ሙኃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት – ብዙ ጊዜ ጊንጥ የሚለውን ቃል ስሰማ ብዙም ትኩረት አልሰጠውም ነበር ዛሬ ግን ጊንጥ አሪፍ ነገር አስተማረኝ፡፡ ይህንን እንድል ያስገደደኝ የዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ አጭር ታሪክ ነው ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡

አንድ ሽማግሌ ውሃ ውስጥ ሊሰምጥ ያለ ጊንጥ ያዩና ሊያድኑት ይፈልጋሉ፡፡ ከዚያም ጊንጡን ከውሃው ለማውጣት እጃቸውን ዘርግተው አነሱት በዚህ ጊዜ ጊንጡ ነደፋቸው:: እሳቸውም ደንግጠው ለቀቁት ጊንጡም ተመልሶ ወደውሃው ገባ፡፡

ሽማግሌው አሁንም የጊንጡን ውሃ ውስጥ መስመጥ ተመልክተው ድጋሚ እጃቸውን ለእርዳታ ዘረጉለት አሁንም በድጋሚ ጊንጡ ነደፋቸው ሲለቁት አሁንም ውሃ ውስጥ ገባ፡፡

ይህንን የሽማግሌውን ትእይንት የሚመለከት አንድ ሰው ወደ ሽማግሌው ጠጋ ይልና ‹‹ይህ እኮ ክፉ ፍጥረት ነው! ጊንጥ እሱን ለማዳን ሲሉ እርሶ እየተጎዱ እኮ ነው›› አላቸው።

ሽማግሌውም እንዲህ ሲሉ መለሱ ‹‹የጊንጡ ተፈጥሮ መናደፍ ነው፡ የኔ ተፈጥሮ ደግሞ መርዳትና ማገዝ ነው፡ ስለዚህ ተፈጥሮዬ ክፉ አደለምና ጊንጡን ከመርዳት አላቋርጥም አረዳዴን ግን አስተካክላለሁ›› አሉና ጥቂት አሰብ አድርገው ተነስተው ከዛፉ ላይ አንድ ቅጠል ቀንጥሰው በቅጠሉ ጊንጡን ይዘው አወጡትና ህይወቱን አተረፉለት፡፡

እኛም እንዲህ ነን ሰውን ለመርዳት ስንሄድ ብዙ ጊንጦች ይነድፉናል፡ ደግ ልናደርግ ስንጓዝ ብዙ እንቅፋቶች ይመቱናል፡፡ ነገር ግን ጊንጡ እንዳይነድፈን እናደርጋለን እንጂ እንቅፋቱ እንዳይመታን እንጠነቀቃለን እንጂ እንዴት ደግ ማድረግ እናቆማለን ?

አንተም አንቺም ሁላችንም እዚህ ምድር ላይ ያለን ሰዎች በሙሉ ስንፈጠር ደግና መልካም ነን፡፡ ግን ሰውን ክፉ የሚያደርገው ተፈጥሮው ሳይሆን መጥፎ አጋጣሚ ነው፡፡

ለዛ እኮ ነው በነዚህ ጊንጦች ስለተነደፍን መልካም ለማድረግ ቅስቀሳ በጎ ለመስራት ማጣራት መጠራጠር በሌላ አይን መመልከት ጀመርን፡፡

እስኪ የዛሬዋን አዲስ ቀናችንን እንዲህ ብንውላትስ ሰው ስንረዳ እንደጊንጥ በሚሆኑ ሰዎች ተሸንፈን መልካም ከማድረግ ከምንቆጠብ የምንረዳበትን መንገድ ለይተን ብናውቅስ፡፡

በነገራችን ላይ ለሰው በጎ ማድረግ ሲባል በገንዘብ ብቻ ይመስለናል አይደለም:: በየቤቱ ገንዘብ ኖሮት ሰው የናፈቀው ህሊና አለ:: ስለዚህ አንዳንዶች ፈገግታችንን አንዳንዶች እኛነታችንን አንዳንዶች መሰማትን ይፈልጋሉና በየደረስንበት ለመልካም ነገር ጊንጥ ፈርተን እምቢ እንዳንል፡፡

መልካም የምታደርጉ ሁሉ ግን ጊንጡንም ቢሆን ከማዳን አትቦዝኑ።