Wednesday, 06 December 2017 13:19

“እውነተኛ፤ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ያሳየው

ደርግ ነው”

ዶ/ር ፍሰሃ አስፋው

በይርጋ አበበ

አርብ 29/03/2010 ዓ.ም የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። በየዓመቱ የሚከበረው ይህ ቀን (በዓል) መሠረቱ በ1987 ዓ.ም የወጣው የአገሪቱ ህገ-መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትን ያመጣ በመሆኑ እንደሆነም አገሪቱን የሚገዛት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ደጋግመው ይናገሩ።

መንግሥት “የማንነት ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተፈቷል፤ ህገ መንግሥቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችን ተቻችለው እንዲኖሩ ያስቻለ የቃል ኪዳን ሰነድ ነው” ሲል ይገልጻል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች የማንነት ጥያቄዎች እና ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ሲፈጠሩ እያየን ነው።

ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በተመለከተ ሕገ-መንግሥቱ እና የፌዴራል ሥርዓቱ የሚጫወቱት ሚና ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ቅድሚያ የሚሰጠው ነጥብ ነው። ህገ-መንግስቱ በሚረቀቅበት ወቅት ኢህአዴግን ወክለው የአርቃቂ ኮሚሽኑ አባል የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና በደርግ መንግሥት የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት አባል ሆነው የወቅቱን ህገ መንግሥት ካረቀቁት መካከል አንዱ የነበሩት ዶ/ር ፍሰሃ አስፋው ላነሳነው ጥያቄ መልስ የሰጡ ምሁራን ናቸው። (ዶ/ር ነጋሶ ጉዳዳ ቀደም ብሎ ለሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ politics of Federalism እና ለናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ ኢንስቲትዩት Constitution for a multinational Democratic state nation the case of Ethiopia በሚሉ ርዕሶች ያወጧቸውን ሰነዶች እንደሳቸው መረዳት እንድንጠቀም በፈቀዱልን መሠረት ነው ለዚህ ጽሁፍ የተጠቀምንበት)።

 

የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር በሕገ -መንግሥቱ

በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ አንድ “የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል” ሲል ይደነግጋል። የፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎችን ሲጠቅስም ስምንት የብሔር ክልሎች፤ ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረር፣ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ መሆኑን በአንቀጽ 47 ደንግጓል።

ዶ/ር ፍሰሃ ፌዴራሊዝም አወቃቀሩን ላይ ያላቸውን ልዩነት ሲገልፁ “ቋንቋን መሠረት ያደረገ መሆኑ በህዝቦች መካከል መለያየትንና መጠራጠርን ያሰፍናል” ሲሉ ይሞግታሉ።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው ለሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ በቀረቡት የጥናት ፅሁፍ ላይ የፌዴራሊዝሙን ጠቀሜታ ገልጸዋል። ዶ/ር ነጋሶ ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም ከ1983 ዓ.ም በፊት በነበረው የአገዛዝ ሥርዓት ማህበራዊ ፍትህ እጦት፣ የኢኮኖሚ ብዝበዛ እና የፖለቲካ ቁጣ (ጥያቄ) ተነስተው ነበር። እነዚህ ጥያቄዎችና ኢፍትሃዊነቶች ደግሞ በሀይማኖት፣ በባህል እና በቋንቋ ላይ ያተኮሩ ነበር። በዚህ የተነሳም በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች አመፆችና ተቃውሞዎች ተነሱ። በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች የኤርትራ የነፃነት ግንባር (ሻዕቢያ)፣ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ህወሓት)፣ የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራቲክ ንቅናቄ (ኦህዴን) ጨምሮ ሌሎች የታጠቁ ሀይሎች እንደነበሩ በፅሁፋቸው አስፍረዋል። ዶ/ር ነጋሶ አያይዘውም፤ ኢህአዴግ ሥልጣን በተረከበበት ወቅት የነበረውን አካባቢያዊ ፖለቲካ ጠቅሰው ባቀረቡት ጽሁፍ “በሱዳን የነበረው የምሥራቅ አፍሪካ ጦርነት እና የሶማሊያ አለመረጋጋት በህንድ ውቅያኖስ ሰሜን ምስራቃዊ ቀጠና እና በቀይ ባህር ዙሪያ አደጋ ያንዣበበ ነበር” ብለዋል። ኢህአዴግ ምንም እንኳን ወታደራዊውን መንግሥት በጠበመንጃ አፈሙዝ አሸንፎ የአራት ኪሎውን ቤተመንግሥት ቢቆጣጠርም፣ ይህ ግን ብቻውን ለሰላም ማረጋገጫ ዋስትና እንዳልነበረ ዶ/ር ነጋሶ ተናግረዋል። ለዚህም ሲባል የሰላም ጉባኤ (ኮንፈረንስ) መዘጋጀቱን ያወሱት የቀድሞ የኢፊዲሪ ፕሬዝዳንት፤ ሆኖም ግን ኢህአፓ፣ መኢሶን እና ኢሰፓ በጉባኤው እንዳይሳተፉ መደረጋቸውንም አውስተዋል።

