November 25, 2017 10:56

 

*****
በህይወት ዘመኔ ደጋግሜ እየጠየቅሁና የማገኛቸውን መልሶች ግን በምንም ተዓምር ለማስታወስ ያቃቱኝ ሁለት ነገሮች አሉ። የኔ የደም ዓይነት ከአራቱ የትኛው እንደሆነ ዕድሜ ልኬን እንዳዲስ ልጆቼን እየጠየቅሁ ነው የምኖረው። ሁለተኛው ሁሌም የማይገባኝ ነገር ደግሞ ታናሽ ወንድሜ ዕድሜ ልኩን ያለመታከት የሚያስረዳኝ አንድ በኦሮሞ ባህል “ሆቦ” እና “ጮራ” ስለሚባሉ የትውልድ ተዋረድ ሥርዓት ነው። ነገሩ በጣም ቀላል ነው፣ አባት “ሆቦ” ከሆነ ልጅ “ጮራ” ይሆናል፣ ለምሳሌ አባቴና ልጄ አንድ ዓይነት ይሆናሉ፣ እኔ ደግሞ ከአያቴና ከልጅ ልጄ ጋር አንድ ዓይነት እሆናለሁ፥ በጣም ቀላልና ለማስታወስ ያን ያህል የማይከብድ ነገር ነው፣ እኔ ግን እስከዛሬ “ሆቦ” ልሁን “ጮራ” የትኛው እንደሆንኩ ማስታወስ አልችልም። ዕድሜ ለቴክኖሎጂ፣ በተጠየቅሁ ቁጥር ተዋክቤ ያልሆነ መልስ ከምሰጥ ብዬ የሁለቱንም ትክክለኛ መልስ በተንቀሳቃሽ ስልኬና ኮምፒውቴሬ ላይ መዘግቤ ተገላገልኩ።

የኢትዮጵያን ፖሊቲካም በተመለከተም እንደዚሁ ልክ እንደ ደም ዓይነቴ ወይም “ሆቦ” ና “ጮራ” ደጋግሜ ጠይቄም እስከ ዛሬም ያልገቡኝ ሁለት ነገሮች አሉ፣ የመጀመርያው የ “ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ” ማንነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሕወሃት ከጥቂት ዓመታት በፊት ያወጀው የጸረ ሽብር ዓዋጅና አፈጻፀም ነው። እነዚህን ጥያቄዎች በተለያየ ጊዜና ቦታ ለተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች አቅርቤ መልሶቹን የሰጡኝ ይመስለኛል፣ ሆኖም ግን እስከ ዛሬም ይኸው ወይ አይገቡኝም ወይ ደግሞ እየረሳኋቸው ሁሌም እንዳዲስ እየጠየቅሁ እኖራለሁ፣ ዛሬ ግን ምናልባት ቀለል ባለ መንገድ የሚያስረዳኝ ካለ በሚል ተስፋ የተለመዱትን ጥያቄዎቼን ለሚመለከታቸው አቅርቤያለሁና እስቲ እንደኔው ግራ የተጋባችሁ ካላችሁ አብረን እንጠይቅ።
የሕወሃት ማንነት፣

በኔ ግምት የሕወሃትን ማንነት፣ ጠንቅቆ የሚያውቅ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፥ ያኔ ድሮ ድሮ በደርግ ዘመን በተቃዋሚው ሰፈር በማውቃቸው የሕወሃት ጓደኞቼ ይነገረኝ የነበረው፣ “የሕወሃት ማንነትና ዓላማው ማኒፌስቶው ላይ በግልጽ ተቀመጦልሃልና አንብበህ ተረዳ” የሚል ነበር። ዕውነትም የድርጅቱን መርሃ ግብር ስመረምር፣ ዓላማው የትግራይን ህዝብና መሬት ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነጻ አውጥቶ ራሱን የቻለና ነጻ የሆነ አገር መመስረት ነው ተብሎ በግልጽ ተቀምጧል። የድርጅቱም ስም “ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ” ይህንኑ ስለሚያረጋግጥ መጠየቄም አላስፈላጊ ነበር። ኋላ ኋላ ግን ትግራይን ነፃ ካወጡ በኋላ ወደ ወሎና ጎንደር መዝለቃቸውን ስሰማ እነዚህ ሰዎች ምን ነካቸው? የትግራይን መሬትና ህዝብ እኮ ነጻ አውጥተዋል ታድያ ወዴት ነው የሚሄዱት? ብዬ ባጠያይቅ መልስ ሰጪ ጠፋ። ምናልባት ፈረንጆች buffer zone የሚሉትን ለአደጋ የማያጋልጥ “የጠላት ግዛት” ለመያዝ ብለው ይሆናል ብዬም ገመትኩ። ብዙም ሳይቆይ ሕወሃት ኢትዮጵያውያን “ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶችን” ፈጥሮና ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት አዋቅሮ ”ዲሞክራሲያዊ የሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት“ የማቋቋሙን ሥራ ተያይዞት ሳስተውል፣ ሁለት የጥርጣሬ መንፈሶች በአምሮዬ ተቀረፁ፣

