December 14, 2017
(December 13, 2017)
በሰሞኑ በወልድያ ከተማ የትግራይ እግር ኳስ ቡድን ከወሎ ቡድን ጋር ሊያደርግ የነበረውን ጨዋታ ተከትሎ የተነሳው ብጥብጥ ለአያሌ ሰዎች ህይወት መጥፋትና መቁሰል ለብዙ ንብረት መውደምም ምክንያት ሆኗል።ይህ እስፖርትን ሽፋን አድርጎ በወያኔ ዘበኛ ፈጥኖ-ደራሽ ሃይል ታጅቦ ወደ ቦታው የተላከ የጥፋት ሃይል ገና ከወሎ ድንበር ላይ ሲደርስ ጀምሮ የሕዝቡን ስሜትና ሞራል የሚነካ ፍጹም ብልግናና ድፍረት የተሞላበት የዘር ጥላቻን ያዘለ ስድብና ህገ ወጥ የቁጣ-ቅስቀሳ ተግባር (provocation) እንጂ በእለቱ የተፈጸመ ድንገተኛ ክስተት አልነበረም።
የዘር በሽታ ያሳበዳቸው እነዚህ የጥፋት መልእክተኞች በስካር መንፈስ በሚመስል ማጭበርበር የፈጸሙት ወንጀል ተዘጋጅተውና ሰልጥነውበት የመጡበት እንጂ በቦታው የተከሰተ አጋጣሚ አይደለም። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ድርጊቶችን መንግስት ተብዬው በመፈፀም ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገንዝቦታል። ለመሆኑም የጠብ ቀስቃሹን ብልግና ተከትሎ ለሚነሳው ህዝባዊ ንዴትና ቁጣ መልስ እንዲሰጥ ተዘጋጅቶ የተላከው የታጠቀ የአጋዚ ሃይል ጭብጥ ማስረጃ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የትግሬ ነጻ አውጪ ነኝ ባዩ ወያኔ መጀመሪያዉኑ እንዳሰበዉ ወጣቶችን በጅምላ በማፈስ ትግራይ ዉስጥ በተዘጋጀ የጅምላ ማጎሪያ በሌሊት እያደኑ በመያዝ በማጎር ላይ ይገኛሉ። በዚህ ካምፕ ዉስጥ የሚደርስባቸዉን ስቃይና እንግልት መገመት አያዳግትም። አካባቢዉን አስተዳድራለሁ የሚለዉ ደካማ ተለጣፊ ድርጅት ይህ ሁሉ ዉንብድና ሲፈፀም ዝም ብሎ ከመመልከት በቀር የወሰደዉ ምንም አይነት እርምጃ የለም።
ከወልቃይት ጠገዴ በተጨማሪ ትግራይ ውስጥ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ ባልሆኑት ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ቀጥሏል። የንግድ ድርጅቶች በእሳት ጋይተዋል፣ሰዎች እየተደበደቡ በከፍተኛ ደረጃ ቆስለዋል፤ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ላይም እንዲሁ ከባድ ጉዳት ደርሶ የሞቱም እንዳሉ ይሰማል።ሌሎቹም መግቢያ መውጫው ጠፍቷቸው በመከራ ዉስጥ ናቸው።
በጥላቻና በዘረኝነት ማጥና መቀመቅ ውስጥ የተዘፈቀው ወያኔ ላለፉት 27 አመታት በወሎ ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ማደህየት እና የመሳሰሉትን ዘርፈ-ብዙ ጥፋቶች አድርሷል፤እያደረሰም ይገኛል። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል፦
- ገና በጥዋቱ አገሩን እንደተቆጣጠረ በየአዉራጃዎች ትምህርት ቤቶች የነበሩትን የምርምር፣ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን፣ የመብራት ጀኔተሮችን፣ የግብርና ቢሮ ቁሳቁሶችን እና የመሳሰሉትን በጠራራ ፀሀይ በመዝረፍ ወደ ትግራይ አግዟል።
- ወሎን ለማዳከምና ፈፅሞ ከታሪክ ማኅደር ለማፅፋት ወያኔ ገና አገሪቱን እንደተቆጣጠረ ከወሰዳቸዉ እርምጃዎች አንዱ ወሎን ለ6 የአስተዳደር ዞኖች መክፈል ነበር። በተለይ ከወሎየዉ የስነ-ልቦናና ታሪካዊ ሁኔታዎች ዉጭ ወንድማማች የነበረዉን ህዝብ አገዉ፣ ኦሮሞ፣አርጎባ ፣አፋር በሚል የቋንቋ አጥር ከፍሎ ማዳከሙ ሳያንሰዉ ለም የሆነዉን የራያን መሬትና በወሎየነቱ የሚኮራውን የራያ ሕዝብ በጉልበት ወደ ትግራይ በመጠቅለል ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
- ሙስሊሙ ማህበረሰብ «ድምፃችን ይሰማ» ብሎ በጠየቀበት ወቅት በወሎ ላይ የደረሰውን እስር፣ እንግልት፣ ግድያና ማዋከብ ይህ ነዉ ተብሎ መዘርዘር ከባድ ነው።
- በወሎ በትላልቅ ከተሞች ዉስጥ የነበሩ ነጋዴዎችን በሰበብ ባስባቡ ግብር በመጨመርና በማዋከብ አካባቢያቸዉን ለቀዉ እንዲሄዱ አድርጓል። በተለይ በደሴ በኮምቦልቻና በወልድያ ከተሞች ዉስጥ የነበሩ ወሎየ ነጋዴዎችን ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ በነፍስ-ወከፍ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ በማስገደድ አካባቢያቸዉን ለቀዉ እንዲሄዱ በምትካቸዉም በገፍ ከትግራይ ነጋዴዎችን በማምጣት ንግዱን እንዲቆጣጠሩት አድርጓል። እነዚህ ከ200 በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች የስም ዝርዘራቸዉ በእጃችን ቢገኝም ለደህንነታቸዉ ስንል ለጊዜው ዝርዝሩን አባሪ ከማድረግ ተቆጥበናል።
