December 9, 2017

ግልፅ ደብዳቤ ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መሪዎች
ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
ይህን ደብዳቤ የምፅፍላችሁ እንደ አንድ ለሃገሩ ተቆርቋሪ ግለሰብ ሆኜ ሃሳቤ እናንተ አሁን በምትመሯት ኢትዮጵያ ላይ ፍቅር፣ እንድነት፣ ሰላም፣ እኩልነት እና ዲሞክራሲ ይሰፍኑ ዘንድ ይረዳ ይሆናል በማለት ነው። ቀጥሎም፣ በኢህአዲግ ውስጥ የተደራጁት የእናንተ አባላት ለሆኑት ለ ኦሮሞና አማራ ክልሎች ፕሬዚዴንቶች ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊነትን እንዲያራምዱ በመከርኳቸው መሰረት ሃሳቤን ብትጥሉትም ብታፀድቁትም የበኩሌን እንደ መርህ እናንተንም ለመምከር ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ ህሊናዬ ይህን ደብዳቤ ፃፍላቸው ስለ አለኝ ለህሊናዬ ታዛዥ ሆኜ ነው።


ተጋሩን፣ ጉራጌን፣ አማራን፣ አፋርን፣ ኦሮሞን፣ ከምባታን፣ ሀዲያን፣ ሲዳማን፣ ሱማሌን እና ሌሎቻችንን በኢትዮጵያም ሆነ በውጪ ሀገር የምንኖረውን ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያዛምደን ኢትዮጵያን በስሙ ያስጠራት የንጉሦች ንጉሥ የካህኖች ካህን የነበረው አባታችን ኢትዮጵ ነው።
ኢትዮጵ የኖረው በጣና ደሴቶች ላይ ሲሆን ዘመኑም ከ 4000 ዐመታት በፊት ነው። እሱም 10 ወንዶችና 3 ሴቶች ልጆች ወልዶ ነበር። 10 ሩ ወንዶች ልጆች 10 ነገዶች ሆነው ለ 4000 ዐመታት በመባዛት እኛን የዛሬዎቹን ኢትዮጵያውያንን አስገኝተዋል። የኢትዮጵ አስሩ ወንዶች ልጆች ስሞችም አቲባ፣ ቢዖር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አክዚብ፣ በሪሳ፣ ቴስቢ፣ ቶላ፣ እና አዜብ ነበሩ። ከ ሶስት ሴት ልጆቹ አንድዋ ሱባ ትባል ነበር። የዛሬ 4000 ዐመት ከወጡት ከእነዚህ ስሞች ውስጥ አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ አዜብ፣ በሪሳ፣ ቶላ፣ አሻን እና ሱባ የተባሉት። ከአባታችን ከኢትዮጵ በኋላ የተከተሉት ነገሥታት ልጆቹ የኢትዮጵያን ስልጣኔ በመላው አፍሪካ አስራጭተው ዛሬ አፍሪካ የሚባለው ሰፊ ምድር እስክ ዛሬ ሁለት መቶ ዐመታትት ድረስ ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ ነበር። LOWER እና UPPER ETHIOPIA ብለው ከፍለውት ነበር። ከእዚህም በላይ የህንድ ውቅያኖስ እና ከ ምእራብ አፍሪካ ብብት ስር ያሉት ውቅያኖሶች ሁሉ የኢትዮጵያ ውቅያኖሶች ይባሉ ነበር። ለማመሳከርያ ከዚህ ፅሁፍ እግርጌ የሰፈሩትን ሁለት ጥንታዊ የአፍሪካ ካርታዎች ተመልከቱ። አሁንም ቢሆን አፍሪካ፣ አፍሪካ የተባለችው በእኛው በአፋሮች ስለሆነ ደስ ይለናል እንጂ አንቆጭም። እስያም እስያ የተባለችው ንግሥተ ሳባ ዙፋኑን በተካችው በ ዐፄ እስያኤል ስለሆነ በእዚህም እንታበያለን። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ “የተቃጠለ ፊት” ሳይሆን “ቢጫ ወርቅ” ስጦታ ለእግዚእብሄር ነው። ቅዱስ ስሟን ለመፋቅ ወይም ለመቀየር የተመኙ ሁሉ የኢትዮጵያ ስም ከእግዚአብሄር ጋራ የተያያዘ በመሆኑ ምኞታቸው ከሽፎ የእግዚአብሄር ዐይኖች ኢትዮጵያ ላይ ተተክለዋል። በቅዱስ መፅሃፉ ውስጥ እግዚእብሄር ኢትዮጵያን ደጋግሞ የሚጠራት ያለ ምክንያት አይደለም። ከማንም ይልቅ ኢትዮጵያን ስለሚወዳት ነው።

