December 10, 2017 09:46

~”የዚህ ዓመት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን የምናከብረው በርካታ ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ምክንያት ለእስር በተዳረጉበት፣ ብሄር ተኮር ግጭቶችና ማፈናቀሎች በተባባሱበት፣ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ አላስፈላጊና ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በመውሰድ የበርካታ ንፁሃን ወገኖቻችን ህይወት በጠፋበትና አካል በጎደለበት ወቅት መሆኑ ሰመጉን በእጅጉ የሚያሳዝን ጉዳይ ከመሆኑ በላይ ሀገራችን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ከመቸውም ጊዜ በላይ አስጊና አሳሳቢ ነው።”
~ “የክልል የጸጥታ ኃይሎችን በአግባቡ የሚያስተዳድርም ሆነ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ስርዓት ባለመኖሩ የክልል ልዩ ኃይል ፖሊስና ሚሊሺያ ታጣቂዎች መጠነ ሰፊ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈፅሙ፣ ለሀገር ደሕንነትም ጭምር ስጋት እንዲሆኑ በር ከፍቷል።”
የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)
(ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀንን አስመልክቶ ከሰመጉ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ)
ታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ•ም

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን እ•ኤ•አ ዲሴምበር 10 ቀን በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ የሚያከብረው በዚሁ እለት እኤአ በ1948 ዓም የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መበቶች መግለጫን ያፀደቀበትን ቀን ለመዘከርና ለማክበር ነው። የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ለ70ኛ ጊዜ ታህሳስ 01 ቀን 2010ዓ• ም “ሁሉም ለሰብአዊ መብቶች መከበር ይቁም!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
የሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) የተቋቋምው በመግለጫው ውስጥ የተካተቱት የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በሀገራችን በሁሉም ቦታ ለሁሉም በእኩል እንዲከበሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር ሰመጉ ላለፉት 26 ዓመታት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት፣ ለህግ የበላይነት መስፈንና ለሰብአዊ መብቶች መከበር አቅም በፈቀደ መጠን ድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል፣ በመወጣት ላይ ይገኛል።
ሰመጉ ከተመሰረተበት ከ1984 ዓ•ም ጀምሮ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመመርመርና በማስረጃ በማስደገፍ ውጤቱን በቅድሚያ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ በመቀጠልም ለህዝብ፣ ለመገናኛ ብዙሃንና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲያቀርብ ቆይቷል። በዚህ ረገድ የሰመጉ ዋና አላማ የሰብአዊ መብት ጥሰት ባስቸኳይ እንዲቆም፣ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ እና በደል የደረሰባቸውም ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ ጥሪ ለማቅረብ ነው። በዚህም መሰረት ሰመጉ ባለፉት 27 አመታት 36 መደበኛ እና 143 ልዩ መግለጫዎችን፣ በተጨማሪም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በርካተ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን አውጥቷል።
በእነዚህ ሪፖርቶች ሰመጉ ባደረገው ምርመራ መሰረት በሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የተፈፀሙ ግድያዎችን፣የድብደባና ማሰቃየት፣ የአካል ማጉደል ድርጊቶችን እንዲሁም በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የተፈፀሙ ህገ ወጥ እስራትን ጨምሮ የዜጎችን የመደራጀት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅና የመሰብሰብ መብቶች ጥሰቶች መፈፀማቸውን ይፋ አድርጓል። በብሔር ግጭት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት ንብረታቸው መውደሙን፣ በልማትና ኢንቨስትመንት ስም ስምምነታቸው ሳይጠየቅና ያለ በቂ ካሳ በርካታ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የሰመጉ ሪፖርቶች ያሳያሉ።
ሰመጉ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ያከናወነው በውሱን የሰው ኃይልና የማቴሪያል አቅም ሲሆን፣ የሰመጉን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን ለታገሉትና መስዋዕትነት ለከፈሉ ግንባር ቀደም አባላቱና ሰራተኞቹ፣ እንዲሁም ለአውሮፓ ህብረት ሲቪል ሶሳይቲ ፊንድ እና ለሌሎች የሰመጉ ወዳጅ ድርጅቶች ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል።
ሰመጉ አሁን በሚገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ቢሆን ሁኔታና አቅም በፈቀደለት መጠን የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ የህግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ካለው የፀና ዓላማ አኳያ ያለመታከት በመስራት ላይ ይገኛል።
ከሰብአዊ መብት ምርመራ ስራ በተጓዳኝ ሰመጉ የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን በማስፋፋት፣ የመብት ጥሰት ለደረሰባቸው ዜጎች ነፃ የህግ ድጋፍና ምክር አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም የህግ ታራሚዎችንና ተጠርጣሪዎችን አያያዝ እንዲሁም የፍርድ ሂደት በመከታተል እንዲሁም የሀገሪቱን ህጎችና ፖሊሲዎች ከሰብአዊ መብቶች ጥበቃ አንጻር በመመርመር እንዲሻሻሉ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ሰብአዊ መብቶች በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ጥበቃና ዋስትና እንዳላቸው የተደነገገ ቢሆንም በተግባር ግን በሕገ መንግስቱም ሆነ ሀገሪቱ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተዘረዘሩ በርካታ መብቶች ሲጣሱ ይታያል። በዚህ ረገድ ያለው የመብት ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ እና አስከፊ እየሆነ በመሄዱ በተለይ ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ችግሩ ለሀገር ደህንነትና ህልውና ጭምር አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል።
