December 4, 2017

ህወሓት በሰባት ገፅ መግለጫው ምንን ሊነግረን ሞከረ?

የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የልቦናዬን በር ከፍቼ ኣነበብኩት። ካንዴም ሁላቴ፣ከሁለትም ሶስቴ። ይህም ኣልበቃ ብሎኝ ደግሜ ደጋግሜ ኣነበብኩት።

በሚቀጥሉት ጥቂት ምዕራፎች የግል ትዝብቴን በራሱ በህወሓት ት አንደበት ላድማጭና ኣንባቢ ለማካፈል እሞክራለሁ።

ሾህን በሾህ ፤ በሬን በገዛ ቆዳው … ፀጋዬ ገብረመድህን ነበር ያለው?

ሲጀመር ሰባት ገፅ ለመግለጫ አያሌ ገፅ ነው። የስብሰባውን ርዝመት ለማመላከት ከሆነ ለአንድ ሳምንት አንድ ገፅ እንደ ገፀበረከት ተችሮናል። ነገሩ ግን ችሮታ ሳይሆን አዲስ የሚነግሩን ከመታጣቱ ይሁን? ያሰኛል።

ህወሓት/ኢህአዴግ” የምንላቸው እኛ ነበርን። ተቃዋሚዎች። የሁለቱን አንድነት እንጂ ልዩነት መለየት ተቸግረን። እነሱም እንደኛው ቸግሯቸው ይሆን? ነው ወይስ የባለቤትነት ጥያቄ መጥቶባቸው? ወይስ ከኢህአዴግ ተነጥለው ለብቻቸው ከመቆሙ ብርድ ብርድ ብሏቸው ይሆን? ለማንኛውም አዲስ አባባል ነው።

ስለብርድ ከወራን ትንሽ ሙቀት የተሰማቸው ከህወሓቶች ይልቅ ደጋፊዎቹ ይመስሉኛል። ህወሓቶች “ስር ነቀል ግምገማ” አድርገን “የአመራር ሽግሽግ” አደረግን ኣሉ እንጂ ከሥርመሠረቱ የነቀሉትን ችግር እንኳን አልነገሩንም። ሰባት ገፅ ከፈጀ መግለጫ ይህንን ብንከጅል በዛብን?

ነው የታሪክ ውደሳው ነሽጧቸው ይሆን? ድርጅታቸው “በሰከነ ሳይንሳዊ አመራር” ፣ “በትክክኛና ••• በጠራ መስመር” የሚመራና “የደመቀ ታሪክ መስራት የቻለ አመራር ባለቤት በመሆኑ ነው?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ደግሞስ “እጅግ የሚያኮራ ተግባራትን የፈፀመ ድርጅት” እንዴት ኣይኮራበትም?

የሚገርመው ከሙገሳውና ከመፃደቁ ቀጥሎ የተባለውን አለመስማታቸው ነው። አዙሪት፣ አዙሪት፣ አዙሪት፣ አዙሪት–አራት ግዜ ኣዙሪት–መባሉን ዘንግተው ይሆናል። ደግሞ አልፈርድባቸውም። ይህን ያክል ጥልቅ የሆነ አዙሪት ውስጥ የገባ ድርጅት እንዴት ሊቀመንበርን በምክትል ሊቀመንበር በመተካት ብቻ ሊወጣው ይችላል የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅ መልሱን ፈርተው ይሆናል።

የግዜም ጉዳይ መጠየቅ ተገቢነት አለው። ለመሆኑ ህወሓትና “እስቲራቴጅክ አመራሩ” አራቴ የማሉበት የኣዙሪት ጉድጓድ የገቡት መቼ ነው? የመንግስት ሥልጣን ሳይዙ? ሥልጣን በብረት ጥርሳቸው ከቆነጠጡ በኋላ? ከስንጠቃው በፊት ወይ በኋላ? “ታላቁ” መሪኣቸው ከመሞቱ በኋላ ነው በፊት? ይህንን አልነገሩንም። ህወሓት/ ኢህአዴግ በትረሥልጣኑን ከተቆናጠጠ ወዲህ ወርቃማው ዘመናችን የትኛው እንደሆነ ቢያስታውሱን ደግ ነበር። ከመለስ ሞት በፊት ከሆነ “የመለስን ለጋሲ ማስቀጠል” ብሎ ነገር ምንድነው? ወይዘሮ አዜብ አደብ ገዝተው እንዲቀመጡ ለማስታወስ ካልሆነ በቀር?