 

ሕገ-መንግሥት እና ሂደቱ

የኢህአዴግ መንግሥት በ1987 ዓ፣ም ህዳር 29 ቀን ያጸደቀውን ህገ-መንግሥት “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተስማምተውና ተቻችለው እንዲኖሩ ያስቻለ የቃል ኪዳን ሰነድ” ሲል ይገልጸዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይህን ነፃነታቸውንና እኩልነታቸውን ያረጋገጠላቸውን ሕገ- መንግሥት የወጣበትን ቀን ለማሰብ በየዓመቱ እየተገናኙ የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን ያከብራሉ። በአሉም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት ይከበራል።

ዶ/ር ፍሰሃ አስፋው ግን ከላይ የሰፈረውን የብሄር ብሄረሰቦችን በዓል ምክንያት አይቀበሉትም። የስነ-ሰብ ምሁሩ ለምን እንደ ማይቀበሉት ሃሳባቸውን ሲያስቀምጡ “ህገ- መንግሥቱ ህዝብ ሳይወያይበት የፀደቀ ነው” ይላሉ።

ዶ/ር ፍሰሃ አክለውም “ለምሳሌ እኛ ያረቀቅነውና ያፀደቅነው ህገ-መንግሥት (በደርግ ጊዜ የወጣውን የኢትዮጵያ ህገ-መንግሥት) ረቂቁ ከታወጀ በኋላ በ16 ቋንቋ ተተርጉሞ ህዝብ ውይይት እንዲያደርግበት አቅርበን ህዝቡ ተወያይቶ ተስማምቶ ነው ያጸደቀው። ኢህአዴግ ያወጣው ህገ-መንግሥት ግን ህዝብ ያልተወያየበት ስለሆነ ነው ህዝቡ ሊቀበለው ያልቻለው” ብለዋል።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው በኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን የወጣው የኢትዮጵያ ህገ- መንግሥት “ህዝቡ አልተወያየበትም” የሚለው ገለፃ ትክክል መሆኑን ይስማማሉ። “እኔ እስከማውቀው ድረስ አርቃቂ ኮሚሽኑ ረቂቁን ለህገ-መንግሥት ጉባኤ ከላከ በኋላ ለህዝብ ውይይት አልቀረበም” ሲሉ ተናግረዋል። ረቂቁ ከመውጣቱ በፊት ግን 73 ጥያቄዎችን ለ23ሺህ ቀበሌዎች ነዋሪ ህዝብ ቀርቦ ህዝብ እንደተወያየበትና የህዝብ አስተያየትን ባማከለ መልኩ የህገ-መንግሥት ምሁራን (experts) ሃሳባቸውን አክለውበት እንደወጣ ዶ/ር ነጋሶ ይናገራሉ።

በአንፃሩ የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት ደግሞ መግቢው ላይ ባሰፈረው ሀሳብ ላይ “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” በራሳቸው ፈቃድ እና በነፃነት ባካሄዱት ውይይት የፀደቀ ህገ-መንግሥት መሆኑን ይገልፃል።

 

የብሔሮች ብሔረሰቦች መብት በሕገ-መንግሥቱ እና በተግባር

የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት በአንቀጽ ስምንት ቁጥር አንድ ላይ “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵ ሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” ይላል። “ይህ ህገ-መንግሥም የሉአላዊነታቸው መገለጫ ነው” በማለት ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጣል።

