December 8, 2017

ሐይለገብርኤል አያሌው (የቀድሞው መዐሕድ አመራር አባል)

የመቀሌው ስብሰባ ማራቶን ሹምና ሽረቱ የመግለጫ ጋጋታው የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት ከግር ጥፍሩ እስከ ዶቃ ማሰሪያው በንጹሀን ደም ለጨቀየው የሌባና የሰው በላ የወያኔ ቡድን ለዳግም ግፍ ለበለጠ አፈና በሚያመቸው መልኩ የጭካኔ ጠበብቶቹን መሪ አድርጎ ሊዘምትብን መዘጋጀቱን አውጇል። የሕዝብ ለህዝብ መተላለቅን የሚሰብኩ ጀሌዎቹን አሰልፎ በሕዝባችን ላይ ከነመርገሙ ሊጫንብን አፈር ልሶ ተነስቷል::  የህወሃት ትዕቢት ጨለምተኝነቱና ለህዝብ ያለው ንቀት ድንበር የለሽ በመሆኑ አማራና ኦሮሞን በእሳትና ጭድ መስሎ በአደባባይ የተናገረውን ስቅላት ይገባው የነበረን ጸረ ሕዝብ ግለሰብ ከፍ ላለ ወንበር መሾም ነደው እንዲጠፋ በተመኘላቸው ሕዝቦች ላይ ሌላ ዙር የከፋ ዘመቻ አቅዶ ለመነሳቱ አመላካች መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም::

የትግሬ ነጻ አውጪውን ወያኔን በተንኮሉ አይነት በጭካኔው ደረጃ በክፋቱ ልቀት ሰይጣንን በእድሜ ካልሆነ በተገባር እንደማይስተካከለው በማህበራዊ ድህረገጽ ያየሁት አባባል የወያኔዎችን ባህሪ በሚገባ ያሳያል። ኢትዮጵያን በመሰለ የደጎችና የመንፈሳዊያን ምድር እንዲህ በድርጊቱ ከዲያቢሎስ የከፋ አረመኔ አገዛዝ በታሪኳ ገጥሟት አያውቅም። ከአንድ መሐጸን የፈለቁትን አቤልና ቃዔልን ደም ያፋሰሰ ጋኔል ፤ በትግሬ ነጻ አውጪ ቡድን ተበልጦ በዘመናት አብሮነት እንደ ሰርገኛ ጤፍ ተቀላቅለው የኖሩትን የአማራና የኦሮሞ ወንድማማች ነገዶች በሃሰት ወሬ ፤ በጥላቻ ቅስቀሳና ፤ በፈጠራ ታሪክ የተሳሰሩበት ገመድ እንዲላላ  አብሮነታቸው ጥርጣሬ እንዲያጠላበት የማድረጉ ሴራ ተሳክቶለት ላለፉት 26 አመታት ፍላጎቱን ለማሳካት አስችሎት ቆይቷል።