መንግስት የሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ ይህንን በማድረግ ረገድ ፈጣንና እውነተኛ እርምጃዎችን ባለመውሰዱና ተገቢውን ቁርጠኝነት ባለማሳየቱ ችግሩ በመቶ ሺዎች ምን አልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሰለባ በማድረግ ላይ ይገኛል። በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ጾታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን እያሰፋ፣ በኢንቨስትመንት ሽፋን ፣ በሰራተኞች መብትና ደህንነት ላይ የሚፈፀመው በደል ተመልካች እያጣ፣ በልማት ስም በዜጎች ላይ የሚደርሰው መፈናቀልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በተመሳሳይ በአካል ጉዳተኞች፣በሕፃናት፣ በአረጋዊያን፣ ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር አብረው በሚኖሩ ዜጎች፣ በእስረኞችና በሌሎችም ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት ከመቀነስ ይልቅ በመባባስ ላይ ነው።
መንግስት የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት ይዞታ ለማሻሻል የወሰዳቸው፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰብአዊ መብት ኮምሽን (ውሱንነቶች ቢኖሩበትም) የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ የተሻለ ተነሳሽነት ማሳየቱ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት መጀመሩ ፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር መውጣቱ ሊበረታቱ የሚገባቸው በጎ እርምጃዎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች ገና በጅምር ያሉ ከመሆናቸውም በላይ ጉዳዩ ላይ የአስፈፃሚው አካል ቁርጠኝነት ካልታከለበት ዘላቂና ውጤታማ መሆናቸው በእጅጉ አጠራጣሪ ነው።
ሰመጉ ለአመታት የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስብ ቢቆይም ለመብት ጥሰቶችና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ መንግስት ባለመስጠቱ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ለታዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች መንስዔ ሆኗል። በተቃውሞ ሰልፎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆኑ የኃይል እርምጃ በመውሰዳቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለአካል ጉዳትና እስራት ተዳርገዋል። ከነባር ክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ እና የብሔር ግጭቶችን ለመከላከል በቂ ሕጋዊ ተቋማዊ እርምጃ ባለመወሰዱ በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የመፈናቀል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የአካል ጉዳትና የእስራት ሰለባ ሆነዋል።
ለአብነትም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በቅርቡ የደረሰውን ግጭት መጥቀስ ይቻላል። የክልል የጸጥታ ኃይሎችን በአግባቡ የሚያስተዳድርም ሆነ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ስርዓት ባለመኖሩ የክልል ልዩ ኃይል ፖሊስና ሚሊሺያ ታጣቂዎች መጠነ ሰፊ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈፅሙ፣ ለሀገር ደሕንነትም ጭምር ስጋት እንዲሆኑ በር ከፍቷል። መንግስት የዜጎችን ሕይወትና ደሕንነት ለማስጠበቅ ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ በጋምቤላ ክልል ከውጭ በመጡ ታጣቂ ጎሳዎች ጭምር በርካታ ዜጎች እንዲገደሉ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናትም ታፍነው ተወስደው ለባርነት እንዲዳረጉ ሆኗል።
የዚህ ዓመት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን የምናከብረው በርካታ ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ምክንያት ለእስር በተዳረጉበት፣ ብሄር ተኮር ግጭቶችና ማፈናቀሎች በተባባሱበት፣ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ አላስፈላጊና ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በመውሰድ የበርካታ ንፁሃን ወገኖቻችን ህይወት በጠፋበትና አካል በጎደለበት ወቅት መሆኑ ሰመጉን በእጅጉ የሚያሳዝን ጉዳይ ከመሆኑ በላይ ሀገራችን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ከመቸውም ጊዜ በላይ አስጊና አሳሳቢ ነው።
ሀገራችን ዘላቂነት ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ ህዝባችንና በተለያዩ የህብተተሰብ ክፍሎች መካከል የመቻቻል እና የመደማመጥ ባህል እንዲዳብር፣ በተለይ በሰብአዊ መብቶች ትምህርትና ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ሰመጉን የመሰሉ የሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት በማዘጋጀት ከፍተኛ እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ ይታመናል። ይህ እንዲሆን ግን ለነዚህ ተቋማት ምቹ የሆነ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ሊኖርና ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ያዳከመው በተለይም በገንዘብ ምንጭ ረገድ የተጣለው የሕግ ገደብ ሊነሳ ይገባል። መንግስትም ገደቡን በማንሳት አስፈላጊውን የሕግ አሰራር ማሻሻያ እንዲያደርግ ሰመጉ አሁንም አበክሮ ያሳስባል። ከመንግስት በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት ተቋማትና መገናኛ ብዙሐን፣ የሲቪል ማሕበረሰቡ፣ እንዲሁም ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሀገራችን ከገባችበት አስጊ ሁኔታ እንድትወጣ የበኩላቸውን እንዲወጡ ሰመጉ በአጽንኦት ይጠይቃል።
በመጨረሻም የዜጎችን የሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች በተግባር እንዲከበሩ ያስፈልጋልና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ ዜጎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማትና ለሰብአዊ መብቶች መከበር የቆሙ ሁሉ ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ሰመጉ ጥሪውን ሲያስተላልፍ፣ ድርጅቱ ለሰብአዊ መብቶች መከበር የድርሻውን ለመወጣት ከዓመታት በፊት የገባውን ቃል በድጋሚ በማደስ ነው።
ሁሉም ሰብአዊ መብቶች ለሁሉም!
የሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ)
ታህሳስ 01 ቀን 2010 ዓ•ም
አዲስ አበባ

 

No automatic alt text available.

 

No automatic alt text available.