ከዐሥራ ምናምን ዓመታት በፊት ወንድሞቻችንን ጓደኞቻችንን በገፍ ወያኔን እንዲቀላቀሉ ያደረገ አንድ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በሰዓቱ ሁኔታው እጅግ አስደንግጦኝ ስለነበረ እንባ እየተናነቀኝ ጭምር ለምን ይሄንን እንዳደረጉ አንዳንድ ወንድሞችን ለመጠየቅ ተገድጀ ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ የሰጡኝ ምላሽ ከሀገር ሀገርና ከሰው ሰው ሳይለያይ አንድ ዓይነት ነበረ፡፡ እሱም “ራሳችንን ከፖለቲካው ማግለላችን ማራቃችን በሌላ በኩል ያሉት መናፍቃኑና ሌሎችም በገፍ መግባታቸውና መሳተፋቸው የእኛ ጥቅሞች እንዲሸረሸሩ፣ እንዲሸራረፉ ሲያደርግ የእነሱ ጥቅሞች ደግሞ እንዲከበሩ አድርጓልና ገብተን ይሄንን ሁኔታ መለወጥ ጥቅማችንን ማስከበር አለብን!” የሚል ነበረ፡፡

በነዚያ ዓመታት አካባቢም ይሄውን ምክንያትም ከአንድ አሁን በእስር ላይ ከሚገኝ የወያኔ ባለሥልጣን አባ ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ላይ የፈጠሩትን ችግር በመቃወም ከ15ዓመታት በፊት በማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ካህናትና ምእመናን በተቀሰቀሰው የተቃውሞ ትግል ምክንያት ጉዳዩ ይመለከተኛል ካለ የሚንስቴር መሥሪያ ቤት “ከአባ ጳውሎስ ጋር ያለባቹህች ችግር አደራድሬ እፈታለሁ!” ስላለ ከደብሩ ተወካዮች ወይም ተደራዳሪዎች አንዱ ሆኘ ከፊቱ በቀረብኩ ጊዜ በግል “እንደናንተ እንደናንተ ያላቹህት ግቡና ጥቅማቹህን አስከብሩ!” የሚለውን ቃል ከአንደበቱ ስሰማ ወያኔ ማኅበረ ቅዱሳንና መሰል የቤተክርስቲያን የወንድም እኅቶች ማኅበራት ውስጥ ሰርጎ እንደገባና በጣም አታላይ በሆነ መንገድም ማኅበራቱን ለመረከብ፣ ለመቆጣጠርና ያለበትን የሰው ኃይል እጥረት በዚህ አታሎ፣ ሸንግሎ ለመቅረፍ እንዳሸመቀ፣ ወንድም እኅቶቻችንንም ይሄንን ብሎ እንደሸወዳቸው ገባኝ፡፡ በዚህም መሠረት ከዚያ በኋላ የተታለሉት ወንድም እኅቶች ከፊሎቹ በግልጽ የወያኔ ካድሬነታቸው እየታወቀ ወያኔን ማገልገል ሲቀጥሉ እንደ ዳንኤል ያሉት ደግሞ ብልጡ ወያኔ የበለጠ በእነሱ ተጠቃሚ የሚሆነው ወያኔነታቸው ሳይታወቅ ሕዝባዊ መስለው በሚሰጡት አገልግሎት መሆኑን ስለተረዳ በዚህ በልኩ እንዲያገለግሉት አደረገ፡፡

ይሄንን የዳንኤል ስውር አገለግሎት ዳንኤል በየጊዜው ወያኔ አጣብቂኝ ውስጥ በገባ ቁጥር፣ ሕባዊ ዐመፅ ባየለበት ቁጥር ወያኔ ከአጣብቂኙ እንዲወጣና የሕዝቡ ዐመፅ ይወገድለት ዘንድ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ልብ ያለ ልባም ይረዳዋል፡፡ ዳንኤል ከዚህም በላይ ተቃዋሚዎች አቅም የሌላቸውና ደካሞች እንደሆኑ በማስመሰል ከወያኔ የተሻለ ኃይል መሬት ላይ እንደሌለ በመወትወት፣ ክርስቲያን በዐመፅና ተቃውሞ መሳተፍ እንደሌለበት በመስበክ…. ወያኔ ተጨማሪ የግዛት ዘመን እንዲያገኝ ሕዝብን ለማሳመን ጥረት የሚያደርግ ተኩላ ነው፡፡