በበዳይና ተበዳይ ትርክት ባለፍ የታሪክ ምጣድ ላይ ሆንን ስንፋጅ ወያኔዎች የዘረፋና የአፈና መዋቅራቸው ሃዲድ ጓዳችን እስኪደርስ ሲዘረጉት ለመንቃት ባለመቻላችን ገና በግዜ በቀላሉ እንገላገልው የነበረውን  የወንበዴ ቡድን ዛሬ ነቅተን ለመታገል ስንነሳ ብዙ መስዋዕትነት ባላስከፈለን ነበር ። ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየጎለበተ ያለውን የአማራና የኦሮሞ አብሮነት ይበልጥ እንዲጠናከር  የቅልበሳ ሰለባም እንዳይሆን ነቅቶ መገኘት ግድ ይላል። ሂደቱን በተገቢው መንገድ በተደደራጀ መልኩ የተናበበ የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመፍጠር መንገድ ጠራጊ እርምጃዎችን በየደረጃው መከተል ይኖርብናል። ሃገራችንን ከብተና ነጻነታችንን ከግፈኛ ለመታድግ  የፖለቲካ ልሂቃኑና የሕዝብ ድርጅቶች ለዘሌቄታዊና ለሰላማዊ ሃገር ምስረታ በሚበጅ መልኩ አብሮነትን ሊያጠናክር የሚችሉ መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀትና በተግባር ለመተርጎም  መትጋት ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ አንጻር ማንም ምንም ይበለው ከበስተጀርባው ያነገበው ስውር ተልዕኮ ይኑረው አይኑረው ፖለቲካዊ ፋይዳው፣ታክቲካዊ አሰላለፉ በፈለገው ደረጃ ይተርጎም የባህር ዳሩ የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካና የማህበረሰብ መሪዎች የጋራ ምክክር መድረክ ታሪካዊነቱን ማንም ሊነሳው አይችልም።ይህ ያልተለመደና ያልተጠበቀ የፖለቲካ ቡድኖች ግንኙነት ሊያስገኝ የሚችለው ማህበራዊ፣ሰብዓዊና ፤ አብሮነታዊነትን የሚያጠናክር ተግባር ተምሳሌታዊ  ነው። በሳትና ጭድነት ተፈርጀው እርስ በእርሳቸው እንዲጫረሱና እንዲጠፋፉ ዕቅድ የተነደፈላቸው ወገኖች የህወሃትን የአፓርታይድ ከፋፍለህ አፋጅተህ ግዛው የጥፋት ፖሊሲ ያከሸፉበት አጋጣሚም ነው። የአማራውና ኦሮሞው የዘመናት አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር ታሪካዊ ክንውን እና አዲስ ምዕራፍ ከፋችም ሆኗል።

ስለነዚህ ሁለት ኢትዮጵያዊ ታላላቅ ነገዶች ብዙ ተብሏል። እንደ ሁለት ጎረቤታማች ሕዝቦች እስኪታዩ ድረስ ለመለያየት ተደክሟል። እሳትና ጭድ ሆነው የትግራይ ቀማኛና ሰው በላ የናዚ ድርጅት እንጀራ መጋገርያ ሆነው እንዲኖሩ ያልተጫረ ክብሪትና ያልተረጨ ነዳጅ አልነበረም። ክፉ ወያኔዎች በገነቡት የጥላቻ ግምብ አማራና ኦሮሞን የመለያየት ሴራቸው እስከዘላለም እንዲቀጥል ሰይጣናዊ  ዘመቻ ሲያቀናብሩ ኖረዋል። በዚህ ሁሉ ሁኔታ በወያኔ አዝማችነትና ጥላቻን በተጋቱ የዋሃን ስሜታዊ  እርምጃ የብዙዎች አንገት ተቀልቷል። ክፋትን በሰበኩ የጥላቻ ደቀ መዛሙርት ተነሳሽነት ብዙ ሺዎች ወልደው ከከበዱበት ፣ ጥረው ግራው ካፈሩት ሃብትና ንብረት ተፈናቅለው ለስደትና እንግልት ተዳርገዋል።

