Share


“መርዝን በመርዝነት ስለመርዝ መመረዝ፣
የመርዙን ለመርዙ በመርዙ ማስመረዝ።”
(ሃይሉ ገ/ዮሃንስ – ገሞራው)

በሃገራችን ኢትዮጵያ የችግሮችን አንገብጋቢነትና ጥልቀት በመረጃና በማስረጃ ሣይጠናከር የሚቀርቡትን መንደርደሪያዎች የማያግዙ የተሳሳተና መደበኛ ያልሆነ ሃሳብ /Informal Fallacy/ በችኮላ ማጠቃለያ /Hasty Generalization/ ላይ የተመሰረቱ ግንዛቤዎችን በማሽከርከር ከምላሹ ይልቅ ብዥታው ጎልቶ የሚወጣው ዱባ ድፍን መሣዩ ይህ “የብሄሮች ጥያቄ” የተሠኘው ነው። በዚህ መጣጥፍ ላይ ፀሃፊው ለማነፃፀር እንዲረዳው የስታሊንን ትንታኔ መጠቀሙ ትንታኔውን በመቀበሉ ሣይሆን “የብሄሮች ጥያቄ” ትርክት መነሻ ሀሳብ የሚያጠነጥኑ ሃይሎች መነሻና መድረሻቸው ይህ የስታሊን መርሆ በመሆኑም ነው። ተግባሩም የጎሣ ፖለቲካ መርዝን በመርዝነቱ በመመደብ፤ መርዙን በመርዙ ለማክሸፍና በመርዙ ለማስመረዝ እንዲቻል ሲባል ነው። ወደዚህ ጥያቄ ውስጥ ከመግባታችን በፊት በአንድ ወይም በሌላ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉትን ማህበራዊና ባህላዊ ክፍፍሎችና ስብስቦች /Social stratification & groups/ መቃኘት የግድ ይላል።

ሀ). ቤተሠብ /family & kinship/

ይህ በተወላጅነት፣ሥጋና በጋብቻ ዝምድና ላይ የተዋቀረ አደረጃጀት ነው።

ለ). ነገድ /Clan/

መሠረቱን በጋብቻ፣ በዝምድና ላይ ያደረገ በጋራ ቅድመ አያት መስመር የተሳሰሩ ቤተሰባዊ የሰዎች ስብስብና የሠፋ ቤተሰብ ነው።

ሐ). ጎሣ /Tribe/

በእድገት ደረጃ ከነገድ ላቅ ያሉ፤በተለያየ መልከዐ-ምድር ሰፍረው በድንበር ዘለል ጋብቻ፣አንፃራዊ አንድነት፣ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ፣ ባህልና ስነልቦና ያዳበሩና በዝምድናና ጉርብትና ሃረግ የተቆላለፉ የተለያዩ ነገዶች ውህደት ነው።ጎሣዎች የጋራ ኢኮኖሚያዊ ትሥስርና የዳበረ ኢኮኖሚ አይኖራቸውም።
መ). ብሄር (ትርጉሙ ከታች ተካቷል)

A. “የብሄር ጥያቄ”
ሀ). ታሪካዊ መሠረት
ዓለም በሶሻሊዝም ጎርፍ ልትጥለቀለቅ በተቃረበችበት እ.አ.አ ከ1917 የራሲያ ቦልሼቪኮች ዐቢዮት ሶስት አመት ቀደም ብሎ እ.አ.አ በ1913 “ማርክሲዝምና የብሄር ጥያቄ” በሚል እርዕስ የተፃፈው የጆሴፍ ስታሊን መፅሃፍ ይህን ጥያቄ ለማስተናገድ የቀረበ የጊዜው ሶሻሊስታዊ መጣጥፍም ነበር። የዚህም መጣጥፍ አይነተኛ ተለዕኮ ወይም የትኩረት አቅጣጫ በሩሲያና በምስራቅ አውሮፓ ውስጥ የነበሩና የካፒታሊስት ኢንደስትሪያል ኢኮኖሚ በአንፃራዊነት ያዳበሩ እንደ ፖላንድ፣ ቼክ፣ ስላቭስ፣ ፓልስ፣ ኦስትሪያ፣ ጆርጂያ፣ አርሜኒያ፣ ዩክሬን፣ ሃንጋሪ ወ.ዘ.ተ አስመልክቶ የተቀመረ የቦልሼቪኮች እይታም ነው።

