December 7, 2017 05:54

አስራት አብርሃም
አስራት አብርሃም

ህወሀት የስልጣን ኃይል ነው፣ ያውም በስጋ ልጅነት፣ በአብሮ አደግነት፣ በአምቻ ጋብቻ የተሳሳረ ቡድን! ለአርባ ዓመታት ያህል ቦታ እየተቀያየሩ እየገዙ ያሉት ትግራይ እነርሱን ብቻ ወልዳ ስለመከነች አይደለም። ህወሀት ገና በጠዋቱ ሲመሰረት ጀምሮ የድርጅቱ “core nucleus” ከእነርሱ ውጪ ሌላ እንዳያስገባ ሆኖ ስለተሰራ ነው። ህወሀት “አውራጃዊት እያ!” (ህወሀት አውራጃዊት ነች) የተባለችው ገና ዛሬ አይደለም። ድሮ ጫካ እያለች የራሷ ታጋዮች ናቸው እንዲያ ያሏት። አንዳንዱ ወደፊት ለሚይዙት ስልጣን ይጠቅማል ተብሎ ከውጊያ እንዲርቅ ሲደረግ ሌላው ደግሞ ለውጊያ ተልኮ ያልሞተ እንደሆን እንደ መፅሐፍ ቅዱሱ ኦርዮን ሰብብ ተፈልጎለት እንዲሞት ይደረጋል። በዚህ ምክንያትም የተወሰኑ አንታገልም ብለው ወደ ውጭ የሄዱና ትግሉን የተዉ ነበሩ።
በህወሀት ትግል ውስጥ 30% የሚሆኑት ሴቶች እንደነበሩ የሚታወቅ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ቅዱሳን ነጋ፣ ትርፉ ኪዳነማርያም፣ አዜብ መስፍንና መንጀሪኖ ብቻ እየተቀያየሩ የሚሾሙበት ምንክያት ሌላ አይደለም ቤተሳባዊ ትስስር ብቻ ነው ምክንያቱ! ቅዱሳን ነጋ የአቶ ስብሀት ነጋ እህትና የአለቃ ፀጋይ ሚስት ነች፣ መንጀሪኖ የመለስና የአቦይ ስብሀት ዘመድ ነች፣ ትርፉ ኪዳነማርያምም እንደዚሁ የአባይ ወልዱ ሚስት ነች። አዜብ መስፍንም እንደዚሁ የአቶ መለስ ሚስት ስለሆነች ነው እዚህ የደረሰችው። እነርሱ እንዲህ በመንደርና በቤተሰብ እየተሿሿሙ ሌላው እውነቱን ሲናገር “መንደርተኛ” “አውራጃዊ” እያሉ ማሸማቀቅ ይፈልጋሉ። ምክንያቱ ግልፅ ነው፣ ማንም ጥቅመኛ እውነትን ይሰማ ዘንድ አይወድም።

ለያዙት ስልጣን፣ ላገኙት ሹመት “ህይወታቸውን ሰጥተው ስለታገሉ ነው” የሚል ምክንያትም ከደጋፊዎቻቸው አከባቢ ሲቀርብ ይታያል። ስለታገሉ ቢሆንማ ኖሮ የአመራር ስብጥሩ አሁን እንደምናየው ባልሆነ ነበር። በታገለ ቢሆን ኖሮማ የሽሬ፣ የተምቤን፣ የአጋመ፣ የእንደርታ፣ የሳሃርቲ የሳምረ፣ የወልቃየት፣ የሁመራ፣ የራያ፣ የኩናማ፣ የኢሮብ ልጆች ሳይታገሉ ቀርተው አይደለም ከስልጣን ጨዋታ ውጭ የሆኑት። በትግሉ ሂደት የተሳተፉት የራሴን የቅርብ ቤተሰቦች እንኳ ልቁጠር ብል ከደርዘን በላይ ይሆናሉ። ሌላውስ ይቅር፣ ከ250,000 በላይ ታጋዮችና ከ700,000 ሺህ በላይ አባላት አለኝ የሚል ድርጅት እነዚህ ብቻ ሁሌ የሚመሩት እነርሱ የመሪነት ቅብዓ ቅዱስ ስለተቀቡ ነው?! አይደለም፣ በቤተሰብ፣ በመንደር ልጅነት፣ በአብሮ አድርግነት በጓደኝነት፣ በአብሮ ተማሪነት ወዘተ ተደራጅተው፣ ሌላው ወደ ላይ እንዳይወጣ፣ ወደ ስልጣን እንዳይጠጋ ተግተው ስለሚሰሩ ነው።

