December 16, 2017

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች፣ ሀብታም ሀገር፤ ህዝቧም ጠንካራ ሠራተኛ ሆኖ ሳለ፤ ለህዝብ የሚያስቡ መሪዎች በማጣቷ በድህነት፣ በጦርነትና በስደት የምንታወቅ ሆነናል።

በሥልጣን ላይ ያለው የህወሀት ጎሰኛ አምባገነን ቡድን በፈጠረው ፖለቲካዊ ጭቆናና የኢኮኖሚ ዘረፋ ምክንያት ወገናችን ከትውልድ ቦታው እንዲፈናቀል፣ እንዲሰደድ፣ እንዲታሰርና እንዲገደል ሆኗል።

ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ድምጻቸውን በማሰማታቸው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እስር ቤት ታጉረው ይሰቃያሉ።

የወያኔ ዘረኛ ቡድን፣ ለአለፉት 30 ዓመታት በጎንደርና በወሎ ህዝብ ሲፈጽመው የቆየውን ጸረ ህዝብ ዘመቻ ወደ ምሥራቅና ደቡብ ኢትዮጵያ በማዛመት፤ በቅርቡ በሰላሌና በጎሬ በሌሎችም አካባቢዎች በአማራና ኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግፍ የወያኔን መሰሪ ተንኮልና ባህሪ አጋልጦታል።

የአገሪቱን ሕዝብ 70ከመቶ(70%) የሚወክለውን የአማራውና ኦሮሞው ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረው የማጥቃት ዘመቻ፣ከግለሰቦች ግድያና ማፈናቀል አልፎ አገርን የሚያፈርስና ሕዝብንና ሕዝብን እርስ በርሱ ለማጫረስ የታለመ ሴራ መሆኑን ሳይውል ሳያደር የዓለም ህዝብ ሊያውቀው የሚገባ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

የህወሀት/ኢህአዴግ አምባ-ገነን ሥርዓት በስልጣን ለመሰንበት ያለመው፣በደም እና በአጥንታቸው ሀገሪቱን ያቆሙትን የአማራንና የኦሮሞን እንዲሁም ሌሎች ማህበረሰቦችን በመለያየትና በማጋጨት በመሆኑ፤ሴራው ከሽፎ፣የነጻነት ጎሕ እንዲፈነጥቅ፣ለሀገርና ለወገን ጠበቃ ሆኖ የሚከራከር ብሄራዊ ድርጅት አስፈላጊ ሆኗል።

ይህን አብይ አላማ ተግባራዊ ለማድረግ፣በክፍለ-ሀገር የተደራጀን አምስት ድርጅቶች፤የጎጃምአለምአቀፍትብብር፣የወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር፣የመላው ሸዋ ህዝብ የኢትዮጵያውያን አንድነት ሁለገብ ማህበር፣የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነትና፣የሲዳሞ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በሐምሌ 6 ቀን 2017 ሲያትል ባደረግነዉ ታሪካዊ ጉባኤ፣አያቶቻችንና ቅድመ-አያቶቻችን በድምና አጽማቸው ጠብቀው ያቆዩንን ሀገር ዛሬ ከተጋረጠባት አደጋ ለማዳን አስተባባሪ መማክርት ፈጥረን እንቅስቃሴ መጀመራችን ይታወሳል።

እንሆ የምስራች!ለሀገራችን አንድነትና ለህዝባችን ልዕልና፤የቆመ የኢትዮጵያ ክፍለሀገራት ሕብረት ፈጥረናል።ጥንትም፣ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ጠብቀው እንዳስረከቡን ሁሉ አሁንም ከሰሜን እስከደቡብ፣ከምስራቅ እስከምዕራብ የሰፈረው ወገናችን እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ለመጭው ትውልድ አንዷን ታላቅና ባለታሪክ አገር ጠብቆ ለማስረከብ ቃል ኪዳን ገብቶ የተነሳ ጸረ ጎሰኝነት ዓላማ ያነገበ የኢትዮጵያውያን ህብረት ነው።ህብረቱን ለመቀላቀል ክፍለሃገሮች በዝግጅት ላይ ያሉ ሲሆን ያልተዘጋጁት እንዲዘጋጁና እንዲቀላቀሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናደርጋለን።

