30 ኖቬምበር 2017

የሕወሓት አርማ

ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የሰነበተው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከሃላፊነታቸው በተነሱትና በተጓደሉት የፓርቲው መሪና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ቦታ ላይ ሽግሽግ በማድረግ ተጠናቋል።

በስፋት ሲነገር እንደነበረው ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተወስኗል።

በተጨማሪም አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ፣ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሆነዋል።

ከሌላው ጊዜ በተለየ ለሁለት ወራት ያህል ሲገማገም የቆየው ሕወሓት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ “ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብና አሠራር እንደወረረው፤ የተማረ ወጣት ኃይል አለማካተቱን እንዲሁም እርስበርሱ በመጠቃቃት እንደተጠመደ” አምኗል።

በተጨማሪም የተጠበቀውን ያህል ልማትና ዕድገት አለማስመዝገቡና መሰል ጉድለቶች መታየታቸውን መግለጫው ያትታል።

ድርጅቱ መሰል ትችቶችን የሚያንፀባርቁ መግለጫዎችን ሲያወጣ የመጀመሪያው አይደለም።

ለመጨረሻ ጊዜ ያወጣው መግለጫም ከዚህ በፊቶቹ የተለየ አንድምታ ያለው አልነበረም።

ነገር ግን ባለፈው ሰኞ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አባይ ወልዱና አቶ በየነ ምክሩ ከሥራ አስፈፃሚ አባልነታቸው ተነስተው በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲያገለግሉ ውሳኔ ሰጥቷል።

የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አባል የነበሩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ደግሞ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑም ታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ ሁለት ስማቸው በይፋ ላልተገለፀ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም አስታውቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀሪ አባላቱ ላይ የሚያካሂደው ሂስና ግለ-ሂስ ቀጥሎም ስብሰባውን አጠናቋል።

የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረ-ሚካኤል

“የዘገየ እርምጃ”

የድርጅቱ የቀድሞ አባልና የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሃገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ እልባት ያገኝ ዘንድ ኢህአዴግን የመሠረቱ ድርጅቶች የሚጨበጥ የፖለቲካ ለውጥና የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባቸው በተለያየ ጊዜ ይገልፁ እንደነበር ይታወሳል።

ኦህዴድ ያደረገውን የአመራር ለውጥ አድንቀው ሕወሓትና ብአዴን ግን አስፈላጊውን ግምገማና ማሻሻያ ሳያደርጉ ቆይተዋል ሲሉ ይተቻሉ።

“ማዕከላዊ ኮሚቴው የወሰደው እርምጃ ቢያንስ ከሁለት ዓመት በፊት መሆን የነበረበትና የዘገየ ነው” በማለት ለቢቢሲ ይናገራሉ።

“አዳዲስ ወጣቶች ወደ ድርጅቱ የሚመጡ ከሆነ ትልቅ የለውጥ ምልክት ነው፤ ድርጅቱ ወዴት እንደሚሄድም አመላካች ነው” ባይ ናቸው ጄኔራሉ።

“ጉድለታቸውን ማመናቸው አንድ ነገር ነው። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ ፀረ-ዲሞከራሲያዊ አስተሳሰብ እንዴት እንደሚወጡ መፍትሄ አበጅተዋል ወይ? የሚለው ነው” ሲሉ ይጠይቃሉ።

የቀድሞ የድርጅቱ አመራር የነበሩትና በ1993 ዓ.ም. ለሁለት ሲሰነጠቅ የተገለሉት አቶ ገብሩ አሥራት “ማዕከላዊ ኮሚቴው የወሰደው እርምጃ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ማሳያ እንጂ የለውጥ ምልክት አይደለም” ይላሉ።

“እርምጃው የሕዝቡን በተለይ ደግሞ የወጣቱን ጥያቄ ያልመለሰ ነው” ሲሉም ያስረግጣሉ።

ከዚህ በፊት እርሳቸውን ጨምሮ በርካቶች ሲባረሩ የቀደሞው የድርጅቱ ሊቀ-መንበር መለስ ‘ሙስና’ እና ‘ፀረ-ዲሞከራሲ’ የመሳሰሉ አጀንዳዎችን ተጠቅመው እንደነበር የሚያወሱት አቶ ገብሩ፤ አሁንም ‘ፀረ-ዲሞከራሲ’ የሚለው ስያሜ የተወሰኑ ሰዎችን ለመምታት የተሸረበ እንደሆነ ያምናሉ።

“ለምልክት እንኳን የሚሆን ለውጥ አልታየም። የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑን የሚያሳየው ነገር ደግሞ ግልፅ የሆነ ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ እንኳን አልተነሳም” ይላሉ።

የህወሓት ግምገማ

ወዴት ወዴት. . . ?

ጄኔራል አበበ ከአቶ ገብሩ በተለየ ቢዘገይም ድርጅቱ ራሱን ካደሰ በሃገሪቱ ውስጥ የሚታዩ የተወሳሰቡ ቀውሶች መፍትሄ ይገኝላቸዋል ብለው ያምናሉ።

ጄኔራሉ “ምናልባት ድርጅቱ ለህዝብ ሲታገሉ የቆዩ ወጣቶችን ማካተት ከቻለ ለውጥ ይመጣል” የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

ድርጅቱ ውስጥ ያሉም ይሁን ውጭ ያሉ ወጣቶች ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያሰምራሉ ጄኔራል አበበ።

ምሁራንና ወጣቶችን ወደ ድርጅቱ ማምጣት ከተቻለ ቢያንስ በግማሽ ያህል እንኳን መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚቻል ይናገራሉ።

አረንቋ ውስጥ ነው ያሉት

“ከሁለት ወይም ከሦስት ሰዎች ውጪ በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ ንፁህ አባል የለም” ይላሉ ጄኔራል አበበ። “ጭቃ ውስጥ ነው ያሉት። ከዚህ ጭቃ መውጣት ይችላሉ ወይ?” በማለት ይጠይቃሉ።

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለም መብራህቱ በበኩላቸው “ድርጅቱ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ትግል የተሻለ ነገር ለማምጣት ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

“የመጠቃቃት ሳይሆን የመገማገምና መስመርን የማጥራት ሥራ ነው እየተሠራ ያለው” ብለውም ያምናሉ።

“አሁንም ብዙ አቅም ያለው አመራር አለ፤ ጠንካራና ቅን ወጣቶች ከድርጅቱ ሸሽተዋል ብዬ አላምንም” ባይ ናቸው።

ከዶክተሩ ሃሳብ ሌላ ጫፍ የሚገኙት ጄኔራል አበበ አሁን ያለውን አመራር “የበሰበሰ” እና “ሐሳብ የማያመነጭ” ሲሉ ይገልፁታል። “ድርጅቱ አሁን ባለው አቅም ችግር መፍታት አይችልም” ሲሉ ይደመድማሉ።