7 ዲሴምበር 2017

 አጭር የምስል መግለጫየኢትዮጵያ ባንዲራ

የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን ማክበር ከተጀመረ እነሆ አስራ ሁለት ዓመት ሞላው፡፡ ሁሌም ግን ሕገ-መንግሥቱ ላይ ስለተቀመጠው እና “እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች” ስለሚለው አገላለፅ ጥያቄ ይነሳል። ለህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት ይህንን ጥያቄ ስናቀርብ “ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ” ሦስት ቃላት እንጂ አንድ ትርጉም ብቻ ያለው ሐረግ አይመስልም፡፡ እንደሳቸው አባባል ይህንን በትክክል ለመረዳት በሕገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች የተዘጋጀውን አጭር ማብራሪያ ማየቱ በቂ ነው፡፡

በማብራሪያው ላይ “በ’ብሔር’ ‘ብሔረሰብ’ና ‘ሕዝብ’ መካከል የመጠንና የስፋት ልዩነት ያለ ቢሆንም…” ይላል፡፡ ስለዚህ ልዩነታቸውን በማብራሪያው ላይ ባይዘረዝርም በደፈናው “የመጠንና ስፋት” ልዩነት እንዳላቸው አስቀምጧል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ሀሳባቸውን ለማጠንከርም ፤ በአማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩትን በተመለከተ አማራን “ብሔር”፣ አገውን “ብሔረሰብ” እንዲሁም ኦሮሞን “ሕዝብ” በማለት በአንቀጹ ማብራሪያ ላይ በመግለጽ በሦስቱ መካከል የመጠንና የስፋት ልዩነት እንዳላቸው ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን በጠቅላላው እንደምሳሌ ኦሮሞን “ብሔር”፣ አፋርን “ብሔረሰብ”፣ ኮሎን “ሕዝብ” በማለትም ማሳያውን ያጠናክራለሉ፡፡

የታሪክ ምሁሩ አቶ አበባው አያሌው የህግ ባለሙያውን ሃሳብ ይጋራሉ። ብሔር አንድ ትርጉም አለው፣ ብሔረሰብም ሌላ ትርጉም አለው ህዝብም እንደዚሁ በማለት። ሕገ-መንግሥታችን ግን ሶስትን ቃላት አንድ ላይ ሰብስቦ የኢትዮጵያን ነገር ቸል ብሎ ‘ስታንሊናዊ’ ብያኔ ይሰጠዋል ሲሉ ያክላሉ አቶ አበባው።

በሕገ-መንግሥታችን ላይ ለሦስቱም አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይኸውም፡- “ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑና የሥነ-ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክአ ምድር የሚኖሩ ናቸው” ይላል፡፡ አቶ አበባው የጋራ ጠባይ ለግለሰብ እንጂ ለብሄር የምንጠቀምበት አልነበረም ሲሉ ይሞግታሉ። የአንድ ብሄረሰብ ጠባይ እንደምን ያለ ነው? ሲሉም ጥያቄ ያቀርባሉ። እንደ አቶ ውብሸት ገለፃ ደግሞ የክልል ሕገ-መንግሥቶች ላይ ትርጉም የተሰጠው በአጠቃላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማለት ሳይሆን የብሔሩን ስም በመግለጽ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የአተረጓጎም ልዩነት አይታይባቸውም፡፡ አቶ አበባው በበኩላቸው ብሔረሰብ የሚለውን በአንድ አካባቢ የሰፈረ የሚለውን ወስደን ለመረዳት የአይሁድ ህዝብን ማየት በቂ ነው። የተለያየ የዓለም ክፍል ላይ እየኖሩ ተመሳሳይ ቋንቋ መናገሩ እና አንድ አይነት ባህል መጋራቱ ብቻ ብሔረሰብ ያሰኘዋል። የግድ በአንድ አካባቢ መስፈር አይጠበቅባቸውም። የተለያየ አካባቢ ሊኖር ይችላል ነገር ግን ተመሳሳይ ባህልና ቋንቋ ይጋራል። ብሄር ግን ልንለው አንችልም ይላሉ።

ሕዝብ የሚለውን ብንወስድ ደግሞ ከቀለም እና ከቋንቋ ባሻገር አንድን ህዝብ አንድ የሚያደርገው አንድ ሉአላዊ አገር መኖሩ ነው። ሕገ-መንግሥታችን እነዚህን ለያይቶ አላስቀመጠም በማለት ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

FDRE Constitution

ታሪካዊ አመጣጡን በጨረፍታ

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ። “መጀመሪያ ሕገ-መንግስቱ ውስጥ መግባት ያለባቸው ምንድን ናቸው ብለን 73 ጥያቄዎች አዘጋጀን። ጥያቄዎቹ በምርጫ መልክ ተዘጋጅተው ወደ ሕዝቡ ወረዱ።” ጥያቄዎቹ ላይ ሕዝቡ ከተወያየ በኋላ በየቀበሌው የተሰጠው ሃሳብ በየክልሉ ከተሰበሰበ በኋላ ጥያቄዎቹን በሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች መሰረት ከፋፈሏቸው። አንቀፆቹ ሲከፋፈሉ 106 ሆኑ።

ሕገ-መንግሥቱን በማርቀቅ ሂደት ውስጥ የደርግ ሕገ-መንግሥትን ያረቀቁ እና ሌሎች ባለሙያዎች በጋራ ተሳትፈዋል በማለት ያክላሉ። ነገር ግን ይህ የሕገ-መንግሥቱ አገላለፅ መብራራት እንዳለበት መጠየቁን አያስታውሱም።