የኢትዮጵያ ሕብረት አላማዎችና ተግባሮች

1. የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ፣የህዝቧን የጸና አንድነት፣የዴሞክራሲያዊ እሴቶችን፣ፍትህን፣የህግ የበላይነትና የዜጎችን በፈለጉት የሀገሪቱ ግዛት ውስጥ የመኖርና የመሥራት መብቶችን ማስከበር፤

2. በጎሳተኮርና በቋንቋ የተመሰረተው ክልላዊ የወያኔ ሥርዓት ተወግዶ፣ሁሉም ኢትዮጵያዊ የብሄር፣የእምነት፣የጾታ፣ተጽዕኖ ሳይገድባቸው፤እኩል የሚሳተፉበት የፖለቲካ፣የማህበራዊና የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት አስተዋጽኦ ማድረግ፤

3. የወያኔ መንግሥት በሚፈጽመው ጎሳ ተኮር እርምጃ በጉልበት ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ሁሉ ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱና ለተነጠቁትና ለወደመባቸው ንብረታቸው ካሳ እንዲያገኙና ለወደፊቱም ከተመሳሳይ አደጋ የሚተርፉበት ሕጋዊ ዋስትና እንዲኖራቸው ድጋፍ መስጠት።

4. በወያኔ መራሹ ስርዓት በየክፍላተ ሃገሩ በተካሄዱት የመሬት ነጠቃዎች ሳቢያ የተፈናቀሉትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባ ለሆኑት ወገኖቻችን ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው ጥብቅና መቆም፤የቀድሞ የክፍላተሃገራት ወሰንና የሕዝብ አሰፋፈር እንዲከበር መጠየቅ።

5. ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የበርካታ ብሔረሰቦች ተወላጅና የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ ፣የብዙ ባህል ባለቤት የሆነ ሕዝብ አብሮና ተስማምቶ መኖሩ የተረጋገጠባት አገር እንደ መሆኗ መጠን ይህን ቅላፄ ማስፋፋትና መጠበቅ፤

6. በሀገር ውስጥ እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው የአሜሪካ፣አውሮፓ፣መካከለኛው ምስራቅ፣አፍሪካና አውስትራሊያ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የሕብረቱን ድጋፍ ካሚቴዎች እንዲፈጠሩ በግንባር ቀደምትነት ማስተባበር።

7. በተፈጥሮና ሰው-ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለተፈናቀሉ፣ለተሰደዱ፣ለታሰሩና ለሞቱ ወገኖቻችንና ቤተሰቦቻቸው፣የሞራልና የቁሳቁስ እርዳታ ማስተባበር፣፣በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ችግር ዓለምአቀፍ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ማድረግ፤

የሕብረት ጥሪ

ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለተገለጹት ዓላማዎች ከዳር እስከ ዳር በቃል ኪዳን ተሳሥረን አብረን እንድንሰለፍ ጥሪ እናደርጋለን።

ኢትዮጵያን የማዳን ጉዳይ ለጥቂት ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች የሚሰጥ አደራ አይደለም። በሕወሀት የዘርና ትውልድን መሰረት ባደረገ ከፋፍሎ የመግዛትፓሊሲ፤ ለዘመናት አንድ ላይ ተከባብሮ የኖረውን የኢትዮጵያን ህዝብ ነጣጥሎ ልዩነቱን ብቻ በማራገብ፤ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት፤ከይዞታው በማፈናቀልና በማንአለብኝነት ጥቂቶች የአገሪቱን ሃብት ለራሳቸውና ለውጪ ሃይሎች በመቀራመታቸው፤ብዙሃኑን በድህነት አረንቋ ውስጥ ነክረውት የበይ ተመልካች ሆኗል።ያም አልበቃም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በደካማ ጎኑ በመግባት እርስ በርሱ እንዲጋጭ አድርገውታል።ስለሆነም በልዩ ልዩ ችግር ውስጥ የተማገደው ሕዝብ ለጋራ ጥቅሙ ለሚከበርበት የስርዓት ለውጥ አብሮ እንዲሰለፍ በምናቀው አካባቢና ህብረተሰብ ውስጥ ገብተን ተገቢውን ድጋፍ ለማበርከት የተቀናጀ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተዘጋጅተናል። በሀገራችን ያንዣበበው ታሪካዊ ፈተና፣የመላው የኢትዮጵያን ልጆች አስቸኳይ ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ፣ለሁሉም ሀገር ወዳድ ግለሰቦችና ስብስቦች ጥሪ እናደርጋለን።

የኢትዮጵያሕብረት

www.ethiopianhibret.com
ethiopianhibret@gmail.com