[ወንድወሰን ተክሉ-ጋዜጠኛ]

**መነሻ-

ህወሃት የፖለቲካ ማርሹን ለውጫለሁ ብላል። እንደ አባባሉ ከሆነ ምናልባትም ከባለ 5ፖለቲካዊ ማርሽ አነዳድ ወደ 3እና 4ፖለቲካዊ ማርሽ ላይ ለውጦ ለውጦ ሊሆን ይችላል እንጂ ሞተሩን አቀዝቅዞ ወደ ዜሮ ማርሽ ሊቀየር ቀርቶ ዝግ ወደሚለው ፍጥነት ቁጥር ሁለት ማርሽ እንዳላስገባ ይታወቃል።

ህወሃት እየተናገረ ያለውን የመለማመጥና ብሎም ሰጥቶ የመቀበልን ፖለቲካዊ ለውጥ ማድረጉን እየገለጸ ያለው በሁለቱ የሀገሪቱና የገዢው ጥምር ኢህአዴግ ድርጅት ውስጥ በተክለ ቁመናቸውና በግዝፈታቸው የአንበሳውን ድርሻ በያዙት የኦሮሚያ ክልሉ ኦህዴድና በአማራ ክልሉ ብአዴን በኩል በተከፈተበት ተጽእኖ ምክንያት እንደሆነ እንረዳለን።

የሁለቱ ድርጅቶች ተጽእኖ መሰረቱ ውስጠ ድርጅታዊ የመለወጥ ጥያቄን ያነገበ ተጽእኖ ሳይሆን ድርጅቶቹን ደፍቆ ባሰጨነቀው ህዝባዊው ዓመጽና ጥያቄ በኩል የተፈጠረና ድርጅታዊ [ኦህዴዳዊ/ብአዴናዊ] ተጽእኖ ያልሆነ መሆኑን ስናይ ሁለቱ ድርጅቶች በስነተፈጥሮዓዊ ባህሪያቸውና ታሪካቸው ውስጥ ያልታየን ለህዝባዊው ተጽእኖ የመወገንና ብሎም ያንን ህዝባዊ ተጽእኖ ተቀብሎ በማስተጋባት ድርጅታዊ መልክና ቅርጽ ሰጥተውት በአራቱ የኢህአዴግ ጥምራዊ ድርጅት ውስጥ አቅርበውት እንዳሉ መረዳት እንችላለን።

ለዛሬው ህወሃት ድርጅታዊ መለማመጥና ሰጥቶ መቀበል ደረጃ ላይ መገኘት መንስኤው ከኢህአዴግ አራት አባል ድርጅቶች ውስጥ ከሁለቱ ማለትም ከኦህዴድና ብአዴን በኩል በተከፈተ ተጽእኖ ምክንያት ነው ቢባልም የተጽእኖውን ሰንሰለት ተከትለን ወደ ዋና ምንጩን ፍለጋ ብንጋዝ የምናገኘው የተጽእኖዎች ሁሉ ምንጭ የሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃት መራሹ መንግስት ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ ተንገሽግሾና ተማሮ የፈጠረው ህዝባዊ ዓመጽ እንደሆነ እናያለን።

የተጽእኖውን ሰንሰለት በዚህ መልክ ላስቀምጠው።

በመጀመሪያ ህወሃት በጨቋኝ አገዛዙ ሰፊውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨቆነ፣አማረረ። የህወሃት እጅ፣ እግር እና ዓይን በመሆን ኢህአዴጋዊ ተክለ ቁመናን ካጎናጸፉት ሶስቱ ድርጅቶች ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደህዴህ እኛ ታማኝነታችን እና አገልጋይነታችን ለፈጠረን ህወሃት ነውና አይመለከተንም” በማለት በጋራ ሰፊውን ህዝብ በመጨቆኑ ሂደት ተባባሪ ብቻ ሳይሆን ግንባር ቀደም ተዋናይና ተግባሪ ሆነው ቀጠሉበት።