አቶ ውብሸትም በወቅቱ የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት የመሩት አቶ ክፍሌ ወዳጆ “ሕገ- መንግሥቱ በሚረቀቅበት ወቅት በሰፊው ተቃውሞ ከነበረባቸው ክፍሎች መካከል መግቢያው አንዱ ነው፡፡ ከአርቃቂዎቹ ውስጥ የነ ክፍሌ ወዳጆ ቡድን በእዚህ መንገድ እንዳይጻፍ ተቃውሞ ነበር” በማለት ያስታውሳሉ ። ሁሉም እንደሚሉት ግን ሕገ-መንግሥቱ መነሻም መድረሻም በመሆን ያገለገለው ‘ስታንሊናዊነት’ ነው።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መግቢያ አንቀፅአጭር የምስል መግለጫየኢትዮጵያ ህገ መንግስት መግቢያ

ብሔር  ብሔረሰብ እና ሕዝብ

እንደ አቶ ውብሸት ገለፃ ሶቪየቶች ”ብሔርን በታሪክ ሂደት ውስጥ የተከሰተ የሰዎች ስብስብ ነው” ይላሉ፡፡ አንድ ብሔር በመጀመሪያ ደረጃ የሚለየው ባሉት የወል ቁሳዊ የኑሮ ሁኔታዎች ነው፡፡ በአንድ መልክአ-ምድራዊ ክልል ውስጥ መኖር በኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፣ በአንድ ቋንቋ መጠቀም በጋራ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የወል ሥነ-ልቡናዊ ገጽታዎችና ባህላዊ አመለካቶች መከሰት የብሔር መሠረቶች እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ በሶቪየቶች አተረጓጎም ”ብሔረሰብ ከደም አንድነት ይልቅ የተመሠረተው በክልል፣ በቋንቋና በባህል አንድነት ላይ ነው፡፡ ብሔረሰብ የነገድ ከፍተኛ ደረጃ የሆነ የብዙ ነገዶች ውህደት ውጤት ነው፡፡” በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ምርምር ማዕከል፣ ያሳተመው የ”አማርኛ መዝገበ-ቃላት” ስለብሔረሰብ ምንነት በሰጠው ትርጓሜ ላይ ‘ከደም አንድነት ይልቅ የብዙ ነገዶች ውጤት አድርጎ ነው፡፡’

በሶቪየቶች አረዳድ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳየት የሚጥር፣ በማኅበራዊ ሥርዓት ከፍተኛ ጫና ውስጥ የገባ ማኅበረሰብ ነው፡፡ በሂደት የኢኮኖሚ ለውጥ እየተከሰተ ሲሔድ፣ ሰፋ ያሉ የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን ሲፈጥር የብሔረሰብ ማንነቱን እየተወ ከፍ ወዳለ ደረጃ በመቀየር ብሔር ይሆናል ይላሉ፡፡ እንደ አቶ ውብሸት ገለፃ የብሔርና የብሔረሰብ ልዩነቶቹ ቀጭን ቢሆኑም በዋናነት መለያቸው ግን የፖለቲካዊ አቋምን የመወሰን ፍላጎት መኖርና አለመኖር ነው፡፡ እንደ ሶቪየቶች አረዳድ ሕዝብ በመጠንና በስፋት ከብሔረሰብ በታች ነው፡፡ የነገድ ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ በቁጥርም ያንሳል፤ በሥነ-ልቦና ረገድም እንደብሔረሰብና ብሔር ጥብቅነት ወይንም አንድነት የለውም፡፡ በመሆኑም ብሔር ከፍተኛ፣ ብሔረሰብ መካከለኛና ሕዝብ ደግሞ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥትም የተቀመጠው ከዚሁ አረዳድ አንጻር ነው የሚሉ አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦ

ሕገመንግቱን ስለማሻሻል

ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሕገ-መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች የሚለውን በደፈናው ማስቀመጡ ችግር አይደለም።

ከዛ ይልቅ ሕገ-መንግሥቱ ላይ በተደጋጋሚ ጭቅጭቅ ከሚያስነሱት መካከል አንቀፅ 39፣ የፌደራሊዝም እና የባንዲራ ጉዳይ፣ የምርጫ ቦርድ ጉዳይ፣ እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ-መንግሥቱን የማየትና የመተርጎም ስልጣን የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ያገባኛል የሚሉ አካላት በሙሉ ተሰባስበው ቢመለከቷቸው እና ቢሻሻል ጥሩ ነው ብለው ያስባሉ። አቶ አበባው እና አቶ ውብሸትም ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ቢኖር ጥሩ ነበር ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ ውብሸት “ይህንን ማሻሻል ሕገ መንግሥቱን እንደመቀየር ይሆናል፡፡ መግቢያው፣ አንቀጽ ስምንት፣ አንቀጽ 39፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አወቃቀርን መለወጥ ይሆናል” ሲሉ ያጠናቅቃሉ። አቶ አበባው በተጨማሪም “በሕገ-መንግሥቱ የቋንቋ አጠቃቀም ዘፈቀዳዊ ነው። ሕገ-መንግሥት የሚያረቅ አካል በተቻለ መጠን ግልፅ መሆን አለበት።”

“ሕገ-መንግሥቱ ሉአላዊነትን ሲበይን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ባለቤቶች ናቸው ይላል ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በቂ ነበር። የሕዝብን የመንቀሳቀስ ፣ እኩል የመዳኘት መብት እየገደበ ያለው አንዱ ይሄ ስለሆነ መከለስ ካለበት አንዱ ይሄ ነው ይላሉ።

BBC