አንደኛው፣ ሕወሃት ምናልባት ወደ አዲስ አበባ የመጣው ለትግራይ ሬፑብሊክ ህልውና ዋስትና ሲሰጥ የሚችል አስተማማኝ የጎረቤት መንግሥት ለመመስረት እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቅረት አስቦ አይደለም የሚለው ሲሆን፣

ሁለተኛው ደግሞ፣ ሕወሃት ወደ አዲስ አበባ የዘለቀውና የከተመው የመገንጠል ዓላማውን ትቶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ጋር በመሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይሆናል ብዬ ገመትኩ።

ቀናት ወደ ወራት ከዚያም ወደ ዓመታት እየተሸጋገሩ ሲሄዱና፣ ሕወሃት በአንድ በኩል፣ “አሁንም የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ነኝ፣ ግን ኢሕአዴግ ውስጥ ደግሞ አባል ብቻ ሳይሆን መሪ ድርጅት ነኝ” እያለን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ስም ዓዋጅ ሲያወጣና ሲሽር፣ ዓለምዓቀፍ ውሎችን ሲፈርምና ሲቀድ አይቼ፣ መቼም ሰው ነኝና ጥርጣሬዬ እንደገና አገረሸብኝ። እነዚህ ሰዎች ልክ አሜሪካ ሳዳም ሁሴንን ከሥልጣን ካወረደች በኋላ፣ ኢራቅ ለአሜሪካ የምታቀርበው የነዳጅ ዘይት ምርት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ወታደሮቿን በኢራቅ ላልተወሰነ ጊዜ ለማቆየት እንደወሰነች፣ ሕወሃትም ደርግን ከገለበጠ በኋላ በኢትዮጵያ ቆይታውን ያራዘመው ነፃ ላወጣት ለትግራይ ሬፑብሊክ ከኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን የጥሬ ሃብት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ለማረጋገጥ ብለው ይሆን ብዬም አሰብኩ። በታቃራኒው ደግሞ፣ የሕወሃት አባላት፣ ወታደራዊ መኮንኖችና የሲቪል ባላሥልጣናት ከትግራይ ውጪ በተለይም በአዲስ አበባ ይህ ነው የማይባል ሃብት “እያፈሩ”፣ ያገሪቷንም ወታደራዊና ሲቪል አስተዳደር ቢሮክራሲውንም ሆነ ኤኮኖሚውን በበላይነት መቆጣጠራቸውን ሳስተውል፣ እነዚህ ሰዎች ወደ ትግራይ አይመለሱም ብዬም ራሴን ለማሳመን ሞከርኩና ድንገት ደግሞ፣ ታዲያ እንደሱ ከሆነ ለምን አንደኛውኑ ስማቸውን ቀይረውና፣ ራሳቸውንም እንደ አንድ የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ድርጅት አዋቅረው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ጋር በአቻነት በመሆን ዲሞክራሲያዊቷን ኢትዮጵያ የመገንባቱን ሥራ አይያያዙትም የሚል ሃሳብ ደግሞ ይመጣብኛል። ግራ የገባው ነገር እኮ ነው እባካችሁ – ለመጠየቅም የማያመች!

አዎ ለመጠየቅም የማያመች ነገር ነው፥ ግን ደግሞ ካልተጠየቀ መልስ አይገኝምና፣ ዛሬ በግልጽ በአደባባይ ለኔና እንደኔም ነገሩ ግራ ለገባቸው ኢትዮጵያውያን በቅንነት እንዲያስረዱን፣ ከማንኛችንም በላይ ለድርጅቱ ቅርብ የሆኑና ዕውነተኛውን የሕወሃት ባህርይ ያውቃሉ ብዬ ለምገምታቸው ለዛሬዎቹ የኦሕዴድና የብአዴን መሪዎች ማለትም ለኦቦ ለማና ጋሸ ገዱ ጥያቄዬን እንደሚከተለው ለማቅረብ ወሰንኩ።

“ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንወክላለን” እያላችሁ፣ እንዴት “የትግራይን ህዝብና መሬት ከቅኝ ገዢዋ ኢትዮጵያ ነጻ አውጥቼ ነጻዋን ትግራይን እመሰርታለሁ” ብሎ ከተቋቋመውና ዛሬም ድረስ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር – ሕወሃት ነኝ” ብሎ በግልጽ እየነገረን ካለው ለትግራይ ብቻ ከተፈጠረ ድርጅት ጋር አንድ “ኢህአዴግ” የሚባል ኢትዮጵያዊ “ግንባር” ውስጥ ፈጥራችሁና አብራችሁ በመሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደምትሰሩ አልገባኝም፣ እናንተ “ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች” ሆናችሁ ካንድ የብሄር ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ባንድ ላይ ሆናችሁ በውነት ኢትዮጵያን እንገነባለን ብላችሁ አምናችሁበት ነው?

መልሱ እንዲቀላቸው በማሰብ፣ እንደ አንድ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊ ከውጪ ሆኜ ሁኔታውን ስገመግመው የሕወሃትን ዕውነተኛ ማንነትና ዓላማ ያንጸባርቃሉ ብዬ የምገምታቸውን አንድ አራት መላ ምቶችን እንደሚከተለው ላመቻችላቸው።

ሀ) ሕወሃት በርግጥም ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጻ ሊያወጣ የተቋቋመና ሌላ የግዛት ማስፋፋት ዓላማ የሌለው ድርጅት ነው፣ ዛሬም የተወለደበት ስሙን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ገና ነጻ ያልወጡ የትግራይ መሬቶች ስላሉ እነሱን ነጻ አውጥቶ እስኪጨርስ ድረስ ስሙን ይዞ መቅረት ስላለበት ብቻ ነው። “ቀሪውን የትግራይ መሬት” ነጻ አውጥቶ ሲያበቃ፣ ወደ ነጻይቷ ትግራይ ተመልሶ አዲስ ስም ለራሱ አውጥቶ ትግራይን የመገንባቱን ሥራ ይቀጥላል ማለት ነው፣ ወይስ፣

ለ) ሕወሃት መጀመርያ ሲፈጠር፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጻ ሊያወጣ ቢሆንም፣ ከነጻነት በኋላ ግን፣ በኢትዮጵያ ያለው “ጨቋኝ መንግሥት ለነፃዋ ትግራይ ህልውና የሚያሰጋ ሆኖ ስለተገኘ፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን “ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች” ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን መንግሥት ጥሎ በምትኩ አስተማማኝ የሆነ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መስርቶ ወደ ትግራይ ይመለሳል። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ደግሞ ጊዜ የሚፈጅ ሥራ በመሆኑ የሕወሃት ሃያ ስድስት ዓመት በኢትዮጵያ መቆየት ያንን ያህል አሳሳቢ መሆን የለበትም ማለት ነው፣ ወይስ፣

ሐ) ሕወሃት የተፈጠረው ትግራይን ነጻ ለማውጣት ብቻ ቢሆንም በሂደት ግን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን “ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች” ጋር በመሆን በኢትዮጵያም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋምና በቅርቡ ነጻ የወጣችዋን ትግራይና አዲሲቷን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን አዋህዶ እንደ አንድ አገር መግዛት መቻሉን ተረድቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ሆኖ ቀርቷል ማለት ነው፣ ወይስ፣

መ) ሕወሃት የተፈጠረውም የሚኖረውም እንደ ትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ነው፣ ትግራይን ነጻ ካወጣ በኋላ ግን ወደ አዲስ አበባ ዘልቆ ድርጅታዊና ወታደራዊ የበላይነቱን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ምርቶችን ወዳገሩ እያጋዘ የሚገኝ የውጭ ወራሪ ኃይል ነው። አንድ ቀን ግን በግፍ አገዛዙ ያልተደሰተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ካመጸና አመጹም ከቁጥጥር ውጪ ከሆነበት፣ የቻለውን ሁሉ ዘርፎ ወዳገሩ ወደ ትግራይ ለመመለስ ዝግጁ በመሆኑ የትውልድ ስሙን አለመቀየሩ ቀድሞውኑም የታቀደበት ነው ማለት ነው?