ክእነርሱ ትውልድ በኋላ የመጣ የተማረ አዲስ የሚባለውማ ጠላታው ነው። ያልታገለ፣ የማያውቅ ጀግና ሊሆን የሚችል አይመስላቸውም። ንቀታቸውን የትየለሌ ነው። ደንቆሮዎችና ትዕቢተኞች ስለሆኑ (ይህም ያላቸው ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት) ከተኩስ ከውግያ ሌላ የጀግንነት አውድ ያለ አይመስላቸውም። ብምንም ዓይነት ሁኔታ የተሻለ ትውልድ መተካት የማይችሉ መካን ፍጥረቶች ናቸው። አንዳንድ በህወሀት የወጣቶች ቅንፍ ውስጥ ታቅፈው የቆዩ ጓደኞቻችን እንደሚናገሩት ከሆነ፣ የህወሀት ኮር አመራሮች ሲበዛ በጣም ራስ ወዳዶች እንደሆኑ ነው። ሌላው እነርሱን ለማገልገል ብቻ የተፈጠረ ይመስላቸዋል፤ እነርሱ ብቻ ባለጽኑ ዓላማ ሌላው ደግሞ ዓላማ የሌለው ይመስላቸዋል። በደም በክፋት በሴራ መንገድ መጥተው ስላሸነፉ ሁልጊዜ ይሄ ዜዳቸው የሚሰራ ይመስላቸዋል። ክፋት መፈልፈል ዘመናዊነት ይመስላቸዋል። ህወሀት ማለት ለእኔ ይህ ነው።

እኔ የሚገርመኝ ነገር፣ አሁን በአንዳንድ ወገኖች እነአባይ ወልዱ ወርደው እነመንጀሪኖ ወደፊት በመምጣታቸው ጮቤ የሚረግጡበት ምክንያት ምንድነው!? የመቀሌ የውሀ ችግር፣ ከኤርትራ ጋር ያለው ችግር እንፈታለን ብሏል?! አላሉም። የትግራይ ወጣት ከስደት እና ከመከራ የሚያወጣ እቅድ ይዘው መጥቷል?! አልመጡም። በፊዴራል ደረጃ እየተነቃነቀ ያለው ገዥነታቸው ለማስጠበቅ ነው የተሿሿሙ ያሉት?! ተማረ የተባለው የህወሀት አባል ትውልድ ደግሞ በዚህ አጋጣሚ ሊያገኝ የሚችለውን ፍርፋሪ እያሰበ ያጨበጭባል፣ እነርሱም እኮ ትውልዱን የሚንቁት በዚህ በዚህ ምክንያት ነው። እርስ በእርስ እንኳ ምን ድርጅቱ ምን እየሆነ ነው ብለው ለመነጋገር አይደፍሩም፣ የአዜብ ነኝ፣ የስብሀት ነኝ እያሉ ስለአሽከርነታቸው ያወራሉ እንጂ!

አሁን እነ አባይ ወልዱ ምን አጥፍተው እንደወረዱ እነዚህኞቹ ደግሞ ምን ሰርተው እንደተሾሙ እንኳ ለአባሎቻቸውና ለደገፊዎቻቸው አልተናገሩም። የቤተሰብ ጉዳይ ስለሆነ እነዚህ በየፌስቡኩ በየቀበሌው ጥሩባ ይዘው የሚጮሁላቸው እንኳ አልነገሯቸውም። ህዝቡንማ ቀድሞውም ከቁም ነገር የሚቆጥረው የለም። አንድ ነገር ግን ስለአዲሱ አመራር መናገር ይቻላል፣ ህወሀት ከ1993ቱ ክፍፍል በኋላ እርስ በእርስ መናበብ የሚችል የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያገኘ ይመስለኛል። ከህወሀቱ ክፍፍል በኋላ በአቶ መለስ የበላይነት ላይ ብቻ የቆመ አመራር ነው የነበረው፤ የአቶ አባይ ወልዱ አመራር ደግሞ እርስ በእርስ መናናቅ የነበረበት፣ የተከፋፈለ፤ የግብና የራዕይ ልዩነት ሁሉ የነበረው ነው ይባላል።