ዳንኤል በእነዚህ የተኩላ ሥራዎቹ ማንነቱ እንዳይገለጥ ወያኔን የተቃወመ መምሰል ከፈለገም ወያኔን የሚቃወሙ ወያኔ ችግር እንዳለበት አምኖ በብዙኃን መገናኛው “በስብሻለሁ፣ ገምቻለሁ፣ የመልካም አሥተዳደር ችግር አለብኝ ሕዝብን በድያለሁ…!” ብሎ ማስተጋባቱን እየተከተለ ሁሉም ነገር በወያኔ አንደበት ከተገለጸ በኋላ ነው ወያኔ ያስተጋባውን መልሶ በማስተጋባት ነጻ ሰው ለመምሰል ጥረት የሚያደርገው እንጅ ዳንኤል ለአንድም ቀን ቢሆን ለሀገር ለቤተክርስቲያንና ለሕዝብ በማሰብ ከወያኔ ኑዛዜ አስቀድሞ ወያኔ ያለበትን ችግር ነቅፎ፣ ተችቶ፣ ተቃውሞ አያውቅም፡፡ እነኝህ እነኝህ ተግባሮቹም በምድረ ቅጥረኛ ቢጤዎቹ ስለሚደገፉና ስለሚራገቡ ለወያኔ የማይናቅ ጥቅም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በዳንኤል ቅጥረኝነት ላይ ጥርጣሬ ያለበት ሰው ካለ ከሁለት ሦስት ዓመት በፊት ስለሱ የጻፍኳቸውን መረጃ ሰጭ የሁለት ጽሑፎችን ሊንኮች (ይዞች) ከታች አያይዠለታለሁና አንብቦ መረዳት ይችላል፡፡

ወደቀደመው ነገራችን እንመለስና ወንድሞች ከላይ በገለጽኩላቹህ ምክንያት እውነት መስሏቸው “ተመሳስለን ገብተን የሀገራችንን፣ የቤተክርስቲያናችንን፣ የወገናችንን ጥቅም እናስከብራለን!” ብለው በቅን ልቡና ወያኔን የተቀላቀሉ ቢሆኑም (ሁሉንም ማለቴ አይደለም በዚህ ምክንያት ተከልለው የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር የገቡም አሉና) ቅን አስበው የገቡ ቢሆኑም አሳዛኙ ነገር ግን ከተቀላቀሉት ውስጥ ያሰቡትን ለመፈጸም ጥረት በማድረጋቸው በተለያየ ጊዜ ከፊሎቹ ታፍነው የደረሱበት ሳይታወቅ ሲቀር፣ ከፊሎቹ ሐሰተኛ ክስ እየተመሠረተባቸው ለእስር ሲዳረጉ፣ ከፊሎቹ ለስደት ሲዳረጉ ዕድለኞቹ ደግሞ ምንም እንኳ ወያኔ እንደነበሩ ታውቆ ስማቸው ቢሰበርም እንዲገለሉ ተደረጉ፡፡

የተቀሩት ግን ወያኔን መስለው ወያኔን አክለው ወያኔን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የታሰበው ተመሳስሎ ገብቶ የሀገርን፣ የቤተክርስቲያንን፣ የሕዝብን ጥቅምን የማስከበር ዓላማም ቀልጦ ቀርቶ ይሄው እንደምታዩት የሀገር፣ የወገን፣ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ከቀን ወደቀን እየከፋ መጥቶ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡ ወንድሞች አስቀድሞ ወያኔን ጨው ሆነው ሊያጣፍጡት የማይችሉት የጎረናና የተመረዘ ወጥ መሆኑን አለማወቃቸው ውድ ዋጋ አስከፈላቸው፣ ጭራሽ ባላሰቡት ወጥመድ ተይዘው “ተመሳስለን ገብተን እናገለግላታለን!” ያሏትን ቤተክርስቲያን፣ ሀገርና ወገን ለመውጋት፣ ለማድማት፣ ለመቃረን ተዳረጉ፡፡