ከነዚህ ግምቶቼ የትኛው ትክክል እንደሆነ አላውቅም፣ ምናልባትም ደግሞ ሌላ ከነዚህ የተለየ ምክንያት ካለ ኦቦ ለማና ጋሽ ገዱ ዕቅጩን እስኪነግሩን ድረስ በበኩሌ “አንቺ ግፍ አትፈሪም በኔ ቤት ሆነሽ፣ ዳንቴል ትሰሪያለሽ ለዚያኛው ቤትሽ” የሚለውን የጌትሽን ነጠላ ዜማ እያንጎራጎርኩ የጥርጣሬ ህይወቴን ለቀጥል። መብቴ ነው አይደል? ሃያ ስድስት ዓመት ሙሉ በጥርጣሬ መኖር ግን ይሰለቻል እኮ ጎበዝ! ቁርጣችንን አውቀን ወይ እንደ ወንድማማችና እንደ አንድ አባት ልጆች ተማምነን ባንድ ላይ የጋራ ቤታችንን እንሥራ፣ አለበለዚያ ደግሞ ሕወሃት ድሮም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በእንግድነት ስለሆነ ባህላችን በሚፈቅደው መሰረት ያለንን በመካፈል እናስተናግዳቸው፣ እነሱም እንደ ጥሩ የጎረቤት እንግዳ፣ ባህላችንን አክብረው ራሳቸውን ዝቅ አርገው ለምናደርግላቸው መስተንግዶ አምስግነውን በጊዜ ወደ አገራቸው ይመለሱ። እኛም ደግሞ በተራችን አንድ ቀን እንደዚሁ እግር ጥሎን የነሱ እንግዳ እንሆን ይሆናል አይታወቅም፣ ጥሩ ጎረቤቶች!
ሁለተኛውና ሁሌም አልገባ ያለኝ ነገር ደግሞ ሕወሃት ሽብርን አስመልክቶ ያወጣው ዓዋጅና አፈጻፀሙን በተመለከተው ነው።

በመሠረቱ፣ ማንኛውም መንግሥት ህገ መንግሥቱን ያልተከተለ የሥልጣን ሽግግር አይፈቅድም። ይህ እንግዲህ ህዝቦች መሪዎቻቸውን ለመምረጥ በታደሉበት አገር ለረጅም ዘመን ሥራ ላይ የዋለ መሪህ ሲሆን፣ እኛን ግን እንደማይመለከት ጠንቅቄ አውቃለሁ፥ በታሪካችን ውስጥ አንድም መሪ በህዝቦች ፈቃድ፣ ማለትም ያለጠብመንጃ ድጋፍ ሥልጣን ላይ የወጣ ባለመኖሩና

ይህንንም ክስተት ደግሞ በደንብም ስለለመድነው “ለምን” የሚል ጥያቄ እንኳ ማቅረብ ገራገር ያስመስላል። የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሪዎች ማለትም ጃንሆይ የመጀመርያውን ህገ መንግሥት “ለሕዝባቸው ከሰጡበት” ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉት፣ መሪዎቻችን በሙሉ የፖሊቲካ ሥልጣኑን የያዙት ህገ መንግሥቱን በመጣስ ነው። ሞክረው የተሳካላቸው (መንግሥቱ ኃ/ማርያምና መለስ ዜናዊ) ሲነግሱ፣ ያልተሳካላቸው (እነ መንግሥቱ ንዋይና እነ ደምሴ ቡልቶ) ደግሞ “ህገ መንግሥታዊ ባልሆነ ዘዴ ሥልጣን ለመያዝ ሞክራችኋል” ተብለው ሞትና እስራት ሲፈረድባቸው ምሥክሮች ነበርን። ይህ ማለት እንግዲህ፣ በኢትዮጵያችን አንድን መንግሥት ህጋዊ የሚያደርገው፣ ገድሎም ይሁን አስገድሎ ሥልጣን መያዙ እንጂ ሥልጣኑን በምን መንገድ እንደያዘ አይደለም ማለት ነው። የሚገርመው ግን፣ መሪዎቻችን ህገመንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን በያዙ ገና በማግሥቱ “ህገ መንግሥቱን ጥሶ ሥልጣን መያዝ በእኔ ላይ ያበቃል፣ ካሁን በኋላ ግን ህገ መንግሥታዊ ባልሆነ ዘዴ የፖሊቲካ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው” ብለው ሲሉን ነው።

