27 ኖቬምበር 2017

ሞሓመድ ዋዴ ሳዳ ኢልባላድ ለተባለ የግብፅ ቴሌቪዥን ጣብያና ድረ ገፅ የሚሰራ ጋዜጠኛ ሲሆን በተፋሰሱ ዙርያ ከሚፅፉ ጋዜጠኞች አንዱ ነው።

“በአገራችን ኑሮ ተወዷል። ለሁሉም ነገር ብዙ እየከፈልን ነው። ህዝቡ ለውሃም ክፈል እንዳይባል ጭንቀት ውስጥ ገብቷል” በማለት ለቢቢሲ ይናገራል።

ሞሓመድ ባለፈው ዓመት ነሀሴ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጎበኙት መካከልም ነበር። “ግድቡ ለግብፅ ህዝብ አንዳች ጉዳት እንደሌለው ፅፌአለሁኝ። እንዳውም ለግብፅ ምን ያህል ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ግድብ እንደሆነ አውቄያለሁ” ይላል።

“ለኢትዮጵያዊ ወንድሞቼ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ውኃቸውን መጠቀምና መበልፀግ ደግሞ መብታቸው ነው። የግብፅ ህዝብ ፍላጎት ውኃው እንዳይቋረጥባት ብቻ ነው” ይላል የአገሪቱ ሚድያ ኢትዮጵያ የናይል ውኃ ልታቋርጠው እንደሆነ በህዝቡ ዘንድ የተሳሰተ ግንዛቤ መፍጠሩን በመናገር።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጋቢት 5, 2004 ዓ/ም ይፋ ሲደረግ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የቃላት ጦርነት ተበራክተው ነበር። በሁለቱም ኣገሮች መካከል የነበረው ግንኙነትም ሻክሮ ነበር።

ይህ በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ግድብ በዓመት ከ6ሺህ ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ የሚታመንበት የ80 ቢልዮን ብር ፕሮጀክት ነው።

ግድቡ በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ግንባታው በቅርቡ 65 በመቶ ብቻ መድረሱ ይነገራል።

በብድርና በእርዳታ መቋረጥ ምክንያት የግድቡ ግንባታ እንዳይስተጓጎል በማሰብም መንግስት ከህዝቡ ጋር በመተባበር ለመስራት ነበር እየተንቀሳቀሰ ያለው።

ከፕሮጀክቱ ጋር ስማቸው ደጋግሞ የሚነሳውና የመሰረት ድንጋዩን ያሰቀመጡት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በግድቡ ዙርያ የሚደረጉ ንግግሮችና የሚሰጡ መግለጫዎች “ቁጭት” አዘል ነበሩ።

የኢትዮጵያዊያኖች “ቁጭት”

ኑሮውን በኬንያ ናይሮቢ ያደረገው አለም አለማዮ ከስድስት ዓመታት በፊት የግድቡ ዜና ይፋ ሲሆን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶት እንደነበር ያስታውሳል።

“የመለወጥ ተስፋና ኃይል የማግኘት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር” በማለት። ነገር ግን የግድቡ ግንባታ ከታቀደው ጊዜ በመዘግየቱ ስሜቱ እንደ ቀዝቀዘ ይናገራል።

“ከሚገባው በላይ ጊዜ የወሰደ ይመስለኛል። ስለ ግድቡ ትዝ የሚለኝ ዜና ሲኖር ብቻ ነው” ይላል።

“አባይ ግብፅ ብቻ የምትጠቀምበት ነው የሚለው ስሜት ላይመለስ የተቀየረ ይመስለኛል”

ወንድወሰን ሚቻጎ ሰይድ ከዚህ በፊት በተለያዩ የውኃ ተቋማት በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት የውኃ ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅትም በስዊድን አገር ሉንድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ የዶክትሬት ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሲሆን በአባይ (ናይል) ‘ሀይድሮ ዲፕሎማሲ’ እና አመለካከት ላይ ጥናት እያደረገ ይገኛል።