ህወሀት ለመቃወም አንድ ሺህ አንድ ምክንያቶች እንዳሉ የሚታወቅ ነው፤ የአንድ ቤተሰብ ድርጅት መሆኑ ራሱ ለመቃውም በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ብለህ ብትናገር ያለው አበሳ ግን ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ደመኛ ጠላታቸው የሚያደርጉህ ወገኖች አሉ። ለምሳሌ እኔ ባለፈው ሳምንት “ከአንድ ቤተሰብ፣ ከአንድ አከባቢ ናቸው ወደ አመራር እየመጡ ያሉት” ብዬ በመናገሬ ለሁለት ዓመታት ያህል ጋብ ብሎ የነበረውን እየተከታተሉና ስልክ እየደወሉ ማስፈራራት እንደ አዲስ ጀምሯል። ይህ በራሱ የስርዓቱ ነርብ የሚጦዘው ምኑ ሲነካ እንደሆነ በትክክል የሚያሳይ ነው። አንዳንዱ ሰው ከሌላው በበለጠ ሁኔታ ስለህወሀት ወይም ስለአመራሩ ምንነት ሲነግር ያዙኝ ልቀቁኝ እንደሚል ምክንያት ለማወቅ ብዙ መከራከር የሚያስፈልግ አይደለም። በተፈጠረው የኔትዎክ ሰንሰለት ውስጥ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው። የህዝብ ጥቅም አሳስቦት አይደለም።  ሆኖም እውነታው ያ ስለሆነ ከመናገር ወደኋላ ማለት አይቻልም። ህወሀት ማለት የአንድ ቤተሰብ ድርጅት ነው።

ህዝቡ መቼም መውለድ አላቆመም፣ ባለፉት አርባ ዓመታት እንደወትሮው ሁሉ ልጆች ወልዶ አሳድጓል። የተማሩ፣ ብዙ ተአምር ሊሰሩ የሚችሉ፣ አገር መለወጥ የሚችሉ ብዙ ሀሳብ ያላቸው ልጆች ወልዷል። ነገር ግን በየት በኩል አልፈው የሚጠቅም ነገር ይስሩ?! በቤተሰብ የተሳሰረ ድርጅትና ስርዓት ባለበት አገር እንዴት በነፃነት ይንቀሳቀሱ?! ማን ነጻ ሆነው እንዲያስቡና እንዲደራጁ ይፈቅድላቸዋል?! ማንም። ተቃዋሚ ሆነው ቢመጡ ያሳድዷቸዋል፤ በኑሮ ይቀጧቸዋል። ህወሀት ማለት ይሄ ነው።

ይሄ የቤተሰብ ስርዓት በቀለኛም ነው። ስየ አብርሃን ለማስረሳት አሞራ የሚባል ጀግና ከተቀበረበት ጉድጓድ አውጥቶ የሚተካ ነው። አሞራ ጀግና ነው፤ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ነገር ግን በአሞራ ደረጃ ጀግንነት የሰሩ ብዙ ብዙ የህወሀት ታጋዮች አሉ። በቅጽል ስሟ ቀሺ ገብሩ የተባለችው ታጋይ እንኳ በሴትነቷ ከአሞራ እኩል ታሪክ ሰርታ የአሞራ ያህል አትነሳም። ምክንያቱ ግልፅ ነው፣ የተምቤን ህዝብ ስየን እንዲረሳ፣ ሌላ ጀግና አለህ በማለት ለማሞኘት ስለተፈለገ ነው።  ንፁህ የሚጠጣ ውሀ፣ ሲታመም የሚታከምበት ጤና ጣቢያ፣ ለልጆቹ ትምህርት ቤት እንኳ በአቅራቢያው የሌለው ህዝብ በአሞራ ስም እስታዲዮም እንሰራልሃለን ይሉታል!

