያ ባለስልጣን ንግግር ያልተሰሙ በኢትዮጵያዊነት ቅላጼ የተዜሙ ሆነው ተገኝተዋል ብል ማጋነን አይሆንብኝም። በተመሳሳይ መልኩም፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ አቶ ንጉሱ ጥላሁንና፣ አቶ አዲሱ አረጋ በተለያዩ ጊዜያት የሚናገሯቸው ኢትዮጵያዊነትን የተላበሱ ንግግሮች በመገናኛ ብዙሃን ሲሰራጩና በኢትዮጵያውያን አድናቆት ሲቸራቸው ታዝበናል። እነዚህ የክልል ባለስልጣናት [የፌዴራል ባለስልጣናት ስለህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሲያወሩ አልሰማሁም] በዚህ ወቅት ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ማዜም እንዲሁም “አንድ ነን፣ አንለያይም” እንዲሉና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር ለምን ፈለጉ የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የክልል ባለስልጣናቱ የኢህአዴግ አባላት እንደመሆናቸው መጠን፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እናጠናክራለን ሲሉ በአባል ድርጅቶች መካከል ተመክሮበት ወይስ በክልል መንግስታት ተነሳሽነት? ይህንን በግንባር ቀደምትነት እየመራና እያስፈጸመ ያለ አካልስ ማን ነው? ኢህአዴግ ወይስ ክልሎች? እንደ ክልል መንግስታት በነጻነት መንቀሳቀስ ይችላሉ ወይስ የፌዴራል መንግስት ጋር ምክክር አድርገው ነው? የሚሉት ጥያቄዎችን ለመመለስ ምናልባትም የኢህአዴግ ሳይሆን የህወሃት አባል (ደህንነት) መሆንን ይጠይቃል። ሆኖም የህወሃት/ኢህአዴግን ታሪክ የምናውቅ ሁሉ አንድ ነገር እንገነዘባለን። ይህም ህወሃት የህዝቡን አጀንዳ በመስረቅ ለራሱ ጥቅም ማዋሉን። ኢትዮጵያዊነትና አንድነት የሚለው ትርክትም ከአማራና ከኦሮሚያ ወጣቶች የተሰረቀ አጀንዳ ነው።

እባቡ የመጨረሻ መርዙን አልተፋም፣ ግን ተዳክሟል?

ህወሃት፣ አቶ መለስ በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ያክል አቋም ባይኖረውም፣ ቢያንስ አሁንም ድረስ መከላከያውን፣ ደህንነቱንና ኢኮኖሚውን፣ ተቆጣጥሮ መገኘቱ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። ሆኖም ለህወሃት አገዛዝ ከፍተኛ ችግር የጋረጡት የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ሳይሆኑ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው። በየጊዜው ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርገው፣ የሚሞተ፣ የሚቆስለው፣ የሚታሰረው ወጣቱ እንጂ፣ የብአዴን ወይም የኦህዴድ ካድሬ አይደለም። አጃቢዎቹ ብዓዴንና ኦህዴድ፣ እንዲሁም ደህዴን እዚህ ግባ የሚባል መዋቅር የሌላቸው ሲሆን፣ በህወሃት ሳንባ የሚተነፍሱ፣ ህወሃት ጠፍጥፎ የሰራቸው ተቀጽላዎች ናቸው። በምንም ሁኔታ ጥርስ አውጥተው ግዙፉን ህወሃትን የሚነክሱበት የህዝብ ድጋፍ፣ የደህንነት መዋቅር፣ የሚተማመኑበት መከላከያ፣ ጉልበትም አቅምም የላቸውም። እነዚህ የክልል ድርጅቶችና አባላት ለራሳቸው ደህንነት የሚፈሩ፣ ይሁንታ ካላገኙ በስተቀር ራሳቸውን ችለው እንኳን መናገር የሚፈሩ ናቸው። ከህወሃት ውጭ የሆኑ የኢህአዴግ አባላት አገልግሎታቸው ለህወሃት ነውና ህወሃት አድርጉ ያላቸውን ድርጊት ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ መታወቅ ይኖርበታል።