በነቢዩ አሞፅ አፍ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡-
<<እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለኔ እንደ ኢትዮጵያውያን ልዶቼ አይደላችሁምን?>> (አሞፅ 9: 7) ከእዚህ ጥቅስ የምንማረው እኛን ኢትዮጵያውያንን እግዚአብሄር ክአሰራኤላውያን ይበልጥ ወይም እኩል እንደሚወደን እና ልቡ ውስጥ እንደእለን ነው። ስለእዚህ እሱ ጥሎ አይጥለንም።

የንግሥት ሳባ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ የነበረው አፄ አክሱማይ በገነባት እና በስሙ በሰየማት በአክሱም ከተማ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ስልጣኔ ለበርካታ ምዕተ ዐመታት ገንኖ ኢትዮጵያን አስከብሯት ነበር። ብልሁና ፍትሃዊው አፄ አክሱማይ ከኢትዮጵያ ዳር ድንበር አልፎ ኢትዮጵያ በዛን ጊዜ ታስተዳድራቸው በነበሩት የግብፅ፣ የሊብያ፣ እና የኑብያ፣ እንዲሁም የባቢሎን ህዝቦች ሳይቀሩ ንጉሦቻቸው ሲበድሉአቸው ለአቤቱታ ወደ እሱ ይጎርፉ ነበር። በእዚህ ምክንያት የ ነገሥታት እራስ የ ዐለም አባት ተብሎ ይጠራ ነበር።

