December 3, 2017 08:46

 

ስፖርት ለፍቅር፣ ለወዳጅነት፣ ለአካል ማጎልመሻ፣ ለጤንነት ነው። ቀደም ሲል በባህር አና በመቀሌ ከተሞች ክለቦች መካከል በተደረገ ጨዋታ የመቀሌ ክለብ ደጋፊዎች ስታዲየሙ በመግባት የባህር ዳር ተጫዋቾችን መደብደባቸው ፣ ያንን ተከትሎ የመቀሌ ክለብ እንዳልታገደ እንደዉም የባሕር ዳር ክለብ እንደተቀጣ የሚታወስ ነው፡፡ደብዳቢ ዝም ተብሎ ተደብዳቢ ላይ ፍርድ !!!!!

ዛሬ ደግሞ በወልዲያ ከተማ በወልዲያ ክለብ እና በመቀሌ ክለብ መካከል በነበረው የእግር ኳ ውድድር ምክንያት በተነሳው ረብሻ ትልቅ ብጥብጥ መከሰቱን እየሰማን ነው። የወልዲያ ህዝብ ተቃዉሞዉን ተቀላቅሎ ድምጹ ሲያሰማ የነበረ ሲሆን በርካታ ንብረቶችም ወድሙዋል። ታጣቂዎች በሕዝቡ ላይ አስላቃሽ ጭስ ይተኩሱ የነበረ ሲሆን እስከአሁን በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም መትረየስ የታጠቁ አጋዚዎች ከደሴ ወደ ወሊድያ እያመሩ እንደሆነ ምንጮች እየገለጹ ነው።

በአሁኑ ወቅት ወደ ወልዲያ የሚያስገቡ፣ ከአዲስ አበባ መቀሌ ያለዉ መንገድንም ጨመሮ ፣ የወልዲያ አጎራባች መንደሮች ህዝብ ወደ ወልዲያ እንዳይገባ የተዘጉ፣ በወልዲያ ከመቀሌ መጥተው የነበሩ የመቀሌ ክለብ ቡንድ ደጋፊዎች ከወልዲያ ለቀው ወጥተዋል። በስታዲየሙ “አማራ፡አማራ” የሚል ጩኸት በጣም ይሰማ የነበረ ሲሆን የእግር ኳስ ዉድድሩም ተቋርጧል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ትንሿ ብጥብጥ በቀላሉ ወደ ለየለት የዘር ግጭት የመዞር አቅሟ በጣም የሰፋ ነው።፡ሁሉም ነገር የሚሰላውና የሚታየው በዘር መነጽር ነው።

ላለፉት 25 አመታት ሕወሃት ዜጎችን በዘር በመከፋፈል እንደ አንድ ሕዝብ ሳይሆን እንደተለያዩ ሕዝቦች እንዲተያዩ፣ አንዱን ሌላውን እንዲፈራና እንዳይተማመን ሲያደርጉ ነበር። በዚህም ምክንያት፣ ሕወሃት ያልነበረን የአማራ ብሄረተኝነት እንዲወልድ ፣ በትግሬዎችም ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲፈጠር አድርጓል። በወልዲያ የታየውም የሕወሃት ፖሊሲተኛ ቀጥተኛ ዉጤት ነው። ሕዝብ በዘር ላይ ተመርኩዞ ከፍተኛ በደል ስለደረሰበት ተቃዉሞ አነሳ።

ከወይን ግንድ ወይን እንጂ ሌላ ነገር አይበቅልም። ሕወሃት እና ኦነግ ካሰፈኑት ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ፣ ከዘርጉት የዘር አወቃቀር ፍቅርና አንድነት ሊመጣ አይችልም። የፈለገ የትጋማራ የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብ እያሉ ኮንፍራንሶች በማድረግ ፕሮፖጋንዳ ቢነዙም፣ መሰረታዊ የሆኑ፣ በሁሉም ቦታ ሁሉም ዜጎች እኩል የሚታዩበት፣ ሁሉም ዜጎች በሁሉ የአገሪቷ ክፍል የመኖር ዋስትናቸው የተረጋገጠበት ሁኔታ ካልተፈጠረ፣ የአገራችን ፖለቲካ de-ethnicized ካልሆነ የሚለወጥ ነገር አይኖርም።

እንግዲህ ትላንት ነው በጎንደር በአማራና በትግራይ ክልል ሕዝብ መካከል መቀራረብ እንዲኖር ተብሎ ስብሰባ የተደረገው። ስብሰባው ምን ዉጤት አመጣ? ውጤቱ ዛሬ ያየነው የወልዲያ ተቃዉሞ ነው። ያ “መቀራረብ” የተባለው አልሰራም።

በመሆኑም በርግጥ መቀራረብ እንዲኖር ከተፈለገ ያለው የዘር መካረር እንዲቀንስ ከተፈለገ፣ ህወሃት የሚከተለውን ማድረግ አለበት፡

1) የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ መዘጋጀት አለበት
2) የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሁሉንም የሕሊና እስረኞች መፍታት አለበት፡
3) በደህንነቱ፣ በመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ዘንድ ያለው የበላይነት መቆም አለበት።
4) ለብሄራዊ መግባባትን እርቅ መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን እርቁን በቀዳሚነት ማመቻቸት አለበት።