ቴዎድሮስ አበበ
Washington, DC ጥቅምት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. │ November 7, 2017
በዓለት ላይ ታንጾ በወርቅ የተጻፈ
በሰማያዊ ክብር ጸንቶ የገዘፈ
የማይገረሰስ ዘመን የማይሽረው
የዓለም ማዕበል የማይገፈትረው
ሊጥሉት፣ ሊፍቁት፣ ሊያጠፉት ቢጥሩ
የማይነቀንቁት ከጠበቀው ስሩ
የማይደበዝዝ ነው ደምቆ የሚያበራ
የአፍሪካ ፀሐይ፣ የነፃነት አውራ
የጥቁር ሕዝብ ሰንደቅ የድል ብርሃን ተስፋ
የማንነት መብራት መቼም የማይጠፋ . . .
“ኢትዮጵያ” ስሟ ነው “ኢትዮጵያ” ዓርማችን
ሲያበራ የሚኖር መሪ ኰከባችን። “ኢትዮጵያ” ስሟ ነው አይጠፋም፣
አይወድቅም ቀደምት፣ ባለታሪክ ክብሯ አይፋቅም
በመንፈሣዊውም በዓለማዊ መዝገብ
“ኢትዮጵያ” ስሟ ነው ቀድሞ የሚታሰብ።
ስሟን ሊሰርዙ፣ ስሟን ሊያቆሽሹ
ከማንነታቸው ተጣልተው የሸሹ
ይደክማሉ እንጂ ያልታደሉ ሆነው
“ኢትዮጵያ” ተተክሏል ምንም ሀይል ላይነቅለው።
በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታትሟል ቀለሟ
ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ናት ይዘመራል ስሟ
. . . ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ናት፤ ገና ይነግሣል ስሟ