28 ኖቬምበር 2017

አቶ ቢዱ ዳደቻ በአሬሮ ወረዳ ተከስቶ በነበረው ግጭት ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። አሁን ላይ ያቤሎ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ የሕክምና እርዳታ በማግኘት ላይ ናቸው።

በሆስፒታሉ ውስጥ የሕክምና እርዳታ እያገኙ ያሉ ሰዎችን በበጎ ፈቃደኝነት ሲያገለግል ያገኘነው ተማሪ ዲዳ ጋዮ “ቤተሰቦቻችን አርብቶ አደሮች ናቸው። የውጊያ ልምድ የላቸውም። በአንድ በኩል ድርቅ በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነት እያጎሳቆለላቸው ነው” ሲል ይናገራል።

በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሚገኙ ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት አሁን ላይ የተለየ አቅጣጫ የያዘና ክብደቱም የጨመረ ይመስላል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከሚያዋስኑት የኦሮሚያ ዞኖች መካከል በቦረና፣ ባሌና ጉጂ ዞኖች ውስጥ ግጭት እንደ አዲስ አገርሽቷል።

ባለፈው አርብ በቦረና ዞን አሬሮ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች በተፈፀመ ጥቃት የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 23 ሰዎች መቁሰላቸውን የኦሮሚያ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገፃቸው አስፍረዋል።

የድንጋይ ውርወራና ተኩስ ያስተናገደችው የሞያሌ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴም እጅግ ተቀዛቅዟል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሞያሌ ከተማ ነዎሪዎች በግጭቱ ምክንያት ስጋት ላይ መውደቃቸውን ይናገራሉ።

የከተማዋ የደህንነት ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የሚናገሩት የሞያሌ ከተማ ነዋሪው አቶ አቢ ቃሊቻ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ማስተማር እንደከበዳቸው የመንግሥት ሠራተኞችም ወጥቶ መግባት ጭንቅ እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አጭር የምስል መግለጫወ/ሮ ሩፋ ዲዶ

በሞያሌ በተፈጠረው ግጭት ሦስት ልጆቻቸውን ያጡት ወ/ሮ ሩፋ ዲዶ ለሰላሳ ዓመታት ያህል ከኖሩበት ቦታ ሸሽተው አሁን ላይ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

“በፍፁም በሰላም ኖረን አናውቅም። ፀሐይና ብርድ እንዲሁም ረሃብ ኑሯችንን አደጋ ላይ ጥሎብናል” በማለት ከተጠለሉበት ሆነው ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የክልል ፖሊሶች ከድንበር አካባቢ ርቀው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ግጭት በተከሰተባቸው ቦታዎች እንደሚሰፍር ቢያስታውቁም በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ የሚገኙ ወረዳዎች ግን ከግጭት ሊርቁ አልቻሉም።

አሁንም ቢሆን በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች እየተስተዋለ ያለው ግጭት የአካባቢውን ከተማዎች ሰላም እያወከ ይገኛል።

ባለፈው እሁድ በያቤሎ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ግጭቱ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ እንደሆነ ይናገራሉ።

የያቤሎ ሆስፒታል ኃላፊ አቶ ሞሉ ዲማ በግጭቱ ቆስለው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ለሌሎች ታካሚዎች የሚሆን ቦታ መጥፋቱንና ባለሙያዎችም ከአቅም በላይ እየሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የሞያሌ ወረዳ አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ሐሰን ማቢቻ ክስተቱ የወረዳውን ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ መጎዳቱንና ምግብን በመሰሉ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ዋጋ ጭማሪ መታየቱን ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስቴር ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ግጭቱ የኦሮሚያ ክልልን ብቻ ሳይሆን በሶማሌ ክልልም ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት አስከትሏል ይላሉ።

በተጨማሪም ዶ/ር ነገሬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰሞኑን በአካባቢው ባገረሸው ግጭት 27 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን መረጃ እንዳላቸው ጠቁመው፤ የፌደራል መንግሥትም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባልሥልጣናትን ለማናገር ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም የሚመለከታቸውን ሰዎች ለማናገር የምናደርገው ጥረት ይቀጥላል።