“ኢትዮጵያኖች ድሃ ሊሆኑ ይችላሉ ግን ኩሩ ህዝቦች ናቸው። የባርነት፣ የቅኝ መገዛት ታሪክ አለመኖር በራስ የመተማመን መንፈስን ፈጥሯል። የተለየ የኢትዮጵያዊነት ስሜት አለ። በአባይ ላይ ደግሞ አንድ የሆነ አስተሳሰብ ተፈጥሯል” ይላል።

“በኢትዮጵያኖች ዘንድ ያለው አመለካከት የራስህ የሆነ ነገርን ያለመጠቀም ቁጭት ነው። ግጥሞቹንና ዘፈኖቹን ብታያቸው እሱን ነው የሚነግሩህ” ይላል።

ለምሳሌም ያህል የሎሬት ፀጋየ ገብረ መድህንን እና የባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሀንስ (ገሞራው) ግጥሞችን ይጠቅሳል።

“ይሄ አመለካከት ግን የአባይ ግድብ ከተጀመረ በኋላ ተቀይሯል። በራሰ የመተማመን፣ በውሀው የመጠቀም ከፍ ያለ ስነልቦና ተፈጥሯል፤ ኢትዮጵያ እንደ ወኃ ሰብሳቢ፣ እንደ ውኃ ማጠራቀምያ ነበር የምትታየው”ይላል

አቶ ወንደወሰን እንደሚለው ሃገሪቱ የአፍሪካ ቀንድ የውኃ ማማ እየተባለች ነበር የምትጠራው። ግድቡ ግን ይህንን አመለካከት በአመዛኙ ቀይሮታል።

“እኔ በተለየ መልኩ ለማየት እየሞከርኩ ነው” የሚለው ኣቶ ወንድወሰን በዋናነት በአመለካከት (ፖለቲካል ሳይኮሎጂ) ወይም ደግሞ እሱ እንደሚጠራው ‘ሃይደሮሜንታሊቲ’ የተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ እያጠና እንደሆነ ይናገራል።

ለምሳሌ በሁለቱም አገሮች መካከል በአስተዋፀኦ እና በመጠቀም ያለው ግንኙነት ተቃራኒ ነው። ኢትዮጵያ (85 በመቶ) አስተዋፀኦ ታደርጋለች የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ደግሞ ብቸኛ ተጠቃሚ ናቸው።

ስለዚህ “የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ የሚል ተቋማዊም ህጋዊም ሆኖ ቆይቷል” ይላል ይህንን አመለካከት ደግሞ ማናቸውም ድርድርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን በመናገር።

አጭር የምስል መግለጫአቶ ወንድወሰን ሚቻጎ መሀል ላይ

“የትኛው የውኃ ድርሻ”?

በ1959 ሱዳንና ግብፅ ያደረጉት በብዙዎች አግላይ ተብሎ የሚገለፅ ስምምነት ነበር። ስምምነቱ “ውሃውን ሙሉ ጥቅም ላይ ማዋል” የሚል ሲሆን የናይል ወንዝ በግብፅና በሱዳን መካከል ጥቅም ላይ እንዲውል ይደነግጋል።

ያኔ የተፋሰሱ አገሮች ቁጥር 9 ነበር። አሁን 11 ሆኗል።

“ዘጠኝ አገሮች ባሉበት ሁለት ለብቻቸው ስምምነት ሲያደርጉ፤ የታችናው ተፋሰስ ሜንታሊቲ (አስተሳሰብ) ማለት ይሄ ነው። ሌሎችን አግልሎ ራስን ብቻ መጥቀም።” በማለት ሃሳቡን ያብራራል።

ሆኖም በ2015 በስድስት አገሮች የተፈረመው የናይል የውሃ አጠቃቀም የህግ ማእቀፍ በሚል እንደተካው ይታወቃል። አዲሱ የህግ ማእቀፍ ለ1959ኙ ስምምነት እውቅና አይሰጥም።

በቅርቡ የግብፅ ፕሬዚደንት አፈታህ አል-ሲሲ ይህንን ስምምነት መሰረት አድርገው የግብፅ የውሃ ድርሻ አይነካም ማለታቸውን አቶ ወንደወሰን “የትኛው ድርሻ” በማለት ይጠይቃል። “ይህንን ድርሻ ኢትዮጵያ የምታውቀው ስምምነት አይደለም” ይላል።

