ኢሕአዴግና 15 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድርድር ላይ
26 November 2017
ነአምን አሸናፊ
በአጠቃላይ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓትና ሕጎች፣ እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ
አዋጆችና ሕጎች ላይ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር በመደራደር ላይ የሚገኙት
15 አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁን
የተወሰኑ አንቀጾች ለማሻሻል ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ከስምምነት
ላይ ደረሱ፡፡
በድርድሩ እየተሳተፉ የሚገኙት አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ
ላይ መሻሻል አለባቸው ያሉዋቸውን፣ እንዲሰረዙ የሚፈልጉትንና እንደ አዲስ
እንዲካተቱ የሚፈልጉዋቸውን ነጥቦች አቅርበዋል፡፡
በዚህም መሠረት ለዚሁ ድርድር ዓላማ ሲባል አንድነት የፈጠረው የ11 ፖለቲካ
ፓርቲዎች ስብስብ 39 አንቀጾችን ካካተተው አዋጅ ውስጥ፣ 11 እንዲሻሻሉ፣
አራቱ እንዲሰረዙና ሁለት ሌላ አንቀጾች እንዲጨመሩ በድርድሩ ወቅት አቅርቧል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ደግሞ ሃያ አንድ አንቀጾችና ንዑስ
አንቀጾች እንዲካተቱ የድርድር ሐሳቡን ያቀረበ ሲሆን፣ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ
ንቅናቄ (መኢብን) በበኩሉ ደግሞ አሥር አንቀጾችና ንዑሳን አንቀጾች እንዲሻሻሉ
ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ምንም እንኳን በድርድሩ እየተሳተፉ የሚገኙት አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች
የተለያዩ የማሻሻያ ሐሳቦችን ያቀረቡ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ግን በአዋጁ
ላይ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሐሳብ አላቀረበም፡፡
ከአገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሻሻሉ የቀረቡት በዋነኛነት ብሔራዊ
የጋራ ምክር ቤት አወቃቀር፣ ፓርቲዎች ስለሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ፣ እንዲሁም
ፓርቲዎቹ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸውን ሚና ስለሚያጠናክሩበት
ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላው እንደ አዲስ እንዲካተት ያቀረቡት ሐሳብ ደግሞ፣ የምርጫ
ውጤት የማሳወቅ ኃላፊነት ለታዛቢዎች ይሰጥ የሚለው ቢሆንም ኢሕአዴግ ግን
ውድቅ አድርጎታል፡፡
ኢሕአዴግን ወክለው የሚደራደሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለዚህ ሐሳብ በሰጡት ምላሽ፣
‹‹የምርጫ ታዛቢዎች ድርሻ መጠሪያቸው እንደሚያመለክተው መታዘብ ነው፤›› በማለት
ሐሳቡን ውድቅ አድርገውታል፡፡
ምንም እንኳን ይህን ሐሳብ ውድቅ ቢያደርጉም በአብዛኛው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች
ያቀረቧቸው ሐሳቦች ጠቃሚ ናቸው በማለት፣ በሕግ አሠራር ታይተው ሊሻሻሉ
እንደሚችሉ ኢሕአዴግ አስታውቋል፡፡
በዚሁ አዋጅ ላይ ድርድራቸውን ያጠናቀቁት ፓርቲዎች የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ
ቁጥር 652/2001 ቀጣይ የመደራደሪያ አጀንዳቸው ሲሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች
እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ በአዋጁ ላይ ያላቸውን ሐሳብ በጽሑፍ እንዲያስገቡ
ተወስኗል፣ ከዚያ በኋላ በሚወሰነው ቀን ድርድራቸውን በአጀንዳው ላይ ይቀጥላሉ፡፡
Source – Ethiopian Report