ከሕጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክስ ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

“ ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ፥ ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም ። ” መዝ 33 ፥ 16 ።
በዓለም ላይ ሰዎች የራሳቸውን ሥልጣን ለማስጠበቅና ዘላለማዊ ለማድረግ ብዙ እንደ ጣሩ ከታሪክ እንረዳለን ። እንደነዚህ ያሉ መሪዎች ሥልጣናቸውን ለማቆየት እጅግ የበዛ ግፍ በሕዝባቸው ላይ ይፈጽማሉ ። ይህን ግፋቸውን የሚፈጽምላቸው የታጠቀ ሠራዊት ያዘጋጃሉ ። ሠራዊቱም ተቀጣሪ ስለሚሆን ያገኘውን ይገድላል ፥ ያሰቃያል ፥ ያስራል ፥ ያሳድዳል ። ግፈኞች ይህን ድርጊታቸውን “ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት ነው” በማለት የመልካም መንግሥት ስም ይቀቡታል ።

ሁኖም ግን ይህ ሁሉ በእውነት ላይ ያልተመሠረተ ተግባር ስለ ሆነ ሥልጣናቸውን ዘላለማዊ ሊያድርገው አይችልም ። በሚያሳዝን ሁኔታ ሁሉም አምባገነኖች የመጨረሻ እድላቸው በአሳፋሪ ሁኔታ ተደምድሟል ።
ለምሳሌ ከሁለት ዓመትና ከዚያም በታች ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት የፈጀው ሄሮድስ ፥ ክርስቲያኖችን በእሳት እያቃጠሉ ለተራበ አንበሳ እየሰጡ ፥ በገደል እየጣሉ ያሰቃዩ የነበሩ የሮማ ቄሣሮች ፣ ሁሉም ዛሬ ስም አጠራራቸው በክፉ እየተነሣ የነርሱ የሆነው ሁሉ እያፈረ ይኖራል ።

በአሁ ጊዜ ሥልጣን የያዙት የሀገራችን አምባገነን መሪዎችም አስፈሪውን ደርግን አባረው ነበረ የተተኩት ፣ ሁኖም ግን እነሱም ከደርግ እጅጉን የከፉ ሁነው ሦስተኛ አሥርታቸውን ሊደፍኑ ነው ። እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ፥ ሥልጣንንም እርሱ ካላከበረ በቀር የጠነከረ ወታደር ማቆሙ ፥ መሣሪያ ማስታጠቁ ሥልጣንን ማቆየት በፍጹም አይችልም ። መጽሐፍ እንዳለ « እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል » ። መዝ 12 6 ፥ 1 ።

በአሁኑ ጊዜ የሕዝባችን አንድ መሆንና በሰላማዊ መንገድ መብቱን ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት አገዛዙ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ትዕግሥተኛውንና በፈሪሃ እግዚአብሔር ላይ በተመሠረተ ጨዋነት የሚኖረውን ሕዝባችንን ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እንዲያመራ እየገፋፋው ይገኛል ። በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ ኋላ ቀር በሆነ ፖለቲካ አገርን ለመምራት መሞክር ፥ በዘመኑ ያለመኖርን ያህል ፥ እንዲህ በዓለም መድረክ ፊት ያጋልጣል ።

የሕዝብን ተቃውሞ በመሣሪያቸው ብዛት ያሸነፉ መሪዎች በዓለም ላይ የሉም ። የሠራዊት ብዛትም ሥልጣንን አስጠብቆ ሲዘልቅ ታይቶ አይታወቅም ። ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ እንደ እንስሳ በመሣሪያ አፍኖ በመግደልና በማሰር ማሸንፍ አይቻልም ። ያ ቢሆን ኑሮ ሂትለር የአይሁድን ዘር ከምድረ ገጽ ባጠፋው ነበር ። ግን ታሪክ እንደዚህ ሲያደርግ አልታየም ። ከህወአት ኢሐዴግ ሲደርስ የሰው ልጅ ታሪክ ራሱን አይቀይርም ። ወደ ማስተዋል ቢመለሱ ይልቅ መልካም ነው ። ለሀገርም ቢሆን ፥ ለሚሳሱለት ገንዘብና ለሚንሰፈሰፉለት ሥልጣንም ቢሆን የሚያዋጣው አውሬ ሁኖ ሰውን አውሬ ማድረግ አይደለም ። መሪ ማለት ሰው ሁኖ ሰውን ሰው ማድረግ ነው ። ሰሎሞን ዳዊት ለልጁ ሰሎሞን “ሰው ሁን»እንዳለ1 ነገሥ 2፡3 ።

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ላይ ሆነን የአውሬነት ሥራ እየሠሩ ሰው ነኝ ማለት እንዴት ይቻላል ?