ህወሀት ማለት በጣም ሚስጥረኛ የሆነ ድርጅት ነው። ከአንድ ወር በላይ ግምገማ ተቀምጠው ስለምን እንደተገማገሙ እንኳ ሳይነገር “እንትና ወርዶ እንትና ተሽሟል” የሚል ድርጅት ነው። የወረደው ባለስልጣን ምን ጥፋት ሰርቶ እንደወረደ አይነገርህም፣ የተሾመው ሰውም እንደዚሁ። በዚህ ምክንያት ለተለያዩ ሀሜቶችና አሉባልታዎች በር የሚከፍት ሁኔታ ይፈጠራል። የወረደው ባለስልጣን “informal” በሆነ መንገድ ስሙ እንዲጠፋ ይደረጋል። ለምሳሌ ስለወ/ሮ አዜብ መስፍን ላይ የተወራ ያለው አስቁኝም፣ አስገራሚም ነው። በወሬ አካፋፈዮቻቸው በኩል “እርጉዝ ነች” የሚል ወሬ እንዲናፈስ የተደረገው። እነዚህ ሰዎች የሴትዬዋን ስም ማጥፋት ነው እንጂ የታያቸው እድሜዋ ራሱ ለእርግዝና የሚሆን ነው ወይ?  የሚለውን ነገር አልታያቸውም። ለነገሩ ማጨብጨብ እንጂ መጠየቅና መመራመር በቀረበት ዘመን ማንም ምን ቢል ልብ የሚለው የለም ብለው ገምተውም ሊሆን ይችላል።

እንግዲህ እንደ መፅሐፍ ቅዱሷ እልሳቤጥ ወይም እንደአብርሃም ሚስት በእስተእርጅናቸው አርግዘው ቢሆን እንኳ ከእርሳቸው ስልጣን ጋር ምን ያገናኘዋል?! ይሄ ስልጣን የቫቲካን አይደለ፣ አቶ መለስ በህይወት የሉ፣ ከሞቱም ብዙ ዓመት ሆኖቸዋል፣ የፍቅር ጓደኛ ቢይዙ ወይም ትዳር ቢመሰርቱ ምንድነው ችግሩ?! አንዲት ታጋይ አስታወሰኝ ድሮ ጫካ እያሉ ግብረ ስጋ ማድረግ ክልክል ነበርና አንዲት ታጋይ ለስራ ጉዳይ ከተማ ይልኳታል፣ እሷ ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅማ ከአንድ በፊት ከምታውቀው ልጅ ጋር አብራ ታድራለች። ይሄ ሌላ እሷን እንዲሰልል የተመደበ ሰው ይህን ነገር ሪፖርት አድርጎ ነበርና ስትመለስ “ሴክስ አድርገሻል” ብለው በግምገማ ወጥረው ይይዟታል። ምንም መፈናፈኛ ቢያሳጧት “ቆይ ግን እናንተ በራሴ እንትን (ስሙን ጠርታ) ምን አገባን ነው የምትሉት? ህወሀት እኔን ነው ወይስ እንትኔን ነው የምትፈልገው?!  አለቻቸው ይባላል።

እንዲህ ዓይነቱ የቤተሰብ ስርዓት በጣም አደገኛና አስፈሪ ነው። ለምሳሌ እኔ ሰዎቹ ያው ራሳቸው መሆናቸው ብረዳም አሁን ሙሉ ትኩረታቸው ሁሉ ወደ መሀል አገር በማድረጋቸው፣ እንደ አዲስ የሚደራጁበት እድል በመፈጠሩ፣ደመኛ ጠላት አድርገው የሚያስቡትን ሰው ላይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል ሀሳብ አለኝ። ለምሳሌ “የህወሀት ፖለቲካ የአድዋ ፖለቲካ ማለት ነው” ብዬ በመናገርዬ አንዱ ሰፈሬ ድረስ መጥቶ “አንተ ለአድዋ ካለህ ጥላቻ የተነሳ እንዲህ የምትለው” ብሎ ሰድቦኛል፤ አስፈራርቶኛል። ይሄ ሰው በሌላ አካል ተልኮ ይሁን በራሱ ተነሳሽነት ያድርገው ለማወቅ አልቻልኩም። በአከባቢው ያገኘኋቸው ፖሊሶችም ሊይዙት አልደፈሩም። “እንደዚያ እንዳለህ በምን እናውቃለን?” “ምስክር አለህ ወይ?” “ደግሞስ አልደበደብህ? ንቀህ ብትተው ምናምን” እያሉ ከእኔ ጋር ሲጨቃጨቁ ነው ያስመለጡት።

