“ማንኛውም የተሽከርካሪ ጎማ ወይም መሪ ምንም ያህል ወደ አንድ ወይም ሌላ አቅጣጫ ቢገፋ፣ቢዞርና ቢንጋለል ሚዛኑን ጠብቆ በመሽከርከር በፊት ወደነበረበት እንደሚመለሠው ሁሉ፤ ከቶውን ሊቀለበስ የማይችል መስሎ የሚታይ ግዙፍ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከተከናወነ በኋላ ሁሉም ነገር እንደገና ወደ ድሮ ቦታው ዞሮ ማፈግፈጉ ወይም ወደ መጀመሪያ ቅርፁ ተመልሶ በነበረበት መዳከሩ ላፍታም አያጠራጥርም”

1984

(ጆርጅ ኦርዌል)

“… Even after enormous upheavals & seemingly irrevocable changes, the same pattern has always reasserted itself, just as gyroscope will always return to equilibrium, however far it is pushed one way or the other “

1984

(George Orwell)

ለስልጣን የቋመጡ እንደ እዝቂኤል ጋቢሳ፣አባስ ገናሞ፣ግርማ ጉተማና ፀጋዬ አራርሳ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ኦሮሚኛ ተናጋሪ የኦነግ አክራሪ ጠባብ ብሔረተኞች ያጨቋቸውን መናጆና መንጋ ጀሌዎችን በፈጠራ ታሪክ በመተብተብ ያለ ልጓም ይጋልቧቸዋል:: ምኞትና ፍላጎት እየተጋጩ እረፍት ይነሷቸዋል:: እውነታን፣ምክንያታዊነትን፣ማስረጃንና መረጃን ሣይሆን ስሜትንና ህልምን እያስጨበጡ ይነዱዋቸዋል:: ያለ ንፋስ የሚበተን አቧራ ያለ ሙቀት በበረዶ የሚቀልጥ ደመና መኖሩን እየሰበኩና በቀን ቅዥት ተሸፍነው እኛ ለናንተ “ህልም” አለን ይሏቸዋል::

የያዙትን ኢትዮጵያዊ ማንነት አስጥለው የማያውቁትን ዓለም እንዲቋምጡ በማድረግና በማስጨበጥ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቅኝት የ19ኛውን ክፍለ ዘመን የፈጠራ ትርክታቸውን ይግቷቸዋል::  ዛሬ ላይ በወያኔ የተጫነባቸውን ጭቆናና የአፓርታይዳዊ ሥርዓት ሣይሆን ጥንት በግል ደረሠብን የሚሉትን “ጉዳትና ቁስል” እያወሡ ከዛሬ ጋር ሣይሆን ከትላንት፣ ከእውነታ ጋር ሣይሆን እነርሱ እራሣቸው ከማይፈቱት ህልምና ቅዠት ጋር ግብ ግብ እንዲይዙ በዘገምተኛ ህሊናቸው ይሠብኳቸዋል::

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነው ከ19ኛውን ክፍለ ዘመን ጋር ያዋጓቸዋል::  እነርሱ በሰማንያ የተጋቡትን የህልም እንጀራና የህልም ዕይታን (wishful thinking & wishful seeing) ምስኪን ደቀመዝሙሮቻቸውን ይጋብዟቸዋል::  የቀቢፀ – ተስፋ ናና ከረሜላ እያስላሡ መርዛማ አረንቻታ ይግቷቸዋል:: በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቅኝት የ19ኛውን ዘመን በምናባቸው ያስዳስሷቸዋል:: ከነባራዊው ዓለም እውነታ ጋር ያፋቷቸዋል:: አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገር፣ አንድ ዓይነት ሃይማኖት ወይም ስነልቦና ያለው የኦሮሞ ማህበረ-ሕዝብ ብቻውን ከኖረ ከጭቆና ተላቆ “ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ” ይሆናል እያሉ በቅዥት ባህር ይቀዝፏቸዋል:: ዛሬ ላይ ሆነው ነገን እንዳያልሙና ለነገ እንዳያቅዱ ችካልና ግርዶሽ ይሆኑባቸዋል:: እነኚሁ ጭፍን ጠባብና አክራሪ ብሔረተኞች ‹ጥሬ ያልሠጧትን ዶሮ እንቁላል ማስፈልፈል፤ ሣር ያልቀለቧትን በቅሎ ማስገር› እንደሚችሉ በመለፈፍና በመስበክ ጀሌዎቻቸውን ኮርቻ ጭነው በቅጥፈት ይገሯቸዋል::

ገና ከፅንሳቸው ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሆኑ ለግል ዝናና ጥቅም የሚራወጡ በገደብ ዐልባ ስሜታዊነትና የግል ዝና የመቃተት ህመም (Histrionic Personality Disorder – HPD) የሚሠቃዩ ቋንጣ እንዳየችው ያቺ ድመት ቀቢፀ ተስፋን ብቻ አንግበውና የአብሮነቱን ጣራ ደርምሠው ዜጎችን ከጋራ ጎጆ ለመበተን የሚቃትቱ ገመምተኞች የህዝብን መፃዒ ዕድል በራሳቸው ወስነው የዋህ እርግቦችን ከሠፈሩበት ዛፍ አውርደው የሠለለ ቅርንጫፍ ላይ ለማሣረፍ እንደሚደክሙና እንደሚታገሉ ያመላክቷቸዋል::