ለህወሃት አስቸጋሪ የሆነው ወጣቱ ትውልድ (ቄሮ) ነው። በአሁኑ ሰዓት ወጣቱን የሚይዝበት አጀንዳ ለማግኘት እየዳከረ ያለው ህወሃት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የብሄር ካርድ በመሳብ ሁከት አስነስቶ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት በማድረስ፣ የአገዛዙን እስትንፋስ ለማቆየት እየጣረ ይገኛል። እስካሁን ድረስም ሰላማዊ ተቃውሞ በተነሳበት አካባቢ ሁሉ የብሄር ግጭት በመቀስቀስ እድሜውን ለማስረዘም ሞክሯል። ተሳክቶለታልም። የሚጠቀማቸውም እነዚሁ የብዓዴን፣ ኦህዴድ፣ እንዲሁም አጋር ድርጅቶች አባላትን ነው።

በቅርቡ እንኳን ወያኔ በእጅ አዙር በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ባስነሳው ግጭት ከባድ ጉዳት መድረሱን ሁላችንም ያየነው ነው። ተንኳሾቹም በህወሃት የሚታገዙ የየድርጅቶቹ አባላት ናቸው። የችግሩ ተጠያቂም በህወሃት የሚዘወር ደህንነትና መከላከያ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ድምፅ ተናግሯል። ህወሃት የአማራና የኦሮሞ ብሄር አባላትን በምዕራብ ኢትዮጵያ በማጋጨት ከፍተኛ ዕልቂት እንዲፈጸም የዘየደው ዘዴ አልተሳካለትም። በህዝብ ትብብር ቁሟል። ወያኔ የዘር ፍጅቱ እንዲካሄድ የሚቀሰቅሰው እንደ ዛሚና ኢኤንኤን በመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ነው። በቤኒሻንጉል ክልልም እንዲሁ ህወሃት ሰርጎገቦችን በማሰማራት በአማራ ክልል ብሄረሰቦች ላይ ጉዳት አድርሷል። ህወሃት ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት፣ የስልጣን ዕድሜውን በማስረዘም የተካነበት ቢሆንም፣ በሁሉም ወገን ያለው ህዝብ ስለነቃበት የማተራመሱን አጀንዳ ሳይገፋበት ለጊዜው እንዲቆም አድርጎታል። የመጨረሻ ካርዱን ከመሳቡ በፊት የህዝቡን ቀልብ ይስብልኛል የሚለውን ስትራቴጂ ነድፏል። ይህ ስትራቴጂም አንድነትን የሚሰብከው “የሰላም ምክክር” ነው።

“የሰላም ምክክር” ዓላማ?

የኢህአዴግ/ህወሃት አገዛዝን በመቃወም በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ከተደረገ በኋላ ህወሃት የአማራና የትግራይ ክልል ህዝቦች ግንኙነት በሚል አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የአማራ ክልል ባለስልጣናትና “የአገር ሽማግሌዎችን” በመቀሌ በመጋበዝ “የሰላም ምክክር” ማካሄዱ ይታወሳል። በሚቀጠለው ሌላ ዙር ምክክር በጎንደር ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። የሰላም ምክክሩ አንድነትን በሚደግፉ በአማራ ክልል ወጣቶች ዘንድ ድጋፍ ያስገኛል በሚል እሳቤ የተደረገ የማታለያ ድርጊት ነው።