በዚህም ብዙ ቤተሠብ ፈርሷል። አረጋዊያን ያለጧሪ፣ህፃናት ያለአሳዳጊ ሜዳ ላይ ተበትነው ቀርተዋል።አምራቹ ዜጋ፣የሃገር አሌኝታው አርሶ አደር በደረሰበት ግፍ ለጎዳና ተዳርጎ ፤ ምጽዋት ጠባቂ ከርታታ የሃገር ሸክም ሆኖ የሃገሪቱን ማህበራዊ ምስቅልቅል የከፋ አድርጎታል።ተዘርዝሮ የማያልቅ እጅግ ብዙ ግፍ ምንም በማያውቁ ንጹሃን ዜጎች ላይ የብሄር ማንነታቸውን ምክንያት በማድረግ ተፈጽሟል። ከዚህ ሁሉ ግፍ በሗላ የኦሮሞ ሕዝብ ያገኘው አንዳችም ትርፍ የለም። እንዲያውም ከአጋር ወንድሙ በመለየቱ ምንም እንደማያመጣ እስከመቆጠር ወርዶ በመብትና በሐብቱ ላይ ባለግዜዎች ፍጹም ወሳኝ የሆኑበት ጭቆና ነው ተንሰራፍቶ የቆየበት። ለዚህ ሁሉ ሰይጣናዊ የጥፋት ዘመቻ አቀናባሪ ወያኔዎች ይህ ሁሉ ጅምር እንጂ ፍጻሜ አልነበረም። የጥላቻ መሃንዲስ፣የዘራፊዎች ሕብረት፣የሰው በላው ስርዓት ምንጭ የሆነው ሕወሃት ከመነሻው ከደደቢት በረሃ ይዞት የመጣውና ያነገበው እኩይ ዓላማውና ዕቅዱ በማያባራ የመጠፋፋት  አዙሪት አማራና ኦሮሞውን ማግደው እስከዛሬ በዘረፉትና ወደፊትም በሚዘርፉት የህዝብና የሃገር አንጡራ ሃብት የቅንጦት ሕይወታቸውን  ያለተቀናቃኝ ለማጣጣም ነበር።

ከዚህ አስፈሪ ሐገር አፍራሽና ትውልድ በታኝ የጥፋት አዙሪት ሕዝባችንን ለመታደግና ሐገራችንን ከብተና ለማዳን የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችና ልሂቃን በጋራ ለማሰለፍ እልህ አስጨራሽ ጥረት ሲካሄድ ቆይቷል።ፖለቲከኞቹና ልሂቃኑ በሚያካሂዱት ገመድ ጉተታና አሮጌ  የታሪክ ሂሣብ ለማወራረድ በፈጠሩት ጊዜውን ያልዋጀ ፉክክር አስፈላጊው የትብብር እንቅስቃሴ ሲጓተት ቆይቷል።

በእርግጥ የኢትዮጵያ ሐገራዊ ንቅናቄ በይፋ ከተቋቋመ ወዲህ በተለይ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይል ለትብብሩ ራሱን አዘጋጀቶ ሲያቀርብ የአማራው ኤሊት ከአደባባዩ ጠፍቶ ሂደቱ በእንጥልጥል ላይ በነበረበት ወቅትና ሁኔታ ላይ የህወሃት የትሮይ ፈረስ የተባሉት ቅልብ ዘቦቹ ኦህዴድና ብአዴን የሕዝብ ኃይል በፈጠረው ማዕበል ተገፍተው የወያኔን የመጠፋፋት ሴራ ለማክሸፍ የሚያስችል ተግባር ለመፈጸም መነሳታቸው በተቃዋሚው ጎራ ለተሰለፍነው ሊያሰራና ልንሰራበት የሚገባውን አጀንዳ በመነጠቃችንና ባለማድረጋችን ለሃፍረት የዳረገን ሲሆን ለብአዴንና ኦህዴድ ምስጋና ማስገኘቱን በፍጹም ልንክደው የማንችለው ሃቅ ሆኗል። ኢትዮጵያ ሐገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። የኦሮሞና የአማራው ማህበረሰብ ሕልውናም የከፋ አደጋ ተደቅኖበታል። የትግራዩ አናሳ ቡድን  የኢትዮጵያን ሕዝብ ረግጦ ለመግዛትና የዘረፋ ስርዓቱን ለማጽናት በሃገሪቱ አብላጫ ሕዝብ የሚወክሉትን የአማራና የኦሮሞ ማኅበረሰቦች እርስ በእርስ እያፋጀ መቀጠል የማያስኬደው  እየሆነ መጥቷል።  የክፋቱ መጋረጃ ተገልጦ የፀቡ ምንጭና የሴራው ቀማሪ የታወቀበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ሁለቱንም ወገን በኃይል ደፍጥጦና የኅብረተሰቡን ቅስም ሰብሮ በወታደራዊ የበላይነት አፓርታይዳዊ አገዛዙን ለመታደግ የአፈና ዕቅዱን እየዘረጋ ይገኛል።

