ብሮድካስት ባለሥልጣን በአዋጅ መጓተት ተልዕኮዬን መወጣት አልቻልኩም አለ
የብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም
  • አንድ ክልል በማዕከላዊ ዲጂታል ኔትወርኩ ለመታቀፍ ፈቃደኛ አልሆነም ተብሏል
  • አራት በሳተላይት የሚሠራጩ ጣቢያዎች የባለቤትነት ይዞታቸውን እንዲያዛውሩ ታዘዘ

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የአገሪቱን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሥርጭት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለመቀየርና ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን የቴሌቪዥን ሥርጭቶች ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ረቂቅ ባለመፅዱቁና ለዓመታት በመጓተቱ፣ የፕሮጀክት ሥራዎቹ ለማከናወን እንቅፋት እንደገጠመው አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ረቡዕ ኅዳር 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በምክር ቤቱ የባህልና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ ከሦስት ዓመት በፊት የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በተደጋጋሚ ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለፓርላማው ቢቀርብም ሊፀድቅ ባለመቻሉ፣ የዲጂታላይዜሽን ሽግግሩም ሆነ ማዕከላዊ የዲጂታል ኔትወርክ ሥራው ተግባር ላይ ሊውል አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም የረቂቅ አዋጁ መጓተትን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡበት በቋሚ ኮሚቴ አባላት መነሳቱ በደስታ ቢቀበሉትም፣ ስለረቂቁ መጓተት ሊጠየቁ የሚገባቸው አካላት ተለይተው በሕግ ይጠየቁ ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ጥያቄ ከእናንተ በመነሳቱ ደስታ ተስምቶኛል፡፡ እንዲያውም ጉልበት ሆኖኛል፡፡ አንድ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ሳይፀድቅ መቆየቱ ለምን ተብሎ ጥያቄ ሊነሳበት ይገባል፤›› ብለው፣ መጠየቅ ራሳቸው ከሚመሩት ባለሥልጣን ጀምሮ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

‹‹ወደ ዲጂታላይዜሽን እንገባለን ብለን ፕሮጀክቱን ሠርተናል፡፡ በኢንሳም በኩል የሴንተር ቦክስ ማምረት ሥራ ተጀምሯል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በቢሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ ነገር ግን የሚጠበቀውና የሚያስፈልገው አዋጅ ሳይወጣ የፕሮጀክት ሥራ ማከናወኑ በየትም አገር ያልተለመደ አሠራር ነው፤›› ሲሉም በምሬት ገልጸዋል፡፡

‹‹እኛ የብዙ አገሮችን ልምድ ለማየት ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ያለ አዋጅ ወደ ዲጂታላይዜሽን ለመግባት የሞከረ አገር ከኢትዮጵያ ውጪ የትም ታይቶ አያውቅም፤›› ሲሉም ለቋሚ ኮሚቴ አስረድተዋል፡፡

‹‹የአዋጁ መዘግየትም ትልቅ ትርጉም አለው፤›› በማለት የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሕገ መንግሥት በሚተዳደር አገር ውስጥ ለአዋጁ መዘግየት ምክንያት ሆኗል ያሉትን አንድ በስም ያልተጠቀሱትን ክልላዊ መንግሥት ወቅሰዋል፡፡

የሚመለከታቸው አካላት በደንብ ተወያይተውበትና በአግባቡ ተፈትሾ ነበር ረቂቁ የተዘጋጀው ብለው፣ ‹‹ፌዴራል መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ሲቀበሉት፣ አንድ የክልል መንግሥት ብቻ ነው በራሴ መንገድ እንጂ በማዕከላዊው ኔትዎርክ አልገባም ያለው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ነገር ግን አንድ ክልል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ብቻ አዋጁ ሊጓተት አይገባውም ነበርም፤›› በማለት ሁለተኛው ምክንያት ያሉትን ገልጸዋል፡፡

በባለሥልጣኑ የሕግና የማስታወቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የሕጉ መጓተት በባለሥልጣኑ አደረጃጀት፣ የፋይናንስ አቅምና በፕሮጀክቱ አማካይነት የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዳይሰጥ እንቅፋት እየሆነ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ለባለሥልጣኑ አመራሮች ከተነሱላቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች ውስጥ፣ ያለ ፈቃድ እየተንቀሳቀሱ ነው ስለተባሉ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና በሃይማኖት ተቋማት የሚሠራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይገኙበታል፡፡

ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ዘርአይ በሳተላይት አማካይነት እየተሠራጩ ካሉ አምስት ጣቢያዎች ውስጥ አራቱ በሕገወጥ መንገድ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ፈቃድ ሳያወጡ እየሠሩ መሆናቸው ዘግይቶ ቢሆንም ተደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