የተጠናወታቸውን የግል የበታችነት ስሜት ከህዝቦች ፍላጎት ጋር እያጋቡና እያጋጩ የነርሱን ከንቱ ህልም ታቅፈውና ተደግፈው ኢትዮጵያዊነትን እንዲንዱና ኢትዮጵያ ሃገራቸውን እንዲያፈርሱ ይገፏቸዋል:: ሽረባና መርዝ ቀምመው ቂም፣በቀልና ደም ያቃቧቸዋል (በዊሊያም ሼክስፒር ድርሠት ውስጥ ኦቴሎ ሚስቱን ዴዝዲሞናን የገደለውና በኋላም ተፀፅቶ እራሱን ያጠፋው በላጎ የቅጥፈት ወሬ ተታሎ እንደነበር እናስታውስ!)።

ይህን መሣዩን ከንቱ ቅዥት ቃዥተውና ምስኪን አሸብሻቢዎቻቸውን አሸክመውና ነድተው በተመሳሳይ ቀመር ከዚህ ቀደም ለስልጣን የበቁ እንደ ወያኔና ሻዕቢያ ያሉ “የነፃ አውጪግንባር” ተብዬዎች የሰበኩትን “ፍትህና ዲሞክራሲ” ነፍገው ለስልጣን ጥማቸው መወጣጫ የተጠቀሙትን የምልዐተ-ህዝቡን ትከሻ ተመልሰው በባሰና በከፋ መልኩ ሲወቅሩና ሲረግጡ አሁን ማየት ብዙ አላስቸገረም ወይም ነቢይ መሆንን አልጠየቀም:: ይህ ጭፍን ጠባብና አክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች ቅዥት እውንና ገቢር መሆን ቢችል ኖሮ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎው ለአንድ ዓይነት ቋንቋ፣ሃይማኖትና ስነልቦና ለመፍጠር የሚደረግ ትግል በሆነ ወይንም አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገር፣አንድ ዓይነት ሃይማኖት ወይም ስነልቦና ያለው ማህበረ-ሕዝብ ከውልደቱ ቀን አንስቶ ዲሞክራሲያዊ በሆነ ነበር::

ለዚህም ነው ‹ቄሣር ክሊዮፓትራን ባይወድ የዓለም መልክ አንድ ይሆን ነበር› በሚል ዓይነት ምልከታና እራስን ብቻ በሚያገለግል ብዥታ(self-serving bias) የሚደፍቋቸው! በጅምላ ፍረጃ (Hasty Generalization) የተካኑት እነዚህ በህልም የሠከሩ ጠባቦች ትላንት ከሚገድሉት ጋር ሲገድሉ፣ከሚቀድሱትና ከሚዘይሩትጋር አብረው ሲጨፈጭፍ፣ሲይስጨፈጭፉና ሲያሸበሽቡ የነበሩ ኦሮሚኛ ተናጋሪ አክራሪ አክቲቪስት ተብዬዎች ዛሬም ተከታዮቻቸውን እየማገዱና በነሱና በነፃነታቸው ስም እየቸረቸሩ ያሉ ፖለቲካዊ በታኝ ሃይሎች (Political centrifugal forces) ናቸው:: ውጤቱ ወይም ጦሱና መዘዙ (unintended consequences) ባይገባቸውም በተግባርም ሊያሣኩ የሚፍጨረጨሩት ሂሣቡ የተወራረደውን፣በተደጋጋሚ በሽንፈት የተገባደደውን ኢትዮጵያን የማፍረስ የቅኝ ገዢዎችን ምኞት ገቢር እንዲሆን ነው:: ጠባብ ብሔረተኞቹ የወያኔ ገዢዎች ድሮም ሆነ አሁን “በነፃነት ግንባር” ስም ያንቀሣቀሱዋቸውንና የሚያንቀሣቅሱዋቸውን ባንዳዎችና ሹምባሾች የተጓዙበትን መንገድ እንዳለ በመቅዳትና በማቀንቀን (copycat) ሊተገብሩም የሚቃጣቸው ጥንታዊውንና ዘመናዊውን ቅዠት ነው:: ሊንዱትና ሊዋጉትም የሚዳዳቸው ረቂቅና ሚስጥራዊ ሐሳብ ወይም የእምነት ቃል የሆነውን ኢትዮጵያዊነትና የመሠረተ-ሃሣቡ ማህተም የሆነችውን የቁርጥ ቀን ልጆቿ በደም በአጥንታቸው እነርሱ ሞተው የታደጓትንና ያኖሯትን ኢትዮጵያን ነው:: ለዚህም እኩይ ተግባራቸው ያሠለፉት በአክቲቪስት ስም በበጎች የተደራጀና በጎች የሚመሩት የጥፋት ብርጌድ ነው::ታዲያ ምን ያደርጋል ታላቁ አሌክሣንደር አንድ ወቅት “በጎች ከሚመሩት የአንበሣ ሠራዊት ይልቅ አንበሣ የሚመራው የበጎች ሠራዊት ይሻላል” ብሏቸው ነበር::