ከሁለት ደርዘን ዓመታቶችም በሃላ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የዓመታት ብሶቱን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ባመረረ ዓመጽ ተቃውሞውን መገልጽ ይጀምራል። በተለይም በመጀመሪያ በኦሮሚያ ከህዳር 2015[2008ዓ.ም] ጀምሮ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ዓመጽ ከዘጠኝ ወር በሃላም በሀምሌ 2016[2008ዓ.ም]ላይ በተጎራባቹ የአማራ ክልል በመዛመት የዓመጹን አድማስ ሲያሰፋና ሀገራዊ ቅርጽና ይዘት ሲሰጠው ተስተውላል።

የሕዝባዊው ዓመጽ እለት በእለት አድማሱን እያሰፋ፣በሃይልና በጉልበትም እየጠነከረ የስርዓቱን አውታርና መሰረት ማናጋት ሲጀምር የወላፈኑ የመጀመሪያ ተለብላቢ የሆኑት በሁለቱ ክልሎች
ውስጥ የኢህአዴግ እጅና እግር በመሆን የድርጅቱ አስኳል በመሆን ሀገሪቷን እየገዛ ያለውን ህወሃት እያገለገሉ ያሉት ኦህዴድና ብአዴን በህዛባዊው ዓመጽ ወላፈን ክፉኛ ሲለበለቡ እናያለን።

ኦህዴድና ብአዴን እደ የገና ዳቦ በሁለት አቅጣጫ ከላይና ከታች እሳት እንደተለኮሰበት፣ በህዝባዊው ዓመጽና “በጌታዬ”በሚሉት ህወሃት ነበልባል እሳት ለመለብለብ ተገደዋል።

ህወሃትን ወክለው በአማራና ኦሮሞ ህዝብ ላይ የተንሰራፉት ብአዴን እና ኦህዴድ በሁለቱ ክልል ህዝብ የተነሳውን ጥያቄ መመለስ ባለመቻል በህዝባዊው ዓመጽ ሲለበለቡ በተመሳሳይ ወቅት ደግሞ የተነሳውን ይዝባዊ ዓመጽ በአግባቡ መቆጣጠርና ማዳፈን ባለመቻል በአሳዳጊያቸው ህወሃት በኩል በተከፈተባቸው ተመሳሳይ ነበልባል ይለበለቡ ነበርና ከዚህ ሁለት አቅጣጫ ከተሎከሰው የዓመጽ እሳት ለማምለጥ ኦህዴድና ብአዴን እንወክለዋለን ያሉትን ሁለቱን ህዝብ የይስሙላ ውክልናውን በማሽቀንጠር እውነተኛ ተወካይ በመሆን የህዝቡን ጥያቄ አንግቦ በማስተጋባትና ብሎም ወክሎ በመሰለፍ እንደሆነ በማመን ታማኝነታቸውን ከገዢያቸው ህወሃት ነፍገው በተፋላሚ መንፈስና አቋም ህወሃትን ሲገዳደሩ ማየት ችለናል።

የሁለቱ ድርጅቶች በህወሃት ላይ ማመጽ ሁለት ዓመታት ከዘለቀው ህዝባዊው ዓመጽ ተጠራርጎ ላለመጥፋት ሲባል የተወሰደ እራስን አድን አቋም እንደሆነ ብናይም ከዚህ ህዝባዊ ዓመጽ ሙሉ በሙሉ ለመዳን ይችሉ ዘንድ እውነተኛ የህዝቡ ተወካይ በመሆን ጥያቄውን አንግበው ለማስፈጸም በመነሳት ብቻ እንደሆነ የተረዱ በመሆን ከምር የሆነ ግብግብን ከህወሃት ጋር ማድረግ በጀመሩ ጥቂት ወራቶች ውስጥ ሁንቴው ኢህአዴግ የተባለውን ጥምር ገዢ ሃይል መሰረት ባናጋ ሁኔታ ለሁለት ሊሰነጥቀው መቻሉን መረዳት ይቻላል።