በተመሳሳይ መልኩ፣ የፌዴራል መንግስቱን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው ህወሃት ህዝብን ማተራመስ አላዋጣ ሲለው የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች “የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት” እንዲያደርጉ ፈቅዷል። በቀጣይም ኦሮሞያ ከሶማሌ፣ አፋር ከአማራ፣ ቤንሻንጉል ከአማራ፣ ትግራይ ከኦሮሚያ እያለ መጨረሻ የሌለው “የሰላም ምክክር” ማድረጉን ይገፋበታል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ለህወሃት አገዛዝ ብዙ ጥቅም አለው። አንደኛው፣ “በአገሪቱ ውስጥ የእርስ በርስ እልቂት እንዲፈጠር እያደረገ ያለው ህወሃት ነው” የሚለውን አጀንዳ በማስቀየር፣ ህወሃት ለሰላም እንደሚሰራ ማሳየት ነው። በዚህም ተቃውሞ ይበርዳል የሚል እሳቤ መነሻ ያደረገ ነው። ሁለተኛውና ዋነኛው ግን አንድነትን በመስበክ አገር ውስጥና ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ መሳብ ነው። ቀጥሎም፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህወሃት/ኢህአዴግ ተቀይሯል በሚል “ለሰላም ምክክሩ” ድጋፍ ያደርጋሉ፣ ለውጭ መገናኛ ብዙሃንና ለአሜሪካ ሴናተሮች ሲቀርብ የነበረው አቤቱታ ያቆማሉ፣ ለአገዛዙ ያላቸውን ጥላቻ ይቀንሳሉ በሚል የተወጠነ ስሌት ነው። ህወሃት በተለይ በውጭ አገር ከሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጋር ላለመላተም ሲል፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያዊነትን ሲጸየፉ የነበሩ ቀለብ የሚሰፍርላቸው የትየለሌ ካድሬዎች ድምጻቸው እንዲያጠፉ ወደጎሬያቸው አስገብቷቸዋል።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በቀጣይ በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚደረጉ “የሰላም ምክክሮች” ለህወሃት ሌላ ጥቅም አላቸው። በተናጠል በክልሎች መካከል የሚደረጉ “ምክክሮች” በአንድ በኩል ክልሎች የራሳቸው ስልጣን አላቸው፣ “የትግራይ/ህወሃት የበላይነት የለም” የሚለውን ትርክት ለማራገብ የታሰበ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በክልሎች ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂዎቹ ክልሎች ናቸው የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ ነው። የህወሃት አባላት በማህበራዊ ድረገጽ የሚጽፉትና የሚያወሩትም ይህንኑ ነው፥ ህወሃት ስልጣን ስለሌለው የትግራይ ብሄረሰብ አባላት እየተጠቁ ናቸው በሚል። በሌላ አነጋገር ህወሃት “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ ፥ በክልሎች አያገባኝም” የሚል መልዕክት እንዲተላለፍለት ይፈልጋል።

የህወሃት የወደፊት አቅጣጫ?

በአጭሩ የህወሃት የቅርብ ጊዜ እቅዱ ተቃውሞን አረጋግቶ ነገሮችን ወደነበሩበት ወደህወሃት የበላይነት መመለስ ነው። ህወሃት በአንድ በኩል ለክልሎች ስልጣን የሰጠ በመምሰል በየአካባቢዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች ክልሎችን “ተጠያቂ” ማድረግ ሲሆን፣ ሁሉንም ጉዳይ አስፈጻሚዎቹ ደግሞ በክልሉ የሚገኙ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ናቸው። አንጋፋዎቹ የህወሃት አባላት እና አገልጋዮች ላለፉት 26 አመታት የምናውቃቸው ሲሆን፣ የህዝብ አመኔታ በማጣታቸው ከፊት ለፊት ሳይሆን ከመጋረጃ ጀርባ በመቀመጥ መሾፈር መርጠዋል። ህወሃት ታዲያ አሁን በአዲስ ብሄር፣ በአዲስ ትውልድ አዲስ አጀንዳ ይዞ ብቅ ብሏል።  ህወሃት በእነ አቶ ለማ መገርሳና በእነ ንጉሱ ጥላሁን ላይ አድሮ ኢትዮጵያዊነት “ሱስ” እንደሆነ እያስነገረ ይገኛል። ጉብኝቱን ተከትሎ ለጊዜው የህዝቡ ተቃውሞው ቆሟል፥ እነ አቶ ለማም አድናቆት ተችረዋል። የአንድነት ሃይሎች “ድሮም ስንል ነበር” በሚል በኢትዮጵያዊነት ስሜት ተውጠዋል። እስስቱ ህወሃት ግን ወይ ከአላማው ፍንክች! ተፈጥሮን ተመክሮ አያድን! አጀንዳ እየሰጠ፣ እያታለለ የበላይነቱን ይዞ ይኖራል።