November 27, 2017 13:53

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 18 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ ማዕከላዊ ኮሚቴ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

በዚህ መሰረት የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ አባይ ወልዱ ከድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባልነታቸው ተነስተው በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲያገለግሉ ወስኗል።

በተጨማሪም የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ በየነ ምክሩም ወደ ድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ ብለው እንዲሰሩ መወሰኑን ድርጅቱ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ከስራ አስፈጻሚ አባልነታቸው እና ማዕከላዊ ኮሚቴው ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑንም ገልጿል።
ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ሁለት የስራ አስፈጻሚ አባላትን ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን፥ ማዕከላዊ ኮሚቴው እያደረገ ያለውን ሂስና ግለ ሂስም እንደቀጠለ ነው።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ይህን ያደረገው በድርጅቱ አመራር ዘንድ ከመድረካዊ ተልዕኮ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የታዩ ድክመቶችን ገምግሞ ለማረም መሆኑም ተገልጿል።

የእርምት እርምጃው ማዕከላዊ ኮሚቴው ከሳምንት በፊት ባጠናቀቀው ጥልቅ ግምገማ፥ የአመራር ዳግም ማደራጀትና ማስተካከያ እንደሚያደርግ መግለጹን ተከትሎ የተወሰደ ነው።
ማዕከላዊ ኮሚቴው በወቅቱ በላከው መግለጫ ያለውን ጥንካሬና መሰረታዊ ድክመቶችን ለመለየት ሂስና ግለ ሂስ መጀመሩን አስታውቆም ነበር።

በዚህም በአመራር ስትራቴጂካዊ ፖለቲካዊ ሁነቶች፣ ሁለንተናዊ የልማታዊ ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ እና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙሪያ በጥልቅ በመገምገም ያሉትን መሰረታዊ ክፍተቶች በዝርዝር ማየቱን መግለጹም የሚታወስ ነው።

በዚህ መሰረት በስትራቴጂካዊ አመራር የታቀፈው ማዕከላዊ ኮሚቴ በትግልና በመርህ የተመሰረተ አንድነት አለመኖር፣ በመጠቃቃትና መከላከል ዝምድና ላይ መመስረት፣ የፀረ ዴሞክራሲ ጥልቅ አስተሳሰብና ተግባራትን መኖራቸውን መገምገሙም ይታወሳል።

በተጨማሪም የወጣቱን ትውልድ እና የምሁሩን አቅም በመገንባት፣ በማሰለፍና ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ መሰረታዊ ጉድለቶች መኖራቸውን ገምግሜያለሁ ሲልም ገልጿል።

ከሳምንት በፊት በነበረው ግምገማ ማዕከላዊ ኮሚቴው ከእህት ድርጅቶች ጋር የግንኙነት ችግር እንዳለ መለየቱን ገልጾም ነበር።

በዚህም በትምክህትና ጥበት ሃይሎች ምክንያት በሃገራችን የተፈጠረው ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ለአደጋ የሚዳርጉ አዝማሚያዎችና ተግባራት ለመታየታቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአመራሩ የራሱ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንደነበረው መግባባት ላይ መድረሱን ገልጿል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ትራንስፎርሜሽን ከማረጋገጥ አኳያ መሰረታዊ ስትራቴጂካዊ የአመራር ችግር እንደነበረበት በመገምገም፥ ባለፉት አመታት በተደረገው እንቅስቃሴ በገጠርና ከተማ የተመዘገቡ የልማት ድሎች መኖራቸውን ያረጋገጠ ቢሆንም ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማሳካት አኳያ የህዝቡ ተጠቃሚነት ከፍላጎቱ ጋር ሲመዘን ግን መሰረታዊ ችግሮች እንደነበሩበት በመገምግም ማረጋጋጥ ችያለሁ ብሎም ነበር በመግለጫው።
ማእከላዊ ኮሚቴው የድርጅቱ ነባር ስትራቴጅካዊ አመራርን ጨምሮ የሁሉንም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሂስና ግለ ሂስ ግምገማ በያዝነው ሳምንት እንደሚያጠቃልል ይጠበቃል።