Skip to content
ጥሩነህ ያዬ
ከቂሊንጦ ምን መልካም ነገር ሊገኝ ነው እንዳትሉኝ እንጂ፥ ብዙ የአማራና የኦሮሞ ልጆች በታጎሩበት ቂሊንጦ የሆነ መልካም ነገር ላጫውታችሁ ነው። በተለይ ዞን 4 የሚባለው የህዝብ ብሶት እየዘረዘሩ ገዥውን ስርዓት በይፋ የሞገቱ ፖለቲከኞችና ብዕረኞች፥ ከሰሜን ጎንደር አርማጭሆ የመጡ፥ አማራ ሕዝብ አሸባሪ አይደለም ብለው አደባባይ በመውጣት የወያኔን ዙፋን ያናወጡ፥ እንቢ ለማንነቴ! እንቢ ለክብሬ፣ እንቢ ለነጻነቴ በሚል ህዝባዊ ነውጥ አገዛዙን ያንቀጠቀጡ፥ በውስጣቸው ብዙ የነጻነት ጥያቄ አርግዘው አሻፈረኝ በማለት ነፍጥ ያነሱ ታጋዮች የሚገኙበት ነው ይባላል።
ቂሊንጦ ዞን 4 ውስጥ ከብዙ አማራዎች ጋር ጀግናው የኦሮሞ ልጅ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ደጄኔ ጣፋ ይገኛሉ፥ ከሰሜን ጎንደር የመጡት አንጋው ተገኝ እና መቶ ዓለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ ብዙዎች እየተመላለሰ የሚጠይቅ የቅርብ ዘመድ የሌላቸውም ይገኛሉ፥ ለእነዚህ እስረኞች ከቤት የተሰራ ምግብ ማግኘት በጣም ከባድ ነው።
የአንጋው አባት አቶ ተገኝ ከታች አርማጭሆ ተነስተው በማያውቁት አገር ብዙ ተጉዘው ለአንድ ጊዜ ቢመጡም፥ በጠባቂዎች ተከልክለው ልጃቸውን ሳያዩ እየተከዙ እንደተመለሱ ሰምቼ ነበርና እንዴት ነው ብየ ስጠይቀው፥ ከሩቅ ለመጡት የጎንደር አማራ ወጣቶች፥ የአቶ በቀለ ገርባ እና የአቶ ደጄኔ ጣፋ ቤተሰቦች የሚያደርጉላቸውን በጎነት እያነሳ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ደግነት እንዲህ ሲል አጫወተኝ፥ የኦሮሞን ህዝብ ክፉ አይንካው ደህና ነነ፥ ከመጣላቸው እያካፈሉ ይመግቡናል፥ እነ በቀለን ብሎ የመጣው ሁሉ ለእኛም ምግብ ቋጥሮ ነው ሚመጣ፥ አሁንማ የምንፈልገውን ሁሉ አውቀውታል፥ የጎንደሬ ልማድ ሆኖብነ እዚህም እንደምንግደረደር ገብቷቸው በሞቴ ማለት ጀምረዋል አለኝ እየሳቀ፥ እኔም እንባየን በጉንጬ ላይ እያጠለልኩ ትንሽ ሳቅኩኝና፥ ለካስ ያለ ነገር አይደለም እነዚህን ሰዎች የምወዳቸው አልኩኝ ለራሴ። ቀጠለና፥ እነሱ ሊለያዩን ይጥራሉ እኛ ግን እንኳን በውጭ ሆነን፥ በእስር ቤት ውስጥም አንድ ነን፥ በፍጹም አንለያይም። በተለይ እኛን መከራው እንደሚጠናብን ስለሚያውቁ ከዓይናቸው ብዙ ተሰውረን ሳንተያይ ከቆየን ምን አድርገዋቸው ይሆን ብለው በመጨነቅ ይፈልጉናል።
ከቂሊንጦ፣ ሸዋ ሮቢት እስከ ዝዋይ ስንንከራተት የተዋወቅነው የኦሮሞ ህዝብና፥ የእነ አቶ በቀለ ገርባ ወገኖች ውለታቸው በጣም ብዙ ነው። የአማራ ህዝብና የጎንደር ወገናችን እንዲያውቅልን እንፈልጋለን ሲሉ የነገሩትን አጫወተኝ፥ እኔም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሰማው መልካም ነው በማለት ሞጫጭሬ በዚህ መልክ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ።
ዛሬ በኢትዮጵያ በሚታየው ብዙ ስቃይ መሃል እሄን ተስፋ የሚሰጥ አንድነትና ትብብር ስሰማ፥ እውነትም ኢትዮጵያ አትፈርስም አልኩና ደስ አለኝ።
መልካም ሰንበት፥
Like this:
Like Loading...