ህወሓት/ ኢህአዴግ “ለህዝብ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት ላይ ሰፊ ድክመት” የታየበት ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ያልነገሩን አሁንም ጆሮኣቸው እንደተደፈነ ስላለ ይሆን? አዙሪት የተገባው “ከታላቁ መሪ” ህልፈት በኋላ ቢሆንማ ዶክተር መረራ “ህወሓት/ ኢህአዴግ የሚናገር አፍ እንጂ የሚሰማ ጆሮ የለውም” የምትለውን ታሪካዊ ትችት በምርጫ 2005/97 የምረጡኝ ክርክር ሳይሆን በ2010/2002 በወረወሯት ነበር።

ያለፈው ይቅር ቢባል እንኳን፣ አሁንስ ጆሮኣቸው የህዝብን ጥያቄዎች ሰምቶ ባግባቡ ለመመለስ ምን ያክል ክፍት ይሆን ብሎ መጠየቁ አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው። ህዝቡ “ልማቱም ዴሞክራሲውም የት አለ?” ሲል እንደ ቆየ እንዳልሰሙ “በአገራችን ታሪክ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት” ገነባንልህ ይሉታል። ከለመድነው አምባገነናዊነት የተለየ አዲስም፣ ፌዴራላዊም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከአዋጅ ባለፈ አላየንም እየተባለ “አዲሲቷን ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ”ን እውን ኣደረኩላችሁ እያለ ይመፃደቃል። ችግሮቻችን “የአፈፃፀም” ብቻ ሳይሆኑ የፖሊሲም ናቸው ብለው እንዳልወተወቱት አሁንም “በገጠርም በከተማም የቀረፅናቸው ፖሊሲዎችና የቀየስናቸው ስትራቴጂዎች ትክክለኝነት” አያጠራጥሩም ይለናል።

እዚህ ላይ ህወሓት እራሱን ሊኮንን ባልተገባ እላለሁ። ህወሓት የህዝብ ጥያቄ ሳይሰማ ቀርቶ መች ያውቃል? እንኳን የህዝብ ጥያቄን ከመኝታ ቤት ሹክሹክታ ጀምሮ የመሸታ ቤት ሃሜት ሳይቀረው የእግር ኮሽታን እንኳን ይሰማል። አለበለዚያ አንድለአምስት ብሎ ለምን ይለፋል? ህወሓት የህዝብ ጥያቄም ይመልሳል። መልሱ በጥይት ባሩድና በእስራት ሆነበት እንጂ!

አሁንስ ይህ ብቸኛው መልሳቸው ላለመሆኑ ድመት ከሁጃጅ መልስ ለአይጥ ሰጠች ከተባለው ማረጋገጫ የዘለለ ምን ኣለ?

ህወሓት ከህዝቡ ይልቅ የ”ውድ የኢህአዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች”ን ዐይኖች በዋርካ ቅጠል ለመጋረድ ሲለፋ ማየት ምንኛ ያስገርማል። የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ መግለጫ እንደሚያስታውሰን “በእህትና አጋር ድርጅቶች መካከል ለበርካታ አስርት አመታት የነበረውን በመርህ እና በትግል ላይ የተመሰረተ ውህደት፣ ለዙርያ መለሽ ስኬት ያበቃን የተግባር አንድነት” ከጊዜ ወድህ “እየተሸረሸረ” መጣ ይለናል። በህወሓት ስሌት “እህትና አጋር” ሁሌም የማያድጉ ህፃናት ስለሆኑ ይህ አባባሉ ሊደንቀን ባልተገባ። ግን ግንኙነቱ “በንትርክና በጥርጣሬ” ባህር የተጥለቀለቀው መቼ ነው? ህወሓት የተስፋዬ ጢሞንና የቢተው በላይን የሞግዚት አስተዳደር ረስቶታል ማለት ነው። ነው ፀጋዬ ገብረመድህን እንዳለን የማይረሳው የተወጋው ሳይሆን የወጋው ስለሆነ ረስተውታል ብሎ ይሆን?