B). የብሄር ትርጉም በጆሴፍ ስታሊን

ስታሊን ብሄር ትርጉም የሠጠው በሚከተሉት ግን በማይነጣጠሉ አምስት መስፈርቶች አማካይነት ነው። የብሄር መለያ መስፈርቶች ፦
1. ‹የዘር ወይም የጎሣ ያልሆነ ነገር ግን በታሪክ ሂደት በአንድ ላይ የተቆራኙ የተለያየ ህዝብ ስብስብ › ነው።
በስታሊን ትንታኔ መሠረት የጣሊያን ወይም የጣሊያን ብሄር የምንለው የተመሰረተው በሮማውያን፣ ኢትረስከን፣ቱተን፣ግሪክስ፣አረብ ወ.ዘ.ተ እንዲሁም የፈረንሣይ ብሄር የተዋቀረው ከጎል፣ ሮማንስ፣ ብሪተን፣ቱተን ወ.ዘ.ተ መሆኑን በማስገንዘብ ብሄር የተለያዩ ህዝብ ቁርኝት እንደሆኑ በምሳሌ አሳይቷል።

2. ‹የጋራ ቋንቋ›

የጋራ ቋንቋ አንዱ የብሄር መለያ ነው። በርግጥ የተለያየ ቋንቋ የሚናገር ብሄር የለም። ነገር ግን አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ የተለያዩ ብሄሮች ልክ እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ወይም ኖርዌጃንና ዳኒሽ ይኖራሉ ይላል። አንድ አይነት ቋንቋ መናገር በራሱ የብሄርን የተሟላ ትርጉም ለመስጠት አያስችልም።

3. ‹የጋራ የሆነ የግዛት አካል›

4. ‹የጋራ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነትና ኢኮኖሚያዊ ጥምረት /economic cohesion/

የጋራ ግዛት አካል ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በዚህ አካል በብሄሩ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ክፍሎች አንድ ላይ የሚያመጣና ወጥ የሚያደርጋቸው የጋራ ኢኮኖሚያዊ ትሥስርና የዳበረ ኢኮኖሚ መኖር አለበት።

5. ‹የጋራ ስነልቦናዊ ቅንብር /psychological make-up/›

ይህ ማለት በጋራ ቋንቋ፣ የግዛት አካል/common teritories/ ፣በዳበረ የኢኮኖሚ እድገት የተፈጠረ ኢኮኖሚያዊ ትሥስርና በባህል የሚገለፅ ተመሣሳይ የስነልቦና ቀመር ያላቸው ዘር ወይም ጎሣ ያልሆነ ስብስብ ነው።

C). “የብሄር ጥያቄ” ትርክትና የብሄር ደረጃ
ምደባ በኢትዮጵያ

የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ መውገርገር በተለይ የጀመረው የሶሻሊዝምን ቅኝት የተላበሰው እ.አ.አ በ1960 የተማሪዎች እንቅስቃሴና በተለይም ‹የብሄሮች ጥያቄ› በሚል እርዕስ እ.አ.አ በ1969 ዓ.ም በዋለልኝ መኮንን በቀረበ ፁህፍ ላይ ነው። በዚህ ፁህፍ ዋለልኝ እንዲህ ይላል።

« … የሶሻሊስት ረዕዮተ ዓለም የተማሪው ረዕዮተ ዓለም የሆነበት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ተፃራሪ ሃይሎች የምንላቸውም በአብዮትና በጥገና ለውጥ መሃል ያለው ሣይሆን በሳይሣዊ ሶሻሊዝምና ጤናማ ያልሆነና ወረተኛ /perversion & fadism/ አስተሳሰብ መካከል ነው። ዋለልኝ ‹የብሄሮች ጥያቄ› በሶሻሊዝም መነፅር መቃኘቱን ሲቀጥል « ኢትዮጵያ የአንድ ብሄር አገር አይደለችም። የራሣቸው ቋንቋ፣አለባበስ፣ ታሪክ፣ማህበራዊ አደረጃጀትና የግዛት አካል ያላቸው የተለያዩ ብሄረሠቦች ሃገር ናት። ታዲያ ከዚህ ሌላ ብሄር ምንድነው? ስለዚህ የኦሮሞ ብሄር፣የትግራይ ብሄር፣የአማራ ብሄር፣ጉራጌ ብሄር፣ሲዳማ ብሄር፣ወላይታ ብሄር፣አደሬ ብሄር አለ። ለመሆኑ ሐሰተኛ ብሄረተኝነት /Fake Nationalizm/ ምንድነው? ይህ ሐሰተኛ ብሄረተኝነት የአማራ ብሄረተኝነት ወይም በተወሠነ መልኩ የአማራ-ትግሬ ብሄረተኝነት ነው። የአማርኛ ሙዚቃ፣የአማራና የትግሬ የሆነው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣የአማራ-ትግሬ ሸማ/ልብስ/ መልበስ ወይም ኢትዮጵያዊ ለመሆን ስም መቀየር፣ በህገ-መንግስቱ ት/ቤት ለመሄድ፣ ስራ ለማግኘት፣ ዜና ለመስማት፣ መፅሓፍ ለማንበብ አማርኛ መናገር የግድ ነው። …የባህል ወረራው በደቡብ ያለው የአማራ፤ በከተማ ያለው የአማራ-ትግሬ ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ነው። ያለው የበላይነት የአማራ-ትግሬ ነው።» ይለናል።

