Posted by admin | 09/11/2017

ከዶ/ር ደረስ ጌታቸው ጋር “VOA” በጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው መሪነት ስለ #ኦሮማራ እየተወያየን ነበር፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ስር-ነቀል ተሃድሶ አድርጎ አሁን ያለው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ እንዲያገኝ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ተወያይተናል፡፡ ውይይቱን ስታዳምጡ ለብዙዎቻችሁ ጭፍን የኦህዴድና ብአዴን ደጋፊ የሆንኩ ሁሉ ሊመስላችሁ እችላለሁ፡፡ በእርግጥ ኦህዴድና ብአዴን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደመሆናቸው መጠን አሁን በሀገሪቱ ለተከሰተው ችግር በቀጥታ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ህወሃት ግን ከሁለቱ በጣም በተለየ መልኩ ጨቋኝና አምባገነን በመሆኑ ዋና የለውጥ እንቅፋት ነው፡፡ ኦህዴድና ኢህአዴግ ከሚወክሉት ህዝብ ጎን አለመቆማቸው ያስወቅሳቸዋል፡፡ ህወሃት ግን ከትግራይ ህዝብ ጎን አለመቆሙ ብቻ ሳይሆን ብአዴንና ኦህዴድ ከህዝባቸው ጎን እንዳይቆሙ ማድረግ የሌት-ተቀን ሥራው ነው፡፡ በህወሃቶች ዘንድ #ተሃድሶ ማለት የሚወክሉትን ህዝብ ጥያቄ የመቀበል ወይም የድጋፍ አዝማሚያ ያሳዩትን የብአዴንንና ኦህዴድን አመራሮች መምታት ነው፡፡ ህወሃት የኢህአዴግ መስራች ድርጅት ብቻ ሳይሆን ዋና ማነቆ ነው፡፡ ስለዚህ የኢህአዴግ መንግስት ህልውና እንዲቀጥል በመጀመሪያ ህወሃት/ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሞላ-ጎደል አልተሳካም፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ሁለተኛ አማራጭ የለውጥ ማነቆ የሆነውን ህወሃትን ከኢህአዴግ ውስጥ ማስወገድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከብአዴንና ኦህዴድ አንዱ ከግንባሩ ራሱን ማውጣት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ይፈርሳል፡፡ እስከ 2012 ድረስ አብላጫ ድምፅ ያለው ኦህዴድ መንግስት እንዲመሠርት ይጠየቃል፡፡ ከዛ ከብአዴን ጋር ተጣምሮ የራሱን መንግስት ይመሠርታል፡፡

በዚህም ህወሃትን ጠራርጎ ማስወገድ ይቻላል፡፡ ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ህወሃት በመቀለ ስብሰባው የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን እንዴት ጠራርጎ እንደሚያስወግድ እየተወያየ ነው፡፡ ከስብሰባው በኋላ ኦቦ ለማ ሆነ አቶ ገዱ፣ አቶ ንጉሱ ሆነ ኦቦ አዲሱ፣…ሁሉም ተጠራርገው ይወገዳሉ፡፡ ከትላንት ጀምሮ የህወሃት ሸርና አሻጥር እየተሸረበ ያለው በዚያ ላይ ነው!! ከዚህ በተረፈ ህወሃት በ1993ቱና በ2008ቱ ተሃድሶ ክፉኛ ተፀፅቶ ብአዴንና ኦህዴድ ላይ ለመፈፀም እያሰበ ያለውን  ያዩታል፡፡