የኢትዮጵያን ሰንደቅዐላማ እያውለበለቡ፣ ከአክሱማይ ልጅ ከ አፄ አውሳብዮስ ጀምሮና ከሱም በኋላ የነገሡት ነገሥታትም፣ ንግሥት ዮዲት (እሳቶ የሚል የቅፅል ስም ጠላቶቿ የሰየሙላት) እስክ አሳደደችው እስከ አንበሳ-ሰገድ ድረስ ለ 850 ዐመታት አክሱምን መናገሻ ከተማቸውና ማእከል በማድረግ ለ 850 ዐመታት ያህል በኢትዮጵያ ላይ ነግሠዋል። ከቀዳማዊ ምንይልክ ዘመን ከጀመርን ደግሞ በአክሱም ላይ የነበረው የንግሥና ዘመን ወደ 950 ዐመታት ገደማ ይሆናል። በላስታ ላሊበላ ለ 343 ዐመታት ያህል የነገሡት የዛግዌ ስርወመንግሥት አባላትና ከ አፄ ዩኩኖአምላክ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኅይለሥላሤ ድረስ በሸዋ በቀዳማዊ ምንይልክ ዙፋን ላይ የነሡትም ነገሥታት ምንጫቸው ከአክሱም እንደ ነበር በኩራት ይናገሩ ነበር። በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵ ዘር ነን ብለው በኢትዮጵያዊነታቸው ይታበዩና ይጀነኑ ነበር። ሁልጊዜም የገናናው የኢትዮጵ ዘር ኢትዮጵያውያን ነን ይሉ ነበር። በቅርቡ ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥለው በኢትዮጵያ ላይ የነገሡት የትግራዩ ተወላጅ አፄ ዮሀንስ እንኳ በኢትዮጵያዊነታቸው ከመኩራት አልፈው ተርፈው አፄ ቴዎድሮስ የጀመሩትን የኢትዮጵያ አንድነት ቀጥለውበት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እያስፋፉና እየጠበቁ ህይወታቸውን አሳልፈዋል። አፄ ዮሃንስ የቆሙት ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ኢትዮጵያ ነበር። እሳቸው ለ አንዲት ካልኢትም እንኳን ኢትዮጵያዊነታቸውን ጥያቄ ውስጥ አስገብተው አያውቁም። ጣልያንን በዶግአሊና በአድዋ ያርበደበዱት የሳቸው የጦር አበጋዝ ጅግናው ራስ አሉላ አባ ነጋም ተጋሩነታቸው አንደተጠበቀ ሆኖ እስከ አጥንታቸው ጥልቀት ድረስ የጠሩ እና የነጠሩ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። በኢትዮጵያዊነታቸው ለአፍታም ያህል ከጣልያኖች ጋራ ያልተደራደሩት ተጋሩው ባሻ አውአሎም እንኳን ለ አድዋ ድል ወሳኝ የሆነውን መረጃ ለጌታቸው ለ አፄ ምንይልክ ያቀበሉት በዚያው በኢትዮጵያዊነት ፍቅራቸው ተቃጥለው አልነበረምን? እንግዲህ የእናንተስ የትግራዋይ ተወላጆቹ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይገባልን? እናንተስ የእነዚህ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ዝርያ አይደላችሁምን? እባካችሁ የእነሱ ዝርያ መሆናችሁን አስታውሳችሁ ኢትዮጵያዊነትን አጥብቃችሁ ያዙ። ለሌሎችም አርአያ ሁኑ። ተራዎቹን እና ብርቱ ከርስትያን የሆኑትን ክቡራኑን የትግራዋይ እባቶቻችሁን እና እናቶቻችሁን እስቲ ተመልከቱአቸው።– በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው አስከሬናቸው በኢትዮጵያ ሰንደቅአላማ ተጠቅልሎ አይደለምን የሚቀበሩት? እናንተስ ከእነሱ እብራክ የወጣችሁ አይደላችሁምን? አሁንም ኢትዮጵያን ካለችበት ማጥ የሚያወጣት ኢትዮጵያዊነት ብቻ እንጂ በቋንቋ ላይ የተገነባው በልማድ ብሄር ብሄረሰቦች የሚባለው በ ትክክለኛ አጠራሩ ግን ጎሳና ነገድ በሆነው ክልለኝነት አይደለም። ይህ ጎሰኝነትና ክልለኝነት የጎሳን እና የነገድን የብሄር ብሄረሰብን መብት አስከብራለሁ ቢልና መብቱ ተገቢ ቢሆንም ድንበር እየሳተ እውስጡ ያሉትን የአናሳዎች መብት እየገፈፈ አያሌ ቀውስ እንዳስከተለ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም። እሱ ለ 26 ዐመታት ተሞክሮ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አይሏል።