- በምሰራቁ የሀገራችን ክፍል የሶማሊ ልዩ ሃይል በሚባል እራሱ ባሰለጠነውና በሚቆጣጠረው ኣጋዚ- መስል ሃይል አማካኝነት በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ ጥቃት በሚፈፅምበት ተመሳሳይ ስልት በቆቦና አካባቢው በ«አፋር ልዩ ሃይል» አማካኝነት ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝብ በየቀኑ እየተፈናቀለ ይገኛል።
- ከዚህ በፊት በጉራ-ፈርዳ፥ወለጋ፥ ሓረርጌና ቤኒ-ሻንጉል የተፈፀሙት የዘር ማፅዳት ወንጀሎች አልበቃ ብሎ ዛሬም በወለጋ በክልል ፖሊሶች ትብብር ቤቱ ተቃጥሎ በጫካ ውስጥ በአማራ ማንነቱ ተፈርጆ የሚንከራተተው አብዛኛው ወሎዬ ኢትዮጵያዊ ነው። ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ኢሰብዓዊ ወንጀሎች በተጨማሪ በየአካባቢዉ ያለፍርድ መታሰርን፣ መገደልን፣ ስራ አጥነትን ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉትን ብንዘረዝር ጊዜም አይበቃንም። ተመሳሳይ ግፎችም በጎንደር፥ በጎጃም፥ በሸዋ፥ በሃረርጌ፥ በጋምቤላና በሲዳሞ ተፈፅመዎል። በተለይም ሚሊሻዎችን በየቀየው ማሰለፍ የሕዝብ- ለሕዝብ መተላለቅ ጦርነትን አሸባሪው ወያኔ «ከኔ በኋላ ሰርዶ አይብቀል» ባለው ዛቻ መሰረት እያዘጋጀ ለመሆኑ አብይ አመላካች ስለሆነ (ሩዋንዳን፥ የመንን፥ ሶሪያን፥ አራቅን፥ዩጎዝላቪያን፥ ሶማሌንና ደቡብ ሱዳንን ልብ ይበሉ) ሁላችንንም ሊያሳስበንና ሊያስጨንቀን ይገባል።
«ወሎ የኢትዮጵያ ዉርስና ቅርስ ማኅበር» ለዚህ በአንድ አናሳ ጎሳ ላይ ተመርኩዞና በሆዳም ግብረ-ኣበሮቹ ተደግፎ በወሎ ላይና በመላዉ ኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለዉን ግፍ በአስቸኳይ አቁሞ ከቻለ ከህዝብ ጋር ታርቆ ካልቻለ ግን ስልጣኑንን ለህዝብ እስካላስረከበ ድረስ ሁሉንም ህጋዊና ፍትሀዊ መንገዶችን በመከተል ህዝባችንን የምናነቃና የምናታግል መሆኑን እየገለፅን። በተለይም በትግራይ የማጎሪያ ካምፕ ዉስጥብ ሆነ በየወህኒ ቤቶች በመሰቃየት ላይ የሚገኙትን ወጣቶችና የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እስካለቀቀ ድረስ ህዝባችን ፍርሃትን ስላሽነፈ ትግሉን እንደማያቆም ግልፅ እየሆነ መምጣቱን ልናስገነዝብ እንወዳለን።
ለሌሎች የኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ደግሞ ልዩነቶቻችንን በማጥበብ፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ ሁላችንም እንወክለዋለን ለምንለዉ ድርጅትም ይሁን ክፍለ-ሃገር የአገርህን-አድን የጋራ ግንባር በመፍጠር ላለፉት ሩብ ምእተ-አመት በህዘባችን ጫንቃ ላይ ተፈናጦ ይህንን ሁሉ ግፍ በማድረስ ላይ የሚገኜዉን እብሪተኛ የታሪክ አተላ የሆነ ቡድንን ፍፁም በቃህ ልንለዉ ይገባል እንላለን። ይቻላልም።
በኢትዮጵያ የውስጥ ጠላቶች ያሰፈኑት የጭቆና ዘመን እያከተመ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ልንገልፅና ልናሰምር የምንወደዉ ነገር ቢኖር የብዙ ነገዶች ድርና ማግ የሆነው የወሎ ህዝብ እንደ ቀድሞ እንደታሪኩ ለሀገሩ ነፃ መዉጣት የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነው። በተለይም ጎበዝ-አለቆቹን ታድጎ ሁለግብና (የኢኮኖሚ ማእቀብም ጭምር) መጠነ-ሰፊ የትግል ስልቶችን መንደፍ ለሰብዓዊና ለሲቭላዊ መብቶች ለሚደረገው የእምቢተኝነት ትግል ቁልፍነቱን ሕዝባችን እየተገነዘበ መምጣቱ ያኮራናል።
ያሸባሪዎችና የወሮበሎች ስርዓት በሕዝብ ትግል ያከትማል!
የጎሳ ካርድህን ቀደህ የዶግ አመድ አድርገው!
ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት ከባድ ፈተናዎችን ያለፈች ሉዓላዊ አገር ናት!
ድል ለወሎና ለሰፊዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ!!
=====
Wollo.org “ወሎየነት መለያችን፥ ኢትዮጵያዊነት ማንነታችን”