የህወሃት ድርጅታዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ህልውናው ተጠብቆ ሊቀጥል የሚችለው ኢህአዴግ በሚባለው ድርጅታዊ ተቋም በኩል ብቻ እንደሆነ ይታወቃል። እናም ይህ የህወሃትን የበላይነት በኢትዮጵያ ላይ በማንገስ እጅ፣እግርና ዓይን በመሆን ህወሃትን እያገለገለ ያለው ኢህአዴግ በተነሳው ህዝባዊ ዓመጽ ምክንያት ከአራቱ አባል ድርጅቶች ውስጥ ሁለቱ ለህልውናቸው ሲሉ በወሰዱት አቋም ድርጅቱ ለሁለት ሲሰነጠቅ ህወሃት ስልታዊ የሆነ የማፈግፈግ፣የመለማመጥና ብሎም ሰጥቶ በመቀበል [Compromise ]የማድረግን ሁኔታ እንዲቀበል ያስገደደው እንደሆነ ይታያል።

በዚህ አስገዳጅ ሰንሰለት ሁኔታ ህወሃት በመከላከያ፣በደህንነት፣በፌዴራሉ የስልጣንና የኢኮኖሚ ክፍፍል ላይ ከአባላቱ ኦህዴድና ብአዴን ጋር ለመጋራትና ብሎም በተነሱት ህዝባዊ ወሳኝ ጥያቄዎች ላይ ለመደራደር እንደሚፈልግ ሲገልጽ ተሰተምቷል።

ይህ አዲሱ የህወሃት ሰጥቶ የመቀበል አቋም [Compromise ] በእርግጥ ድርጅቱ ለህልውናው ሲል ወዶም ይሁን ተገዶ ያደረገውና የሚተገብረው እውነተኛ ዓላማና ውሳኔ ነውን የሚለው ጥያቄ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ አግባብ የሆነ ተጨባጭ መልስ የሚያሻው ጥያቄ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።

ከዚህ አንጻርም የህወሃትን አዲሱን የመለማመጥ አቀራረብና አቋም መንስኤውን ከላይ እንደመነሻነት ካሳየሁ ዘንዳ እውነተኛነቱ ላይም ማቀረብ ያለብኝን እውነታ ላይ ያተኮረውን ክፍል ወደ ማቅረቡ መዛወር ይኖርብኛል።

** ስልታዊው የህወሃት ልምምጣዊ አቀራረብ ሲፈተሽ-

በመጀመሪያ ህወሃት በጨቋኝ አገዛዙ ሕዝቡን አስጨነቀ። የተጨነቀው ሕዝብም ከጭንቅቱ ለመገላገል አስጨናቂውን መልሶ ማስጨነቅ ጀመረ። የተጨቋኙ ሰፊው ሕዝብ አስጨናቂ ዓመጽም በመጀመሪያ በህወሃት ውስጥ ልዩነትን በመፍጠር ድርጅቱን በሁለት አንጃ ከፈለ።

የተጨቋኙ ሕዝብ አስጨናቂው አመጽ ቀጥሎም የህወሃት ሀገር አቀፍ መግዣ፣በመበዝበዣና መጨቆኛ መሳሪያ የሆነውን ኢህአዴግን ለሁለት ሰነጠቀ።

የኢህአዴግ ድርጅታዊ ህልውና እና ታማኝ አገልጋይነቱ ለህወሃት እጅግ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ማንም ወደደም ይጥላ፣ ይቀበል አይቀበል የህወሃት ድርጅታዊ የገዢነት ህልውና በኢህአዴግ ድርጅታዊ ታማኝነት፣ታዛዥነት፣አገልጋይነት ህልውና ላይ የተመሰረተ ነው። ኢህአዴግ ከሌለ የህወሃት ፍርጅታዊ ስልጣን፣ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ፖለቲካዊ የበላይነት ህልውና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተንኮታኩቶ በተነሳበት የትግራይ አካባቢ ብቻ የሚቀር ይሆናል።

ኢህአዴግ ከሌለ ህወሃት ህወሃት ወደ ኦሮሚያ፣አማራና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያደርሱትን ፈረሶች ተነጠቀ ማለት ነው። በተለይም ከአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ከ60% በላይ የፓርላማ አባላት፣ከ70%በላይ የሀገሪቱን ሕዝብና መልክዓምድር፣ ከ65% በላይ የሀገሪቱን ተዋጊ መከላከያ ሃይል ያላቸው ኦህዴድና ብአዴን የኢህአዴግና ብሎም የአስኳሉ ህወሃት አባልነታቸውን፣ታማኝነታቸውን እና አገልጋይነታቸውን አቆሙ ማለት ለህወሃት የምጽዓት ቀን ያህል ሰማይ ምድሩን የሚያጨልምበት አስጨናቂ ክስተት በመሆኑ ዛሬ እያሳየን ያለውን የመለማመጥና የሰጥቶ የመቀበልን አቋም ብናይ ልንደነቅ አይገባም።