በእውነትም አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር መፍትሄው ኢትዮጵያዊነት እንጂ በቋንቋ ላይ የተገነባ ጎሰኝነት አይደለም። ጎሳ ማለት ቋንቋ ማለት ነው እሱውም <<ጎሰአ>>፣ ማለትም ተናገረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የፈለቀ ነው። ስለዚህ ቋንቋ ማለት ጎሳ ነው። ጎሳ ማለትም ቍንቋ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጎሳ የቋንቋ ክፍል እንጂ የደም ወይም የ ዘር ዘርፍ አይደለም። አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በሞላ በዛ ቋንቋ አፍ ከፈቱ የዛ ቋንቋ ወይም ጎሳ አባላት ይሆናሉ። ይህን ሁልጊዜ በምጠቅሰው ምሳሌ ላሳይ።– እኔ በፈረንሳይ፣ በጀርመን እና አንግሊዝ ሃገሮች ኖሬ ሶስት ልጆች ብወልድና እነሱ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ እና እንግሊዝኛ ቢናገሩ፣ የእኔ አፍ መፍቻ ደግሞ ኦሮምኛ ቢሆን ልጆቼ ሶስት የተለያዩ ቋንቋዎች በመናገራቸው ጎሳቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና እንግሊዝ ቢሆንም የርስበርስ ዝምድናቸው አይፋቅም። እኔም ኦሮምኛ ስለተናገርኩ ጎሳዬ ኦሮሞ ቢሆንም አባትነቴ አይሰረዘም። እኛን የሚያዛምደን የኔ ደም ወይም ዘር እንጂ ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለምና። ስለእዚህ ስዎችን በስጋ የሚያዛምድ ደም ወይም ዘር ነው እንጂ ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለም። ደሞ ቋንቋ ሊረሳም ሊለዋወጥም ስለሚችል አስተማማኝ የማንነት መለያ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ 82 ቋንቋዎችና ዳያሌክቶች እንደ አሉ ይነገራል። ቋንቋ ማለት ጎሳ ማለት ስለሆነ በእዚህ ቁጥር መሰረት 82 ጎሳዎች አሉ ማለት ነው። በልጆቼ ምሳሌ እንደምናየው ደም አንጂ ቋንቋ አያዛምድም። አነዚህ ሁሉ የቋንቋ ተናጋሪዎች በደም ወይም በዘር የሚዛመዱት ሁሉም ከኢትዮጵ ወይም ከእሱ 10 ልጆች አብራክ ስለፈለቁ ብቻ ነው። በተጨማሪ ደግሞ በጋብቻ ደም ስለተደበላለቁ እና በኢትዮጵያ ግዛት ለ ሺዎች ዐመታት አብረው ኖረው በባህል፣ በልቦና እና እምነት ስለተሳሳቡ እና ስለተወሳሰቡ፣ እንዲሁም የጋራ የማንነት እሴቶችን ስለአካበቱ ነው። አንግዲህ እናንተም የኢትዮጵያን ህዝቦች የሚያዛምዳቸው እና አንድ የሚያደርጋቸው፣ ክዛም አልፎ የሚያኗኑራቸው ኢትዮጵያዊነት አንጂ ጎሰኝነት ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልል አለመሆኑን ተረድታችሁ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ተጋሩነታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ላይ አተኩሩ። ኢትዮጵያዊነትን ስላራመዳችሁ ቋንቋ እና ባህላችሁን ትተዉታላችሁ ማለት አይደለም። ትግርኛ እንዳትናገሩ፤ ደስ የሚለውን ዘፈናችሁን (ለኔ በግሌ የትግሪኛ ዘፈን ደስ ይለኛል) እንዳትዘፍኑ፣ ልዩ ዳንኪራችሁን እንዳትደነክሩ ወይም ከበሯችሁን እንዳትመቱ የሚከለክላችሁ የለም።

ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኛት የየራሳቸው ብርቅዬ ቋንቋዎችና ባህሎች ያሉአቸው የበርካታ ጎሳዎችና ነጎዶች ሀገር መሆንዋ ነው። ኢትዮጵያውያን በቋንቋቸው፣በባህላቸው እና በገጥታችው ሳይቀር የተቅለመለሙ አበቦች ናቸው። አንድ ዐይነት አበባ ለዐይን ያሰለቻል። ጥሩ ወለላ ማርም አይስጥም። አያያዙን ካወቅንበት በአንድነታችን ውስጥ ልዩነት መኖሩ ምርቃት እንጂ እርግማን አይደለም። እርግማን ካደረግነው ግን ይሆናል። እስካሁን እርግማን አድርገነዋል።