አማራና ኦሮሞ እንደ ድርና ማግ የተጋመዱ ፣እንደ ሠርገኛ ጤፍ የተቀላቀሉ ዘመን ተሻጋሪ ዕድል ፈንታና ጽዋ ተርታቸው አንድ የሆነ ወንድማማች ነገዶች ናቸው። የአማራውና የኦሮሞው የጋራ ኅብረት ለኢትዮጵያ ኅልውና መረረጋገጥ ጽኑ መሠረት ነው።  ለዚህ ነው የአማራውና የኦሮሞው ኅብረት ያስፈለገው አማራው ለኦሮሞው ወይም ኦሮሞው ለአማራው ውለታ ሰጪና ተቀባይ እንዲሆን ሳይሆን አንደኛው ለሌላኛው ኅልውና እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው።ለረጅም ዘመናት በደምና በአጥንት ተጋምዶ የኖረው የኦሮሞውና የአማራው አብሮነት የተፈጠረበትን መላላት አጥብቆና አጠናክሮ የጋራ ጠላቱን በተባበረ ክንዱ በመደቆስ በዴሞክራሲና በእኩልነት ላይ የቆመ የኢትዮጵያን አንድነት  በፀና መሠረት ላይ ለማቆም የሚያስችል እምቅ ኃይል አለው። በጠላት ሴራ ተቋርጦ የቆየውን ኅብረትና አንድነት በማደስና በማጥበቅ የኢትዮጵያ ህልውናን በአፋጣኝ ለመታደግ አማራውና ኦሮሞው ግንባር ቀደም ሆነው  መገኘት ይኖርባቸዋል። በዚህ ፈታኝ ወቅት በአስቸኳይ ኢትዮጵያን እንደሃገር  ለማቆየት ከአማራውና ኦሮሞው ሕዝብ ጎን በመሰለፍ በተለይ በውጭ የሚገኘው ወገን በነቃና በተደራጀ መልኩ ለሃገር ውስጡ ዕንቅስቃሴ ደጀንና አለኝታ መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል።

በአንድ ሃገር የፖለቲካ ሥርዓት ምስረታ ይሁን ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሕዝብ ቁጥር ለውሳኔ አሰጣጥና ለለውጥ ቅልጥፍና ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታወቃል። ከዚህ አንጻር በሃገራችን ካለው ወቅታዊ ዘውግ ተኮር አሰላለፍ አኳያ የኦሮሞና የአማራ ማህበረሰብ ከሃገሪቱ ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር ከ70 በመቶ የማያንሳውን የሚወክሉ በመሆናቸው የእነዚህን ሁለት ትልልቅ ብሔሮች  በጋራ ማሰለፍ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ወሳኝ አጀንዳ ነው። ሃገር ከብተና እንዲተርፍና አስተማማኝ ለውጥ እንዲመጣ የሚመኝ የየትኛውም የፖለቲካ ይሁን የዘውግ እባል በመጀመሪያ ይህን ጥሬ ሃቅ በቀና መንፈስ መቀበል ይኖረበታል። የኦሮሞና የአማራ አብሮነት በጠንካራ መሰረት ላይ ከቆመ ለሁሉም ሕዳጣን ሕዝቦች የሰላምና የእኩልነት  ዋስትና ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም ። አማራውና ኦሮሞውን በዋናነት መዕከል አድርጎ በሕብረብሔራዊ መልክ ይሁን ፤ በብሄር ወይም በጆግራፊያዊ አሰፋፈር የተደራጁትን ሁሉ ወደ አንድ የጋራ የትብብር መድረክ በማምጣት ህወሃትን በማስወገዱ የጋራ ዘመቻ ሓቀኛ ትብብር መፍጠር  ሃገራችንና ሕዝባችንን ለመታደግ ያለው ብቸኛ አማራጭ ይህን እውነት ተቀብሎ መቆም ሲቻል ነው።

እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

አሜን!!!