ከመግለጫቸው ግን አንድ ነገር ሲቆጨኝ ሌላው ደግሞ ደነቀኝ። ሀላፊነት መውሰዳቸው እንደ ሃይለማርያም ይቅርታ ፀፀትንና እርምትን የማይጨምር እስከሆነ ድረስ የእሳቶች ሁሉ አቀጣጣይ የሆነችውን “ልክ ይገባሉ” አባባል አለማንሳታቸው ቆጨኝ። በህወሓት ምድር ጡረታ የወጣ የሃገር ጉዳይ የሚወሰንበት ዝግ ስብሰባ መጠራትን እንጂ መጠየቅን አይጨምርም መሰለኝ። በዛው አንፃር ከሰባት ገፅ የህወሓት መግለጫ “ኪራይ ሰብሳቢ” የምትለው አደናጋሪ፣ በዛውም ልክ ባዶ ቃል መታጣቷ ነው መጀመሪያ የደነቀኝ። የለመዱት ሲጠፋ ቅር መሰኘት አይቀሬ ነውና እስቲ ላፋልግ ብየ አዲስ ንባብ ስጀምር የኪራዮች ሁሉ እናት የሆነችውን የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን ማለታቸው እንደሆነ በማያሻማ መልኩ የተቀመጠችውን “ለዕኩልነትና ተጠቃሚነት የከፈሉት እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሳይበቃውና ተከታታይ ገዢዎች ያሳረፉበት ቁስል በወጉ ሳያገግም ለሌላ የተቀናጀ ጥቃት” ተጋለጥን የምትለዋን ሃረግ ኣገኘኋት። ለመሆኑ ደርግን በመጣላቸው የሚያግበሰብሱት ኪራይ መች ተከፍሎ ያልቅ ይሆን? ስለቁስል ካነሱ የሌላውስ የት ይግባ ኣሉ? በራሱ ሃገር እንደስደተኛ ከቄኤው የተፈናቀለና ከራሱ ውጪ ደራሽ ያጣው ግማሽ ሚሊዮን የውስጥ ስደተኛ ምን ይበል? 26 ዐመታት ከማንነቱ በተቀረ ያለ ኣንዳች ጥፋት ወንጀለኛ ተደርጎ ቋንቋው የእስር ቤት ቋንቋ የሆነውስ ምን ይበል?

ባጭሩ ህወሓት መቀሌ ከተመ እንጂ ከተሜ ሆኖ አልተመለሰም። አሁንም የገጠር አራዳነቱ ኣልለቀቀውም። እንዲያውም እርጅና ተደምሮበት እርስ በርሱ የሚጋጭ በሬ ይወልዳል የሚል ተረት ተረት ይተርክ ጀመር። ገና ሥልጣን ተደላድሎ እንዳበቃ በብረት በር ታሽጎ ላይከፈት የተዘጋው ጆሮው አሁንም “ከኣዙሪት” ደብረፅዮን በሚል ታምራዊ ቁልፍ አልከፈት እንዳለው ይገኛል። ዛሬም እንደ ትላንቱ መሰረታዊ ችግሩ የአፈፃፀም ብቻ እንደሆነ አፉን ሞልቶ ሊነግረን ሰባት እንጨት ይቆርጣል። ጉደኛው ህወሓት፣ ጉድ አያልቅበት።