ኢትዮጵያዊነት ላይ አትኩራችሁም የአመራር ሚና እየተጫወታችሁ ሌሎቹንም ኢትዮጵያውያንንም፣ ማለትም ብዙሃኑን የኦሮሞን፣ የአማራን፣ የአፋርን፣ የተጋሩንም ጭምር፣ የሲዳማን፣ የጉራጌን፣ የሃዲያን፣ የከምባታን፣ የሱማሌን፣ የክፋን እና ሌሎቹን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተወካይዎች ጋብዛችሁ ተመካክራችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ርትእ፣ የሰብአዊ እና የሃብት እኩልነትን አስከብሩ። የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ በድፍን ኢትዮጵያ የመንቀሳቅስ እና የመኖር መብትን አስከብሩ። በጎሰኝነት ጦስ በከንቱ የሚፈሰውን ደም አስቁሙ። የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ በአስቸኳይ ፍቱ። ኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ የአሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህብረተሰባዊ ማህበራትን ሳትንቁ በማሰባሰብ እነሱም የሃገራቸውን ወደፊት እንዲወስኑ ዕድል ስጡአቸው። የከንግዲህ ወዲህ አርማችሁንም እስከመጨረሻው ኢትዮጵያዊነትን አድርጉ። አሁን በሃረር የሶማልያ ክልል በእብሪተኞች መሰሪነት ከመኖሪያቸው የተፈናቅሉት አሮሞዎችና ከነሱ ጋር በሰላም ለዘመናት የኖሩት ሶማሌዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው አንዲመለሱ ጣሩ። የጎንደር ህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ የተቻላችሁን ፈፅሙ። ይህን ሁሉ ብትፈፅሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅር፡ አንድነት፣ እኩልነት፣ የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የሰብአዊ መብት፣ ዲሞክራሲ እና የህግ የበላይነት ይሰፍናሉ። ኢትዮጵያም በነፃነቷ ለዘላለም ትኖራለች።