የሠራዊት ብዛት የሥልጣንን ዕድሜ ሊያረዝም ቢችልም እንኳ ሊያኖር ግን አይችልም ። ምክንያቱ የሰው ልጅ ጊዜያዊ ስለ ሆነ ያረጃል ያፈጃልና ፥ በምትኩ ደግሞ አዲስ ሐሳብ አዲስ ራእይ የያዘ ትውልድ ይተካል ። በዚያው አንጻር የአስተዳሰብ አድማሱ ያድጋል ወይም ይለወጣል ። በዚህ መሠረት የሰው ልጅ ሐሳብ ቀዋሚ አይደለም ፥ ወይ ያድጋል በምትኩ አዲስ እየተተካ እየተሻሻለ ይሄዳል ። ካላደገ ደግሞ ይጠፋል ቀዋሚ ግን አይሆንም ። እስከ አሁን የታወቀው ሐቅ ይህ ነው ። መሪዎች ዘላለማዊ ሆነው አያውቁም፣ ሕዝብ ግን ዓለም እስከምታልፍ ድረስ ቀዋሚ ሆኖ እየበዛ ይኖራል ።

ለዚህ ነው የኢትዮጵያን ሕዝብ « እናንተ አ ብራችሁ የኖራችሁ አሁንም የ ም ትኖሩ ና ች ሁ ። ለ ዕ ለት ጥቅም የቆሙ ፖለቲከኞች አ ያታሏችሁ ፣ እነርሱ ያልፋሉ እንናተ ግን ሁ ል ጊዜ ትኖራላች ሁ ፣ እናንተ ስታልፉ ልጆቻችሁ ይተካሉ » እያለች ቤት ክርስቲያን በየጊዜው የምትማፀነው ። ሕዝቡም ለቤተ ክርስቲያን ጥሪ መልሱን በትብብር በመግለጹ የምናደንቀውና የምናከብረው በዚህ ምክንያት ነው ። ለኢትዮጵያ ህልውናም ዋናው መፍትሔው ይኸው ነው ።

ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው እንዳለው ፣ የትኛውንም ቋንቋ የምትናገሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ! አሁን በኦሮሞኛ ተናጋሪና በአማረኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን የተካሄደው ውይይት መልካም ጅምር በመሆኑ እንዲቀጥል እናበረታታለን ። የሕወሐቱ ውይይት ግን ወደ ጠብ እንጂ ወደ ሰላም የሚወስድ አይደልምና ፥ ሕዝቡ ከሕወሐት ሽንገላ እንዲጠበቅ እንመክራለን ።

አሁንም ከየትኛውም የሕወሐት ፖለቲከኛ ኢትዮጵያ የሚል ቃል ከአንደበታቸው ሲወጣ አልሰማንም አላየንም ። በሕወሐት መንደር አሁንም የኢትዮጵያዊነት ጥላቻ እንደ ሞላ ነው ። አሁንም ዋኖቻቸው አማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ አልተበደለም ባዮች ናቸው ። አሁንም በጉልበታቸው እየተመኩ ነው ። አሁንም በስደት ያሉትን እንኳ ለማሰርና ለመግደል ይዝታሉ ። ግን ይህ ዘለቄታ የለውምና ወደ ልባችሁ ተመለሱና ከአታላይ የፖሊቲካ ማጥ ውጡ እንላለን ።

በአገራችን የሕወሐት ፖለቲካ አቀንቃኞች ሀብት ተሰብስቧል የሚሉት እነሱ በመሣሪያና በሥልጣናቸው ተጠቅመው የደሀ መሬት እየዘረፉ የሰበሰቡት ገንዘብ የሕዝብ ገንዘብ የሆነ ይመስል ለምጽድቅ እንዲያውም ስድብ የሚመስል ማታለለ ነው እንላለን ። ምክንያት የሰበሰባችሁት እናንተ ናችሁ እንጂ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው ሀብት ያከማቸው ? በኢትዮጵያ የተስተካከለ የሀብት ክፍፍልና ክምችትማ ቢኖር በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በመንግሥት አልባ አገሮች በስደት እየተንከራተቱ አያልቁም ነበር ።

ለራሳቸው አገርና መንግሥት በሌላቸው ሀገሮች የሚንከራተት ሕዝብ ፥ በራሱ አገር ሀብት የሚታፈስ ከሆነ ምን እንደዚያ ሊያደርገው ይችላል ?

በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰው እንደ እንስሳ የሚሸጥበት ቦታ እንዳለ መስማት ፣ ይልቁንም ኢትዮጵያውያን የዚህ አስከፊ ሰለባ ሲሆኑ ማየት ምን ያህል ልብን እንድሚያደማ ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶሱ ይገነዘባል ። ኢትዮጵያ አንድ ዶሮ ከሽህ ብር በላይ ይሸጣል ፣ በመንግሥት አልባዋ ሊቢያ ግን አንድ ሰው  በመቶ ዶላር ይሸጣል ። ታዲያ ኢትዮጵያውያን ተሻጮች ከነዚህ መካከል መሆናቸውን ስንሰማ ደግሞ የበለጠ ልባችን ይደማል ። በዚህ ሁሉ በመንግሥትነት ስም የተቀመጠው የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም ቃል ሲያሰማ አይታይም ። በአንጻሩ ግን ሥልጣኑን ለማቆየት የአገር ሀብት እየበዘበዘ ሁለት ወር ሙሉ በስብሰባ ተጠምዶ ፥ ሕዝብ ለማጫረስ ወስኖ መነሣቱ ፥ ከመንግሥትነቱ ይልቅ ሽፍታነቱን በዓለም ፊት አስመስክሯል ።

ወገኖቻችን በዓረብ አገር የሚደርስባቸው እንግልት አሁንም አላቋረጠም ፣ አሁንም ወደ ዓረብ አገር የሚጓዝ ሕዝብ በእጥፍ ጨምሯል ። ከነዚህ ተሰዳጆች መንግሥት ተብየው ትርፍ ያገኛል ። በዚህ ሁሉ ለሕዝብ መልካም የማሰብም ሆነ የመመኘት ምልክት የለም ። አሁን በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ የተፈጸመው ግፍ ጆሯችን ሲሰማ በእውነተኛ ዓለም የምንኖር እስከማይመስል ድረስ ድርጊቱ አሳዝኖናል ። የአንድ መቶ ዓመት አዛውንት በእሥር ቤት ደብድቦ የሚገድል መንግሥት ያለበት አገር በየትኛው መለኪያ እንደ መንግሥት ሊቈጠር ይችላል ። ይህ ሁሉ ችግር እያለ ይህ ሁሉ ግፍ እየተፈጸመ ሌላው ኢትዮጵያዊ መተባበር እንዴት አቃተው ? ትልቁ ጥያቄ ይህ ነው ።

በድርጅት ስም የተዳራጁ የፖለቲካ አትራፊ ወገኖች ይህን ቢያደርጉ አይደንቅም ፣ ግን እንደ ሰው የሚያስበው ወገናችን ምን ነካው ? እስከ መቼ ? ምን እስከሚሆን ነው ይህ ሁሉ ዝምታ? ይህን ጥሪ በዚህ በፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ወር ስናቀርብ በታላቅ ኃዘን ሆነን ነው ።

ጥሪያችን ፣ የቃላት ስንጠቃ ፖለቲካውን አቁማችሁ ፥ በአንድነት ፥ በእርቅ ፥ በይቅርታና በሰላም ሁናችሁ ይህን ነጻነት የተጠማና የተራበ ሕዝብ እርዱት ። ነገ ይህ እድል ላይገኝ ይችላል ፥ ዛሬን ግን እግዚእብሔር እድል ሰጥቷል ነው የምንለው ።

በኢትዮጵያ የምትኖሩ ወገኖቻችን ! በፖለቲካ ስም የዕለት ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ ፖለቲከኞች እንዳያታልሏችሁ አደራ እንላለን ።

እናንተ የተለያየ ቋንቋ የምትናገሩ ናችሁ ፥ ነገር ግን በአንድ ምድር የምትኖሩ አንድ ሕዝብ ናችሁ ፣ ታሪክ የሚያስረዳው ይህንን ሀቅ ነው ። ልዩ ናችሁ የሚሏችሁ ፖለቲከኞች ሌላ ሥራ አጥተው የናንተን ልዩነት ለሥራ ማግኛ ለማድረግ ነው ። እናንተ አብራችሁ የኖራችሁ ፥ ለወደፊትም አብራችሁ የምትኖሩ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ ናችሁ ። እግዚእብሔርን አጋዥ አድርጋችሁ ፥ እርስ በርሳችሁ እየተረዳዳችሁ፥ በጸሎትና በምህላ ሁናችሁ፥ ይህን ክፉ ቀን እንድታሳልፉት በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

አባ ጴጥሮስ የአውስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