ሌላው እኔን የሚገርመኝና የሚያስታውሰኝም ‹የእንሰሶች ዓመፅ (Animal Farm)› በተሰኘው ልበ ወለድ መፅሐፉ ጆርጅ ኦርዌል የዜጎችን ፍፁም እኩልነት እናሠፍናለን ብለው ስልጣን፣ልዩ መብትና ጥቅም ለጥቂት ምርጦች ጀባ የሚሉ ግብዝ መንግስታትን የተቸበት ምፀት ውስጥ በእንሰሶቹ የመጀመሪያ የአመፅ እንቅስቃሴ ምዕራፍ እንሠሦቹ ሁሉ ተግባብተውበት የነበረው “ሰባቱ ትዕዛዛት” (Seven Commandment) በተሰኝውና በአሣሞቹ የተነደፈው መተዳደሪያ ሰነድ ላይ የተደነገገው (ልክ እንደ ወያኔ “ሕገ-መንግስት”) ‹ሁሉም እንሰሶች እኩል ናቸው (All animals are equal)› የሚለው መመሪያ ያለ እንሰሶቹ እውቅና ወይም ይሁንታ(awareness & approval) ጮሌዎቹ አሳሞቹ (ልክ እንደ ወያኔ) ሥልጣን መንበር ላይ ከተቆናጠጡ በሗላ የበላይነታቸውን በሚያሠፍንና በሚያረጋግጥ መልኩ ተሻሽሎና ተለውጦ ‹ሁሉም እንሠሦች እኩል ናቸው:: አንዳንዶቹ ግን ከሌሎቹ የበለጠ እኩልነት አላቸው (All animals are equal, But some animals are more equal than others)› በሚል አዲስ መመሪያ/motto/ ተተክቶ የአሣማዎቹ መንግስትና አሳማዎቹ ቁንጮ ሆነው በመውጣት በትረ-ሥልጣኑን በመቆጣጠር ያገዱዋቸውንና የነዱዋቸውን እንሰሶች ነው:: በዚሁ መፅሃፍ ‹ናፖሊዮን› የተሰኝው አሣማ ‹አንዱ እንሰሳ ሌላውን ፈፅሞ መግደል አይችልም> ሲልና ሲደነፋ ቆይቶ ‹ለዓመፅ ተነሳስታችሁ ነበር› በሚል ሰበብ በውሾቹ ያስገነጣጠላቸውን የዋህ እንሰሶችን ነው:: ‹የሰው ልጅ ሁሉ ጠላታችን ነው› በሚል ሸውራራ ዕይታ ከአላማጆቻቸው ጋር የነበራቸውን መስተጋብር አፍርሰው የበተኗቸውን እንሰሶች ነው:: የዚህ መፅሐፍ ይዘትና ምፀት ወያኔ በቋንቋ ፌደራሊዝምና በጎሣ ስም አደራጅቶ የነዳቸውን እንደ እዝቂኤል ጋቢሳና ፀጋዬ አራርሳ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ኦሮሚኛ ተናጋሪ የኦነግ አክራሪ ጠባብ ብሔረተኞች ነው። እነዚሁ አክራሪ ጠባብ ብሔረተኞች አንዴ የደነቆሩበትንና የነርሱን የበታችነት ስሜት የሚያካክሱበትን የመገንጠል አባዜ አንግበውና በፈጠራ ትርክት ጠቅጥቀው  ሙዝዝ በማለታቸው ይህን አፓርታይዳዊ የወያኔ የሺፍታ ስርዓት እንዲቀጥልም ምክንያት ሆነዋል። ንፁሃን የኦሮሞ ወጣቶችን መማገዱንና የጭዳ ከብት ማድረጉን ቀጥለዋል።

አሁን የማየው ትይንትም ከዚህ ያልሸሸና ያው ጠባብ ብሔረተኞቹም ሆኑ ገዢዎቹ የወያኔ አሣሞች፤ተናካሾቹም የኦሮሞ አክራሪ ጠባቦች ያው የናፖሊዮን ውሾች መሆናቸውን ብቻ ነው:: የኦሮሞ አክራሪዎችም ሆኑ ወያኔዎች ጠባብ ብሔረተኞች ናችው።ሁለቱም ግንኙነታቸው የአዞና የወፍ ነው። ሁለቱም የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው። ሁለቱም የሚዋጉት ኢትዮጵያዊነትን ነው። መፍትሄውም ለጋራ ጠላቶቻችን የጋራ ግንባር መፍጠር ብቻ ነው። መፍትሄውም ሁለቱንም በጋራ መታገል ነው።

ብደምረው፣ብቀንሰው፣ባባዛውና ባካፍለው ዜሮ እየሆነ ያስቸገረኝ ስሌትም ይህ ብቻ ነው!!