እነዚህን አንገብጋቢ ጉዳይዎች በመፈፀም ፈንታ እንደ ቀድሞው ለብቻችን ስልጣኑን ጨብጠን፣ እንደ በፊቱ በጦር ኅይል ብቻ ችግሩን እንፈታዋለን ካላችሁ ውጤቱ ይብስ እልቂት፣ ይብስ ሰቆቃ ይሆናል። አመፅ አመፅን ይወልዳልና የአመፅ ክበት እየተሽከረከረ ሁሉንም ያወድማል። አሁን ሁሉም ሰው በፖለቲካ ስለበስለና መብቱን እና ማንነቱን ስለአወቀ ፍርሃቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ለመብቱ እና ነፃነቱ ሲዋድቅ እየታየ ነውና። ደሞም የአሁኗ ኢትዮጵያ የዛሬ 26 ዐመትዋ አይደለችምና። ሰለ እዚህ ቡናው ፈልቶ መንተክተኩን ማሽተት ይገባችኋል። እናንተ ባላችሁበት የስልጣን ማማ ላይ ሆናችሁ ሰፊውን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ ለመላው የኢዮጵያ ዜጎች ህይወት መጠበቅና ደህንነት ሃላፊነት አለባችሁ። ለራሳችሁም ደህንነት እንዲሁ። እምብዛም ብልሃት ያደርሳል ከሞት፣ እምብዛም ስለት ይቀዳል አፎት ተብሏልና። ደሞም ኅያል ሁልጊዜ በጦሩ ብዛት አያሸንፍምና። አዱኛና ጊዜም ከዳተኛ ናቸውና። በእዚህ ዐለም ላይ ለዘላለም ፀንቶ የሚኖር ምንም ነገር የለምና። ሁሉም ነገር ማብቂያ ወቅት አለውና። የእናንተም ጉልበት እንደ ድሮው አይደለም። በዱር በገደሉ 17 ዐመታት፣ በከተማዎች 26 ዐመታት፣ በጠቅላላው ቢያንስ ለ 43 ዐመታት ታግላችሁ እረፍት አግኝታችሁም አታውቁም። ለመሆኑ ጡረታ ወጥታችሁ እፎይ ብላችሁ የምትተርፋችሁን አጭር እድሜ የምትዝናኑባት መቼ ነው? ከእናንተ በዕድሜ ለሚያንሱት፣ ጉልበትና አዲስ ሃሳብ ለአዲስ እውነታ ለሚያፈልቁት ወጣት ኢትዮጵያውያን ስልጣን አስተላልፋችሁ እናንተ የታፈራችሁ፣ እንዲሁም የተከበራችሁ እና እንደ አርአያ የምትታዩ አረጋውያን ዜጎች የምትሆኑበት ወቅትስ መቼ ይሆን? የእናንተም ዕጣ ፈንታ በ እነ ሳዳም ሁሴን፣ በ እነ ጋዳፊ እና ሰሞኑን በግድ እና በውርደት ሰልጣናቸውን እንደለቀቁት እንደ ሮበርት ሙጋቤ አንዳይሆን እሰጋለሁ፡ እመኛለሁም። በእዚሁ በኛው አገር አፄ ኃይለሥላሴ እንዳማረባቸው በጊዜ ስልጣን አለቅም፣ ገና በድዴ እገዛለሁ ብለው እንደዛ ተከብረውና ታፍረው እንዳልነበር የደረሰባቸውን ውርደትና ሞት እናንተ የምታውቁት ነው። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ለተቀናቃኞቹ ስልጣን አላጋራም፣ ዲሞክራሲም አልፈቅድም በማለቱ የደረሰበት ውርደትና ሽሽት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ስለ ዲሞክራሲ ካወራን ላይቀር የአሜሪካን ዲሞክራሲ አስተውሉ— ፕሬዚደንቶቹ በሞላ ከ 8 ዐመታት በላይ ስልጣን ላይ አይቆዩም። በስልጣን ላይ ብዙ መቆየት አምባገነንነትን እና ሙስናን ያስከትላልና። እውነተኛ ዲሞክራሲ ማለት የስልጣን ዘመን የእድሜ ልክ እንዳይሆን ገደብ ሲኖረው ነው። በ እርጥም አውነተኛ ዲሞክራሲ ማለት ይሄ ነው። ውድ የህወሀት መሪዎች ሆይ! ስለዚህ የኔን ትንሿን ምክሬን ሳትንቋት እንደምትተገብሯት እምነቴ የፀና ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክ የ 100 ዐመት ሳይሆን በ ሺህዎች የሚቆጠር መሆኑን የአክሱም ታሪክ ብቻ እማኝ ነው። መላው አፍሪካ ድሮ ኢትዮጵያ ይባል እንደነበር የሚመስክር ጥንታዊ ካርታ እታች ሰፍሮአል። ያኔ አፍሪካ የታችውና የላይኛው አፍሪካ ተብሎ ነበር የተከፈለው ። ዝቅ ብላችሁ አሱን ከማየት አትዘናጉ።

በሚቀጥለው ገፅ የአለው ካርታ ደግሞ ከምአራብ አፍሪካ ብብት በታች ያለው ውሃ ሁሉ የእትዮጵያ ውቅያኖስ ይባል አንደ ነበር ያሳብቃል። ዛሬ የህንድ ውቅያኖስ የሚባለውም ጥንት የኢትዮጵያ ውቅያኖስ ይባል እንድነበር የሚያሳይ ካርታም ዐይቻለሁ።

በ ምእራብ አፍሪካ ብብት ስር በእንግሊዝኛ የኢትዮጵያ ውቅያኖስ የሚለውን ፅሁፍ አስተውሉ።