D). ጆሴፍ ስታሊንና የዋለልኝ እይታ

የዋለልኝ ፁሕፍ መሠረት ያደረገው ሶሻሊዝምና የስታሊን ‘ማርክሲስምና የብሄር ጥያቄ’ የሚለው መጣጥፍ ነው። ዋለልኝ ለትንታኔው የሚጠቅመውን የስታሊን ትንተናን ጥራዝ በመንጠቅ ቢሆንም የስታሊን አምስት የብሄር መስፈርቶች በቅጡ የገቡት አይመስልም። ዋለልኝ «የራሣቸው ቋንቋ፣ አለባበስ፣ታሪክ፣ማህበራዊ አደረጃጀትና የግዛት አካል ያላቸው የተለያዩ ብሄረሠቦች ሃገር ናት»፡ይለንና ‹ታዲያ ከዚህ ሌላ ብሄር ምንድነው? ስለዚህ የኦሮሞ ብሄር፣የትግራይ ብሄር፣የአማራ ብሄር፣ጉራጌ ብሄር፣ሲዳማ ብሄር፣ወላይታ ብሄር፣አደሬ ብሄር አለ።› ሲል እራሱን ጠይቆ ለራሱ ይመልሳል። በተለይም አንድን ብሄር ብሄር የሚያሰኙት መስፈርቶች ውስጥ ‹የጋራ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነትና ኢኮኖሚያዊ ጥምረት /cohesion/ የሚለውን በተለይ የአንድን ብሄር የላቀ አደረጃጀትና ቅንብር፣የበለፀገ ኢኮኖሚን ገላጩን ቁምነገር ይዘነጋና የችኮላ ማጠቃለያ /Hasty Generalization/ ላይ ይደርሳል። ለዋለልኝ 183,415 የሚሆን ህዝብ ያለው ሃረሪ ሳይቀር ብሄር ነው። የቀረው ነገር ቢኖር የሃገሪቱን የጋማ ከብቶች በብሄር መሸንሸን ብቻ ነበር። ለርሱ ፁህፉን ከገለበጠበት የስታሊን መፅሃፍ ላይ ዕንኳን ብሄር ‹ዘር ወይም ጎሣ አይደለም› የሚለውን ሃረግ እንኳ ዘንግቶታል። ዋለልኝ የብሄርን ጭቆና የሚገልፀው በልብስ፣በዘፈንና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማራና ትግሬነት ነው። እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች እናንሣ። እርሱ በነበረበትም ሆነ በአሁኑ ዘመን ከበዓላት ውጭ የተባለውን ሸማ በከተማዎች፤በመላው ገጠር አይለበስም። ብዙው ኢትዮጵያዊ የሚውለውና የሚታየውም የአማራ ባህላዊ ልብስ ተላብሶ ሳይሆን በእርዛትና ነው። አማርኛ በታሪክ አጋጣሚ የሃገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ ሆኗል። ይህ ማለት የሌሎች ጎሣዎች ቋንቋ ላይ ተፀእኖ ቢኖረውም ጨፍልቋቸዋል ለማለት አይቻልም። በኢትዮጵያ ውስጥ 34.4% የሚሆነው ህዝብ ኦሮሚኛ፣ 27% አማርኛ ተናጋሪ ነው። መቶ ሚሊዮን ከሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ አሁን እንኳ አማርኛን ከአማራ ውጭ የሚናገር ህዝብ አራት ሚሊዮን አካባቢ ነው። 98% ፐርሰንት የትኛውም ጎሣ አባል የራሱን ቋንቋ ይናገራል። አማርኛ የከተማ ነዋሪውና የአማራው ቋንቋ ብቻ ነው። ሃይማኖትን በተመለከተ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማራው የተቀበለው ሃይማኖት እንጂ የግል ንብረቱ አይደለም። በኢትዮጵያ ውስጥ 43.5% ኦርቶዶክስ፣ 18.6% ፕሮቴስታንት፣ 33.9% ሙስሊም ሲሆን በኦሮሚያ ብቻ 47.6% ህዝብ ሙስሊም ነው። ዋለልኝና የርሱንና የስታሊንን ንድፈ-ሃሣብ ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ሳያቆራኙ የሚያላዝኑ የዘመናቸን አክራሪ የጎሣ ፖለቲከኞች ትርክት ውጭ የ2010 በዓለም አቀፉ የሃይማኖት እድገት የመረጃ ቋት መሠረት የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች እ.አ.አ በ1910 ቁጥራቸው 3,290,000 እንደነበረ ይህም እ.አ.አ በ2010 ወደ 35,710,000 ማደጉን ነው።ከላይ በሰፈሩት መረጃዎች በህዝብ ላይ ተጫነ የሚሉት ቋንቋና ሃይማኖትና ልባሣት ከንቱና በምኞት ላይ የተመረኮዘ ቅዠትም ነው።