ዶ/ር ፍሰሃ አስፋው ደግሞ በብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበርና እኩልነት መጎናጸፍ ላይ ቅሬታ ባይኖራቸውም የሚያነሱት ጥያቄ ግን አለ። ዶክተሩ ሲናገሩ “ታሪክን በታሪክነቱ ማስቀመጥ ጥሩ ነው። ብሔረሰቦች በዘውዱ ጊዜ በቋንቋህ አትጠቀም፤ ባህልህን አታሳድግ የሚል አልነበረም። በደርግ ጊዜ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የብሔረሰቦችን እኩልነት በይፋ ያወጣው የደርግ መንግሥት ነው። የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት አቋቁሞ፤ ጥናት አስጠንቶና በ16 ቋንቋ አስተርጉሞ ህገ መንግሥት ያስፀደቀና እውነተኛ የሆነ የብሄረሰብ እኩልነት ያሳየው ደርግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶ/ር ፍሰሃ አክለውም የኢህአዴግ መንግሥት በብሄሮች እኩልነት ላይ ያለውን አቋም የሚገልፁት “ለፖለቲካ ትርፍ እንጂ ከልብ የመነጨ አይደለም። የብሄረሰብ እኩልነት ማለት በቀጠሮ እየተገናኙ ጭፈራ መጨፈር አይደለም። ትክክለኛ የብሔረሰብ እኩልነት የሚባለው የኢኮኖሚ እኩልነት፣ የፖለቲካ እና የልማት እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እንዲሁም የአስተዳደር እኩልነት ሲፈጠር ብቻ ነው” ይላሉ። በእሳቸው እምነትም እውነተኛ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት “አልተከበረም!”። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የምትከተለው ፌዴራሊዝም ለክልሎች የሚሰጠው ሥልጣን ውስን ነው። ከላይ የወረደን መመሪያ እንጂ ክልሎች በራሳቸው ፈቃድና እቅድ የሚሰሩት የለም” ሲሉ የፌዴራል መንግሥት የፖለቲካ ጡንቻ ከክልሎች የገዘፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪን ህገ-መንግሥት ካረቀቁት 29 ሰዎች አንዱ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ምንም እንኳን ከህገ-መንግሥቱ አንቀጾች መካከል በተወሰኑት ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ቢገልጹም “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት” እውቅና መስጠት መቻሉን ይናገራሉ። እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ምልከታ የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት ለብሔር ብሔሰቦች የሰጠው መብት ተገቢ ቢሆንም “እስከመገንጠል” በሚለው ክፍል ላይ ግን ልዩነት አላቸው። ብሄራዊ ቋንቋን፣ የመሬት ባለቤትነትን፣ ሰንደቅ ዓላማ እና አንቀፅ 39 ላይ ያለው እስከመገንጠል የሚሉ የህገ-መንግሥቱ አንቀፆች ያኔም ሆነ አሁን አጨቃጫቂ እንደሆኑ ተናግረዋል። በብሔር ብሄረሰቦች እኩልነት ላይ ሳይሆን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አከባበር ላይ ልዩነት እንዳላቸው የገለፁት ዶ/ር ነጋሶ “በዓሉ ላይ ልዩነት አለኝ። ምክንያቱም ህዳር 29 ህገ-መንግሥት የፀደቀበት እንጂ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አይደለም” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።

በአገሪቱ በርከት ያሉ አካባቢዎች ዘርንና ብሄርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እየታዩ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ 12ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ከነገ በስቲያ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ይከበራል። በህገ-መንግሥቱ እና በፌዴራል ስርዓቱ አወቃቀሩ ላይ ልዩነት ያላቸው ወገኖች ለወቅታዊ የአገሪቱ ችግር ምንጭ አድርገው የሚያቀርቡት ህገ-መንግሥቱን እና የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀሩን ሲሆን፤ ከዚህ ጎን የተሰለፉ ወገኖች ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዶላር ኮንትሮባንድ እና የጫት ንግድን በላይነት ለመውሰድ የሚደረግ ጤናማ ያልሆነ የኪራይ ሰብሳቢ ባለሥልጣናት ሥራ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

Source   –   Sendek