November 8, 2017 14:35

ጋዜጣዊ መግለጫ

አፊሌ በምትባል የኢጣልያ ከተማ የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ በመባል ለሚታወቀው ፋሺሽቱ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ ስለ ተቋቋመው መታሰቢያ ጉዳይ በሚመለከታቸው ተጠያቂ የከተማው ባለሥልጣኖች ላይ የሐገሩ ፍርድ ቤት እጅግ የሚያረካ፤ ፍትሐዊ ውሳኔ አስተላልፏል። ለዚህ አርኪ ውጤት በድርጅታችን ከተፈጸመው ጥረት በተጨማሪ በኢጣልያ የላዚዮ አውራጃ ገዥ፤ ለሲኞር ኒኮላ ዚንጋሬቲ፤ ለአውራጃው ምክር ቤትና ለአፊሌ ፍርድ ቤት ከፍ ያለ ምሥጋና ይገባቸዋል። እንዲሁም ጉዳዩን በትኩረት ተከታትለው፤ ይህ ፍትሐዊ ውጤት እንዲገኝ ለረዱት አንፒ (ANPI) ለተሰኘው ድርጅት፤ በሮም የኢትዮጵያ ማሕበር አባሎች፤ እንዲሁም ለቫሌሪዮ ቺሪያቺ (Valerio Ciriaci) እና ለካርሜሎ ክሪሸንቲ (Carmelo Crescenti) ልዩ ምሥጋና ማቅረብ ተገቢ ነው።
ይህ የሚያበረታታ ውጤት የተገኘው በኢጣልያኑ ፍርድ ቤት ፍትሐዊነት በመሆኑ ድርጅታችን ጥልቅ ምሥጋናውን ያቀርባል። በተጨማሪም የሮዶልፎ ግራዚያኒ መታሰቢያው መወገድ ጉዳይ በቀጣይነት በፍርድ ቤቱ ታይቶ ተገቢው ፍጻሜ እንደሚገኝ ያለንን ተስፋ እንገልጻለን።
እንደሚታወቀው፤ ፋሺሽት ኢጣልያ እ.አ.አ. በ1935-41 ኢትዮጵያ ላይ በፈጸመችው እጅግ የከፋና መጠነ-ሰፊ የጦር ወንጀል፤ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መጨፍጨፋቸው፤ 2000 ቤተ ክርስቲያኖችንና 525000 ቤቶችን እንዲሁም 14 ሚሊዮን እንስሶችን ማውደማቸው፤ በተጨማሪም እጅግ ብዙ የኢትዮጵያን ንብረት መዝረፋቸው የታወቀ ነው። ይህ ሁሉ የጦር ወንጀል የተከናወነው በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ መሆኑ የማይረሳ ነው።
ከላይ ለተጠቀሰው ወንጀል ተጠያቂ ከሆኑት ኢጣልያኖች ውስጥ ከፍተኛ ሚና ለነበረው፤ በኢጣልያ ሕግ እንኳ ወንጀለኛነቱ ለተረጋገጠበት ለሮዶልፎ ግራዚያኒ እ.አ.አ. በ2012 አፊሌ በምትባል የኢጣልያ ከተማ እንደ ጀግና የሚያስቆጥረው መታሰቢያና መናፈሻ ተሰይሞለት የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት ተመርቆለት ነበር። ይህንን ፋሺሽታዊ እኩይ ተግባር በመቃወም ድርጅታችን የአቤቱታ ደብዳቤዎችን ለኢጣልያ መንግሥት፤ በተጨማሪም መታሰቢያው ለሚገኝበት አውራጃ (ላዚዮ) ገዢ፤ ለክቡር ኒኮላ ዚንጋሬቲ (Nichola Zingaretti) አቅርቦ ነበር።
የቀረበውን አቤቱታ በመደገፍ፤ ኢጣልያ የሚገኙ አንዳንድ የሐገሩ ዜጎች፤ ለምሳሌ ቫሌሪዮ ቺሪያቺና ካርሜሎ ክሪሸንቲ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ማሕበርና አንፒ (ANPI) የተሰኘ የፋሺሽት ተቃዋሚ ድርጅት በፈጸሙት በመታሰቢያው ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማከናወን ጭምር ባከናወኑት የተቃውሞ ተግባር የላዚዮ አውራጃው ምክር ቤት ጉባኤ የግራዚያኔ መታሰቢይ መወገድ እንዳለበት ከመወሰኑ በላይ፤ ውሳኔው በአስቸኳይ ካልተፈጸመ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንዲመራ ተወሰነ። ለመታሰቢያው ይቀርብ የነበረው በጀትም እንዲቋረጥ ተደረገ።
ነገር ግን፤ መታሰቢያው የሚገኝበት የአፌሌ ክተማ ከንቲባና ባልደረቦቹ የምክር ቤቱን ውሳኔ ባለመፈጸማቸው ጉዳዩ ለብዙ ወራት በኢጣልያ ፍርድ ቤት ሲታይ ከቆየ በኋላ፤ዛሬ፤ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ/ም በተሰጠው ውሳኔ፤

1ኛ/ የአፊሌ ከንቲባ፤ ኢርኮሌ ቪሪ (Ercole Viri) የ8 ወሮች እስራትና የ120 ዩሮ (Euro) ቅጣት
ተፈርዶባቸዋል።
2ኛ/ ሁለት የከተማው ምክር ቤት አባሎች፤ ፔፔሮኒ እና ፍሮዞኒ (Peperoni and Frosoni)
እያንዳንዳቸው የ6 ወሮች እስራትና የ80 ዩሮ (Euro) ቅጣት ተፈርዶባቸዋል።
3ኛ/ ተከሳሾቹ ለ5 ዓመት ከመንግሥት ሥራ እንዲወገዱ ተፈርዷል።
4ኛ/ ተከሳሾቹ፤ የፋሺሽት ተቃዋሚ ለሆነው አንፒ (ANPI = Italian National Partisan
Association) ለተሰኘው ድርጅት 8000 ዩሮ (Euro) እንዲከፍሉ ተፈርዷል።
5ኛ/ ክሱን ላቀረበባቸው መሥሪያ ቤት 1800 ዩሮ (Euro) እንዲከፍሉ ተፈርዷል።
ከላይ የተዘረዘረው የኢጣልያ ፍርድ ቤት ውሳኔ፤ የይግባኝ ሒደት ቢኖርበትም በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው አሰቃቂ የጦር ወንጀል እንዲሁም ባሁኑ ዘመን ሮዶልፎ ግራዚያኒን ለማጀገን ለሚፈልጉ ፋሺሽቶች ፍትሐዊ መልስ የሰጠ ሲሆን ድርጅታችን አንግቧቸው ያላሰለሰ ጥረቱን እየቀጠለባቸው ላሉት መሠረታዊ ዓላማዎች፤
(ሀ) የኢጣልያ መንግሥት ተገቢውን ካሣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘለቄታው በሚጠቅም መንገድ
እንዲከፍል፤
(ለ) የተዘረፈው ንብረት ለኢትዮጵያ እንዲመለስ፤
(ሐ) ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤
(መ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው የፋሺሽት የኢጣልያ የጦር
ወንጀል እውቅናና ድጋፍ እንዲሰጥ፤ እና
(ሠ) ለፋሺሽቱ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ የተቋቋመው መታሰቢያና መናፈሻ እንዲወገድ፤
የሚያበረታታ ክስተት መሆኑን ያመለክታል።
ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ለውድ ሐገራችን የሚገባትን ፍትሕ እንድናስገኝ ያበርታን። አሜን