ማንም ሲጨነቅ -ከሚያስጨንቀው ለመገላገል የትኛውንም ነገር ሊያደርግ ይችላልና። እናም ህወሃት የተከዜን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ጎንደር፣የዓባይን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኦሮሚያ ምድር የተንሰራፋበት ፈረሱ ኦህዴድና ብአዴን “አንጋለብም” በማለት “በቃኝ አሻፈረኝ” በማለታቸው ህልውናው ለአደጋ እጅግ በመጋለጡ የተነሳ እጅግ ተደናግጦ ሲለማመጥ ታይቷል። ህወሃት ከትግራይ ባሻገር ባለችው ኢትዮጵያ ላይ የስልጣን ህልውናው እንዲቀጥል የኢህአዴግ ህልውና በተለይም የኦህዴድና ብአዴን ታማኝ አገልጋይነት ያለምንም ጥያቄ መቀጠል አለበት። ለዚህም የተከፈለውን ከፍሎ የሁለቱን ድርጅቶች ታማኝነትና ኢህአዴጋዊነትን ለማስቀጠል እየተንቀሳቀሰ እንዳለ እናያለን።

ህወሃት ሲጨነቅ ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው ዓይደለም። እጅግ ሲጨነቅ ያልተጠበቁ ግን ስልታዊ የጭንቅ ማምለጫ ዘዴዎችን ሲጠቀምም ይህ የዛሬው ልምምጥ አዲስና የመጀመሪያው ዓይደለም።

ድርጅቱ ከተፈጠረበት የደደቢት በረሃ አንስቶ አራት ኪሎ ቤተመንግስት እስኪገባና ብሎም በትረስልጣኑንም ጨብጦ ሀገሪቷን ሲገዛ በተለያየ ወቅትና ክስተቶች ይህንን መሰል ስልታዊ የጭንቅ ማምለጫ ዜዴዎችን እየተጠቀመ መምጣቱን መዘንጋት የለብንም።

መቼም ቢሆን ህወሃት የጭንቅ ማምለጫ ስልታዊ አቋሞቹን ተግብሮና ተጠቅሞበት እንደማያውቅም የ42ዓመት ታሪኩ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።

በበረሃ ቆይታው ያኔ ገና ሲነሳና ደደቢት በነበረበት ወቅት ያስጨነቁትን አቻ ታጋይ የሆኑና በሌላ ድርጅት የታቀፉ የትግራይ ልጆችን “እንታረቅ” ብሎ የታረቀ በማስመሰል አርዶና ደግሶ በመጋበዝ ካስተኛ በሃላ በተኙበት እያረደ ያሰናበተ ድርጅት አይደለምን?

በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በወቅቱ ያስጨነቀውን ቅንጅት ጋር መደራደር ይቅርና “ኢህአዴግ ከጸሃይ በታች ከማንም ጋር ይደራደራል” በማለት ያስጨነቀውን የቅንጅትን ሀገር አቀፍ አድማ አዋጅ ካሰረዘ ማግስትን በቅንጅቱ ላይ ጦርነት አውጆ ያፈራረሰው ድርጅት አይደለምን?

እጅግ በርካታ ከሆኑት ተግባራቶቹና አቋሞቹ ውስጥ ትንሽ ቆየት ያሉትን ትተን የዛሬ ዓመት ያደረገውን ብናይ – የምንረዳው እውነቷ ህወሃት በስነ-ባህሪው ሰጥቶ በመቀበል [Compromise ] ከሚባል አሰራር ጋር አለርጂክ የሆነበት ያህል ፈጽሞ የማይቀበልና የማይፈጽማቸው ተግባራት እንደሆኑ እንረዳለን።

ባለፈው ዓመት ላይ መንግስት እስከ ሕገ-መንግስት ማሻሻል ደረጃ ከተቃዋሚዎች ጋር እደራደራለሁ በማለት ተቃዋሚውን ሁሉ ሲጋብዝና ድርድሩንም ጀምሬያለሁ ሲል እንደነበረ ሁላችንም እናስታውሳለን። ግን ያንን አባባል ተተግብሮስ አይተናልን?