ሶስቱም አገሮች የግድቡን ከአካባብያዊ ተፅእኖ ስምምነት በተመለከተ በጋራ ሲያካሂዱት የቆዩት ድርድር እክል እንደገጠመው እየተነገረ ነው። የግድቡ ግንባት ከ65 በመቶ መድረሱን እየተነገረ ሲሆን፤ ትልቁ ችግር አሁን ግድቡን እንዴት ነው መሙላት የሚቻለው የሚል ነው።

የምስራቅ ናይል ቴክኒካል ኦፊስ (ኢንትሮ) ምክትል ዴይሬክተር አቶ ፈቅ አሐምድ “በአገሮቹ መካከል ከፍተኛ ትብብር በሚደረግበት በአሁኑ ወቅት እንዲህ ዓይነት መግለጫዎች እና የሚዲያ ቅስቀሳዎችን ማድረግ ማንንም አይጠቅምም” በማለት እንቅስቃሴው ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ለቢቢሲ ይናገራሉ።

እስከአሁን ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች “ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም እና በታችኛው አገሮች ላይ የከፋ ጉዳት አለማድረስ” የሚሉ መርሆች መሆናቸውም ይናገራሉ። “ታሪካዊ መብት” መልሶ የሚነሳበት ጉዳይ እንደሌለ በማስረዳት።

የአባይ ጉዳይ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ ሁኔታዎች ያለበት በመሆኑ ግን በቀላሉ የአመለካከት ለውጥ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም።

“ውኃው በስምምነት ከተጠቀምንበት በቂ ነው፤ ነገር ግን ውኃን ከብሄራዊ ደህንነት ጋር ማገናኘት ለድርድርም አይመችም” ይላሉ።

አጭር የምስል መግለጫጥቁር ዓባይና ነጭ ዓባይ ካርቱም ላይ ይገናኛሉ

‘ሰሌክቲቭ ሚሞሪ’ (የተመረጠ ትዝታ)

የአባይ ጉዳይ የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ኣካል ተደርጎ ይታይ ነበር።

አሁን ደግሞ “ገልፍናይዜሽን ኦፍ ዘ ናይል” አለ ይላል አቶ ወንድወሰን አሁን የተከሰተው አለመግባባት በገልፍ አከባቢ ያለው ቀውስ ነፀብራቅ መሆኑን ይናገራል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኳታር መሄዳቸው በግብፆች ሌላ ትርጉም እየተሰጠው እንደሆነ በመናገር።

“ሌላው በታችኛው ተፋሰስ ያለው ችግር ኢትዮጵያ ሁሌም ዝናብ ያላት አድርገው ነው የሚስሏት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ እንዳለ አያውቁም ሁለቱም ዝናብና ድርቅ የሚፈራረቁባት አገር ነች።

ድርቅ ደግሞ ሌላ ትርጉም የለውም፤ የወሃ ዕጥረት የሚያመጣው ነው፤ እርጥበት ማጣት ነው።”

የናይል ጉዳይ የመሪዎችና የፖለቲከኞች ጉዳይ ሆኖ መቅረቱ ችግሩ ውስብስብ እንዲሆን ማድረጉ ኣቶ ወንድ ወሰን ይናገራል።

“የአባይን ችግር የሚያጎላው የፖለቲከኞች ሜንታሊቲ ነው። ህዝቦች ግን መስማማት የሚችሉ ይመስለኛል” ብሏል።

በ500 ዓመተ ዓለም “ግብፅ የአባይ ፀጋ” ነች በሚል ሄሮድስ የተናገረው እስከ ዛሬ ይጠቀሳል።

“ይህ የማይለወጥ አመለካከት ነው የሚያሳየው። ሄሮድቶስ ይህንን ነገር ሲናገር ስለ የአባይ ምንጭ የሚያውቀው ነገር አልነበረም” ይላል ወንድወሰን።

“ውኃ ሁሌም ይንቀሳቀሳል፥ ይወርዳል። አእምሮኣችን ግን እንደቆመ ነው። ለሚንቀሳቀስ ወንዝ ስታቲክ የሆነ ጭንቅላት ነው ያለን። ይህንን መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል።”