ሕወሃት ለሥልጣኔ ያሰጉኛል የሚላቸውን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎችን በሙሉ ለመምታት እንዲያመቸው “ህገመንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ለመውሰድ እየሞከሩ ነው” የሚላቸውን ሶስት አገር በቀል ተቃዋሚ ድርጅቶችን (ኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት ሰባትን) አዲስ ባወጀው የጸረ ሽብር አዋጅ መሰረት በአሸባሪነት ፈረጃቸው። እነዚህን ድርጅቶች እንኳን በዕውንና በህልምም ያዋራቸው “የሽብርተኞች ግብረ አበር” ተብሎ እንደሚወነጀል ለፈፈ። ጸረ ጠብመንጃ ትግል ያካሄዱ የነበሩ እነመረራ ጉዲናና በቀለ ገርባም ከነዚህ ሽብርተኛ ድርጅቶች አባላት ጋር ታይታችኋል ተብለው ወህኒ ቤት ተላኩ። ብዕር ብቻ በማንገት የመናገርና የመጻፍ ህገመንግሥታዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሞከሩት እነ እስክንድር ነጋም ወንጀለኞች ተብለው ተፈረደባቸው። በፌስቡክ ወይም በኢንቴርኔት ተጻፅፋችኋል ተብለው ብዙ ወጣቶች በአሸባሪነት ወንጀል ተከሰሱ።

ይህን “የጸረ ሽብር”ን ዓዋጅ በተመለከተ ሁሌም የማይገባኝ አንድ ነገር አለ። ዓዋጁ በታወጀበት ወቅት “ህገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የፖሊቲካ ሥልጣን ለመውሰድ” ተደራጅተው ይንቀሳቀሱ የነበሩና ዛሬም ያሉ ሶስት ብሄራዊ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ማለትም ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ትሕዴን- (የትግራይ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ – TPDM) እና አንድ አገር አቀፍ ድርጅት (ግንቦት ሰባት- አርበኞች) ነበሩ። አራቱም ድርጅቶች በትጥቅ ትግል አጥብቀው የሚያምኑ ሲሆን፣ የሥልጠና ጣቢያና ቁሳቁሳዊ ዕርዳታ የሚያገኙት፣ ከኤርትራ መንግሥት ነው። አራቱም ድርጅቶች የታጠቀና የተደራጀ ኃይል ሲኖራቸው ከሁላቸውም ግን በትጥቅም ሆነ በታጣቂው ኃይል ብዛት የመጀመርያውን ደረጃ የያዘው ትሕዴን ነው። ታድያ ሕወሃት ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት ሰባትን በሽብርተኝነት ሲፈርጅ፣ እንዴት ትሕዴን ን ዝርዝሩ ውስጥ ሳይጨምር ቀረ? አንዲት ቀን ጠመንጃ አንግተው የማያውቁና ጸረ ጠመንጃ ትግል አቋም ያላቸውን በቀለና ገርባና መረራ ጉዲናን “በአሸባሪነት” ሲወነጅላቸው፣ የትሕዴን መሪው ሞላ አስገዶም ከነክላሽንኮቩ ከመቶ በላይ የሚሆኑትን ወታደሮቹን ከነትጥቃቸው መርቶ ኢትዮጵያ ሲገባ እንኳን አሸባሪ ሊባል፣ እንዴት እንደ አንድ ጀግና ሊቀበሉትና በሰላምም እንዲኖር ተፈቀደለት? ይቺ ነገር ምናልባትም ከመጀመርያው ጥያቄዬ (የሕወሃት ማንነት) ጋር አንዳች ግንኙነት ይኖራት ይሆን? ብዬ ሁሌም ራሴን እንደጠየቅሁ ነው። ዓዋጁ በፓርላማ ቀርቦ የተወያዩበትና የጸደቀ በመሆኑና በቦታው ከነበሩ፣ ከኦቦ ለማና ጋሽ ገዱ በላይ የአዋጁን ትክክለኛ ይዘት ሊያውቅ የሚችል የለምና እስቲ እንደሚከተለው ልጠይቃቸው፣

አንደኛው፣ የትውልደ-ትግራይ (ትሕዴን) ጠብመንጃ የሚተፋው ጥይት፣ መረጋጋትን የሚያሰፍን እንጂ የማይገድል፣ የትውልደ-ኦሮሞ (ኦነግ) የትውልደ-አማራና (ግንቦት ሰባት) የትውልደ-ዉጋዴን (ኦብነግ) ጥይት ደግሞ ግድያና ጥፋትን ብቻ ይዘራል” ብላችሁ ተስማምታችሁበት ነበር? ወይስ፣

ሁለተኛው፣ የዓዋጁ ተፈጻሚነት በኢትዮጵያ ምድርና በኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ላይ እንጂ፣ በቅርቡ “ነጻ በወጣችው” የትግራይ ግዛትና የትግራይ ድርጅቶች ላይ አይደለም ብላችሁ ነው?
እባካችሁ መልሱልኝ፣ አመሰግናለሁ።
*****

ጄኔቫ፣ 15 ኖቬምበር 2017
wakwoya2016@gmail.com