* ለድርድሩ የተሰበሰቡት “ድርጅቶች” ስንትና እነማን ናቸው?

* ስንቶቹ ጀምረው ስንቶቹስ ቀጠሉ?

* አጠቃላይ ድርድሩ ዛሬ ያለበት ደረጃ ምንድነው?

መልሱን ሁላችሁም ታውቁታላችሁ።

ህወሃት በ42ዓመት እድሜው ለመጀመሪያ ግዜ በታሪኩ አድርጎት የማያውቀውን የመካፈልና ብሎም በአስጨናቂ ወቅቶች ያቀረባቸውን ጭንቅ ማምለጫ ስልቶችን በእውነተኛ ተግባሩ ዘንድሮ ሲተገብር እናያለን ብላችሁ ተስፋ የምታደርጉ ካላችሁ መብታችሁ ነውና ቅዋሜ የለኝም።

እኔ ግን ህወሃት በ42ዓመቱ አድርጎት የማያውቀውን ዛሬ በስተእርጅና ያደርገዋል ብዬ እራሴን አልዋሽም።

ብሬሌ ከነቃ አይሆንም እቃ ይላል የአበው ይትባህል።

ኦህዴድና ብአዴን ምስጋና ለሕዝባዊው ዓመጽና ዛሬ የነቁ ሆነዋል። እነሱን ዳግም የህወሃት ፈረስ ሆነው ለማየት ማሰብም መብት ቢሆንም ተፈጻሚ ግን የሚሆን አይሆንም።

ህወሃትም የጭንቅ ማምለጫ ስልቶችን በማውጣት ደረጃ ዛሬ የመጀመሪያ እንዳልሆነ ሁሉ የመጨረሻውም አይሆንም። ሲተገብር እንዳልታየ ሁሉ ዘንድሮም ሲተገብር ይታያል ብለው የሚያስቡ የዋሆች ብቻ ይሆናሉ።

ሀወሃት ከዓመጸ አንጃ ጋር ልዩነቱን አቻችሎ የመቀጠል ድርጅታዊ ተፈጥሮ ኖሮት አያውቅም። በድርጅቱ ውስጥ የተለየ አመለካከትና ጥያቄ ያነሱትን በበርካታ “እንፍሽፍሽ” ብሎ በሚጠራው መንጥር ዘመቻው ስንቱን እየመነጠረ በማስወገድ እዚህ የደረሰ ድርጅት ዛሬ ከኦህዴድና ብአዴን የቀረበለትን ልዩነት ተቀብሎ በማስተናገድ ድርጅታዊ ህልውናውን ይከላከላል የሚሉ በርካታ ቢሆንም ተፈጻሚ ሆኖ የማናየው ባዶ ተስፋና ቃል ብቻ መሆኑን እራሱ ህወሃት በማንነቱ ቁልጭ አድርጎ እየነገረን ነው።

ብርሌው ከነቃ -ካልሆነ እቃ- ጠጅ ጠጪው አዲስ ብርሌ ለመግዛት ተገዳል ማለት። ያለብርሌ አይጠጣም ጠጅ።

ህወሃት የኦህዴድና ብአዴን ዓመጺ አመራርና ድርጅቶቹን መቶ በመቶ አጥፍቶ በምትካቸውም የለመደውን ተጋላቢ ታማኝ ፈረስ ለማቋቋም ወስናል።

ይህንን ውሳኔውን ለመተግበር እስኪያስችለው ግዜ መህዣ ስልት እየተጠቀመ ነው።

ይሳካለታል አይሳካለትም? የኦህዴድና ብአዴን ተራማጅ አመለካከት ያላቸው አመራሮችስ በቀላሉ ይጨፈለቃሉ ወይስ ይጨፈልቃሉ የሚለውን ነጥብ በቀጣይ እመለስበታለሁ- ቸር እንሰንብት።

—— አስተያታችሁን በኢትዮ-ሚዲያ ኢ-ሚይል ወይም በግሌ teklu7@gmail.com ልትልኩልኝ ትችላላችሁ።

ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com December 24, 2017