በቀደምለታ ባሕርዳር ላይ የብአዴን 37ኛ ዓመት ክብረ በዓል አካል የሆነ ብሔርተኝነትን የተመለከተ አንድ የውይይት መድረክ ተኪያሒዶ ነበረ፡፡ እዚያ ውይይት ላይ ዳንኤል ክብረት ተሳትፎ ነበረ፡፡ መሳተፉ ያበሳጫቸው ወገኖች ዳንኤል እዚያ መገኘቱን የሚያሳይ ፎቶ (ምሥለ ዘአካል) ለጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው ያደርሱታል፡፡ እሱም ዳንኤል 37ኛውን የብአዴን ምሥረታ ለማክበር በመታደሙ ማዘኑን ገልጾ ፎቶውን (ምሥለ ዘአካሉን) ለጠፈው፡፡ አጭበርባሪው የወያኔ ካድሬ (ወስዋሽ) ዳንኤልም ከስር ይሄንን አስተያየት አስቀመጠ፦

“ሙሉቀን መረጃህ የተሳሳተ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ብሔረተኝነትን በተመለከተ ሁለት የተለያዩ ሐሳቦች የቀረቡበት ማያ ፕሮሞሽን ያዘጋጀው መድረክ ነው፡፡ የተጋበዙትም የየዩኒቨርሲቲው ምሁራን የክልሉ ኃላፊዎችና ሌሎች ናቸው፡፡ የተዘጋጀውም ለቴሌቪዥን ሾው ነው፡፡ የብአዴን በዓል ያለቀው ሰኞ ነው፡፡ እኔም የተጋበዝኩት ብሔረተኝነት ከሀገር አንድነት ጋር ይሄዳል አይሄድም በሚለው ላይ ሐሳብ ለመስጠት ነው፡፡ የሰጠሁትንም ወደፊት ሲቀርብ እናየዋለን፡፡ በኔ እምነት ሐሳቤን ሊሰማኝ ለወደደ ሁሉ ማካፈል ነው፡፡ ያዘጋጁት ሰዎችም ከታወቀው መንገድ ወጥተው ሌሎች ሐሳቦችም እንዲቀርቡ በማድረጋቸው ይመሰገናሉ!” ብሎ፡፡ ሙሉቀንም ጠልቆ ሳይመረምር ወዲያው ተምቦጅቡጆ ስሕተት እንደፈጸመ አስታውቆ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ነገርግን ምንም ይቅርታ የሚያስጠይቅ ነገር አልነበረም፡፡ ሙሉቀን በሰዓቱ መድረኩ በማን ለምን ዓላማ እንደተዘጋጀ ባያውቅም በዚህ ሰዓት በእጅ አዙር በወያኔ የሚመራ ካልሆነ በስተቀር  በፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ እንዲሠራ ፈቃድ ያለው ነጻ መንግሥታዊ ያልሆነ አካል ፈጽሞ እንደሌለ በመረዳት የዳንኤልን ሐሰተኛ ምክንያት ውድቅ ማድረግ ነበረበትና ነው፡፡ በዕለቱም የአማራ ቴሌቪዥን በዜና ሽፋኑም መድረኩን ያዘጋጀው የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እና ማያ ጋዜጣ መሆናቸውን በመናገር ዳንኤል እንደዋሸውና እንዳጭበረበረው ገልፆ ነበረና፡፡

https://lm.facebook.com/l. 1

እንዲሁም፦

https://lm.facebook.com/

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com