E). “የብሄር ጭቆናው” ትርክት ሚስጥር

ዋለልኝም ይሁን አክራሪ የጎሣ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር እንደሌለ አሣሳምረው ያውቃሉ። ኢትዮጵያ ቤተሠብን፣ የነገድና የጎሣ ስብስቦችን አቅፋ የያዘች ሃገር ናት። እነዚህ ስብስቦች በነጠላም ይሁን በቡድን በዳበረ የእርስ በርስ ግኑኝነት ተቆላልፈው፣ ወጥ በሆነ ቋንቋ ተጣምረው፣በስነልቦና የተገመደ ባህልን ይዘውና የብሄራዊ ማንነት/National Identity/ ተላብሰው ባለመገኘታቸው ብሄር ብለን ልንሰይማቸው ከቶውንም አንችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውም በፊውዳሊዝም ስርዓት ሣቢያ የነበረ የመደብ ብሄራዊ ጭቆና እንጂ የብሄር ጭቆና አይደለም። ይህ የፊውዳሊዝም ስርዓትም ከሁሉም ዘር በታማኝነትና በጋብቻ ትሥስር የተቆራኙ ግለሰቦችን ያቀፈ ልክ በሌላው ዓለም የነበሩ ተመሳሳይ ስርዓተ ማህበራት ጋር የቅርጽ እንጂ የይዘት ልዩነትም ያልነበረው ነው። በስታሊንም መስፈርት “ለብሄር ጭቆናው” መፍትሄ ላይ የተቀመጠውን “የብሄሮች የራስን እድል በራስ መወሰን መብት እስከ መገንጠል” ስለሚል አንድ ጎሣ የመገንጠል ጥያቄን ለማንሣት እራሱን ወደ ብሄር ደረጃ በፈቃዱ ማድረስና ማደናገር ብቻ ነው። ጎሣዎች በዚሁ መፅሃፍ የሚፈቀድላቸው የውስጥ የራስ ገዝ አስተዳደርም በመሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ ዋለልኝና አክራሪ የጎሣ ፖለቲከኞች እንዳላዘኑት “የብሄሮች እስር ቤት” ሣትሆን የተጨቆነ ህዝብ መታጎሪያ ሃገር ናት። ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር የለም። ብሄር ከሌለ ስለ “ብሄር ጭቆትና” ማውራት አንችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ጥንትም የነበረው ብሄራዊ ጭቆና ነው።ዛሬ ያለው ወያኔያዊ የአፓርታይድ ስርዓት ነው። ይህም ስርዓት የአንድ ጎሣ ስብስብ ሆኖ የፖለቲካ

ስልጣን በመያዝ ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛን በመላው ህዝብ ላይ የሚፈፅም ወራሪ የሽፍታ ቡድንም ነው። ወያኔያዊ የአፓርታይድ ስርዓትንም የጨቋኝ ብሄር መዋቅር ለማለት የማንችለው፡-

1. ትግራይ ብሄር አይደለችም። ወራሪው ወያኔም የጎሣ ጥርቅም ነው።በቋንቋ ፌደራሊዝም ስም የተቃኘ የአፓርታይድም ስርዓት ነው።

2. ይህ ወያኔያዊም ጎሣ ባህሉንም ሆነ ቋንቋውን በሌሎች ላይ አልጫነም።

3. የወያኔ የጎሣ የበላይነት የሚገለፀው በተቆጣጠረው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መዋቅሮች በጠቀጠቃቸውና አግላይና ብቸኛ ተጠቃሚ ባደረጋቸውም የጎሣ አባላቱ ነው።

‘የህዝብን ችግር መፍታት የሚቻለው የችግሮቹን መንስኤና ባህርይ መረዳት ሲቻልና ለችግሮቹ የፈጠራ ትርክት ሣይሆን ተጨባጭ መፍትሄ ይዞ በመገኘት ብቻ ነው።’
‘ETHNIC POLITICS AND PORK” TEND TO GO TOGETHER’
James D. Fearon