አራቱ የተባሉት ጣቢዎች ኢቢኤስ፣ ኤልቲቪ፣ ቃናና ናሁ ሲሆኑ ባለቤቶቻቸው ትውልደ ኢትዮጵያ ይሆኑ እንጂ የውጭ ዜግነት ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹የሚዲያ ሥራ ከኢትዮጵያውያን ውጪ የሌላ አገር ዜግነት ባላቸው አካላት እንዲከናወን ሕጋችን አይፈቅድም፡፡ ነገር ግን ባለቤቶቹ የውጭ ዜግነት ኖሯቸው፣ ፈቃድም ያወጡት በውጭ አገር ነው፡፡ በአንፃሩ አብዛኛው የፕሮግራም ዝግጅታቸውም ሆነ የአገልግሎት ክፍያ የሚሰበስቡት በአገር ውስጥ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ሕግ ለማስከበር ተብሎ ለዕርምጃ መቻኮልን ባለሥልጣኑ አለመፈለጉንና ዕርምጃ መወሰዱ በራሱ ችግር እንደሚያመጣ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ዕርምጃም ቢወሰድ የሚፈጠረው መንጫጫት ቀላል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቢሆንም በዚሁ እንዲቀጥሉ መፍቀድ በራሱ አደጋ ያለው በመሆኑ አራቱን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ባለቤቶች ጠርተን፣ ባለቤትነታቸውን ወደ ሌላ ግለሰቦች ወይም ዘመዶች፣ ጓደኞች፣ አልያም ሌላ ለመረጡት አካል እንዲያዘዋውሩ ነግረናቸዋል፤›› ሲሉ አቶ ዘርአይ አክለዋል፡፡

እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት የሚሠራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በተመለከተ ቁጥራቸው ከ20 እንደሚበልጡ የገለጹት አቶ ዘርአይ፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ በፕሮቴስታንትና በሙስሊም እምነቶች የሚተዳደሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በብሮድካስት አዋጁ የሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት አገልግሎት እንዲሰጡ የማይፈቀድ ቢሆንም፣ እነሱን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየትና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ቀጠሮ መያዙን አስረድተዋል፡፡ ተይዟል በተባለው ቀጠሮም ከፍተኛ የመንግሥት አካላት፣ የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ሚኒስቴር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል መንግሥታት፣ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው በጋራ መድረኩ እንደሚሳተፉ አክለዋል፡፡

በመድረኩ በሚመለከታቸው አካላት የጋራ ውሳኔ እንዲተላለፍ እንደሚጠበቅ፣ የእምነት ተቋማትም ሐሳብ እንዲሰጡ ያደረጋል ብለዋል፡፡

አቶ ዘርአይ ወደ ዋናው ጉዳይ በመመለስ ቋሚ ኮሚቴውም ሆነ ምክር ቤቱ ሕጉን በማፅደቅም ሆነ በአፈጻጸሙ ላይ ከባለሥልጣኑ ጎን ካልቆሙ፣ የባሰ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ደጋግመው አስጠንቅቀዋል፡፡

ባለቤትነታቸውን እንዲያዛውሩ ከታዘዙት ጣቢያዎች አንዱ የሆነውን የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ከመሥራቶቹ አንዱና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማን ፍሰሐ ጽዮንን ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

አቶ አማን የቴሌቪዥኑን ኔትወርክ በተመለከተ በሕጉ በኩል ክፍተት በመኖሩ፣ ባለሥልጣኑን ወደ ዕርምጃ እንዲገባ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢቢኤስን በተመለከተ መናገር የሚቻለው ላለፉት ስምንት ዓመታት በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ሲልቨር ስፕሪንግ በሚገኘው ማሠራጫ ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ በአሜሪካ ሕግ መሠረት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተን የታክስ ግዴታችን እየተወጣን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ሥርጭቱንም በተመለከተ በአሜሪካ ብቻ ወደ 40 በመቶ እንደሚሸፍንም ገልጸዋል፡፡ ቀሪው ደግሞ በኢትዮጵያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጣቢያው ቀጥሯቸው የሚያሠራቸው ሠራተኞችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚመለከተው አካል የሥራ ፈቃድ አውጥተው ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም የተቋሙ አጋር በመሆን የማስታወቂያና የፕሮግራም ግዥዎችን የሚያከናውነው ኢንኮም ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ተመዝግቦ የሽያጭና የማስታወቂያ ሥራውን እንደሚያከናውንም አክለዋል፡፡

የቃና ቴሌቪዥን ተወካይ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር እየተነጋገሩ በመሆኑ፣ ለጊዜው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

Source    –   Ethiopian Reporter