በነገራችን ላይ  አድዋ ለማን ርቆ ለማን ቀርቦ ነው እኔ የተለየ ጥላቻ የሚኖረኝ?! የተምቤን ልጅ ብሆንም ከአድዋ ጋር አንድ ወንዝ ነው የሚለየን። ከዚህ በላይ ደግሞ ያስተማርኩብት የኖርኩበት ከተማ ነው። እንደማነኛውም የትግራይ ህዝብ ደግ ህዝብ፣ ራሱን ችሎ፣ ራሱን ሆኖ የሚኖር ህዝብ ያለበት ቦታ ነው። እንደሌላው የትግራይ አከባቢ መሰረታዊ ልማት ያልተሟላለት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚታይበት አከባቢ ነው። ነገር ግን በአድዋ ልጅነት፣ በአብሮ አደግነት፣ ቤተሰብነት፣ በስጋ ዝምድና፣ በአምቻ ጋብቻ ተደራጅተው ስልጣን የያዙ፣ ባለሀብት የሆኑ፣ ኢኮኖሚውን የተቆጣጠሩ፣ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ የሆነላቸው፣ አድራጊ ፈጣሪ የሆነው የሚኖሩ ግለሰቦችና ቡድኖች የሉም ማለት አይደለም። በጣም ነው ያሉት።

እነዚህ ናቸው ከሁሉም በላይ የሚያስፈሩት። እነዚህ ናቸው በትግራይ ህዝብ ስም እያተረፉ፣ ግፍ እየሰሩ ያሉት። በዚህ ምክንያትም ነው ከእነዚህ ግልጽና ህቡእ ቡድኖች ጋር ጸብ ውስጥ እየገባን ያለነው። ምክንያቱም በእነርሱ ጦስ የትግራይ ህዝብ በተለይ ደግሞ ንፁሀን ዜጎች ዋጋ እየከፈሉ ስለሆነ ነው። ከዚህ ውጪ ከእነዚህ ወገኖች ጋር የተለየ ጥላቻ ሊኖረን አይችልም። እንደምናየው በመለያየትና በመከፋፈል ላይ የቆመ ስርዓት ደግሞ አማራ፣ ኦሮሞ ትግሬ እያለ በመከፋፈል ብቻ አልቆመም፣ ይሄው በትግራይ ውስጥም አድዋ፣ ሽሬ፣ ተንቤን፣ እያለ እየከፋፈለን ነው የሚገኘው፤ ለዚህ ነው በዜግነት መብት ላይ ብቻ የተመሰረተ ግንኙነት ብቻ ነው ሊኖረን የሚገባው እየተባለ ያለው።

በጥቅም በጓደኝነት በመንደር ልጅነት ከተሰባሰብክ በኋላ ግን ከሌላው ጋር የጋራ አጀንዳ ሊኖር አይችልም። በውሸት አንድ ነን ስላልክ ብቻ አንድነት አይመጣም። እንዲህ በመሆኑም ነው ስለህወሀት አንድ ነገር በተናገርክ ቁጥር “አድዋ ስለምትጠላ ነው” እየተባለ ያለው። እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም ህወሀት አውራጃዊ የሆነ የስልጣን ኃይል ነው። በክብ መዋቅር የተዋቀረ፣ እንደ ቀይ ሽንጉርት የተነባበረ ሽፋን (leve of layers) ያለው፣ የውስጠኛው ኮር ኒኩለስ የአቦይ ስብሀት ኔትዎርክ ነው፣ ቀጥሎ ያለው ሰርክል አብሮ አደግነት ነው፣ የአድዋ ልጅነት ነው፣ ቀጥሎ ያለው ሰርክል የትግራይ ልጅነት ነው፣ ቀጥሎ የሚመጣው ሰርክል ኢህአዴግነት ነው። ይሄ አደረጃጀቱና ልዩ ልዩ መልክ መያዙ ነው እጅግ በጣም አደገኛ የሚያደርግው። የማፊያ ስርዓት እንኳ በዚህ መልኩ በተወሳሰበ ሁኔታ የሚደራጅ አይመስለኝም። በአጠቃላይ ካየነው ህወሀት መፍረስ ያለበት እንጂ መታደስ የሚችል ስርዓት አይደለም። መታደስ አይችልም።